በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥራ ሁለት

ቤተሰብን የሚያናጉ ችግሮችን መቋቋም ትችላላችሁ

ቤተሰብን የሚያናጉ ችግሮችን መቋቋም ትችላላችሁ

1. በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ ምን ስውር ችግሮች አሉ?

አሮጌዋ መኪና በደንብ ታጥባ ተወልውላለች። ከውጪ ለሚያያት በጣም የምታብረቀርቅ ከመሆኗም በላይ አዲስ መኪና ትመስላለች። ከውስጥ ግን በዝገት እየተበላች ነው። አንዳንድ ቤተሰቦች ያሉበት ሁኔታም ልክ እንደዚሁ ነው። ከውጪ ሲታዩ ምንም ችግር የሌለባቸው ይመስላሉ፤ በፊታቸው ላይ የሚነበበው ፈገግታ ያለባቸውን ፍርሃትና ሥቃይ ይሸፍነዋል። በጓዳቸው ውስጥ የሚፈጸሙ ጎጂ የሆኑ ነገሮች ግን የቤተሰቡን ሰላም እያናጉት ነው። ይህን መዘዝ ሊያስከትሉ የሚችሉት ሁለት አስቸጋሪ ሁኔታዎች የአልኮል ሱሰኝነትና በሌሎች ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ናቸው።

የአልኮል ሱሰኝነት የሚያስከትለው ጉዳት

2. (ሀ) የአልኮል መጠጦችን መጠቀምን በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ምንድን ነው? (ለ) የአልኮል ሱሰኝነት ምንድን ነው?

2 መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጦችን ልከኛ በሆነ መንገድ መጠቀምን አያወግዝም፤ ስካርን ግን ያወግዛል። (ምሳሌ 23:​20, 21፤ 1 ቆሮንቶስ 6:​9, 10፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:​23፤ ቲቶ 2:​2, 3) ይሁን እንጂ የአልኮል ሱሰኝነት ከስካርም የከፋ ነገር ነው፤ የአልኮል መጠጦች ተገዥ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ያለ ገደብ የመጠጣት ልማድ ያስከትላል። ዐዋቂዎች የአልኮል ሱሰኞች ሊሆኑ ይችላሉ። የሚያሳዝነው ደግሞ ወጣቶችም የአልኮል ሱሰኞች ሊሆኑ መቻላቸው ነው።

3, 4. የአልኮል ሱስ በአልኮል ሱሰኛው የትዳር ጓደኛና በልጆቹ ላይ ምን ውጤቶች እንደሚያስከትል ግለጽ።

3 መጽሐፍ ቅዱስ አልኮልን አላግባብ መጠቀም የቤተሰብን ሰላም ሊያደፈርስ እንደሚችል ያመለከተው ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። (ዘዳግም 21:​18-21) የአልኮል ሱሰኝነት በመላው ቤተሰብ ላይ ጎጂ ተጽዕኖ ያሳድራል። የትዳር ጓደኛው የአልኮል ሱሰኛውን ከሱሱ ለማላቀቅ ወይም ደግሞ ተለዋዋጭ ባሕሪውን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለች። * መጠጡን ትደብቅበታለች፣ ትጥልበታለች፣ ገንዘቡን ትሸሽግበታለች፣ እንዲሁም ለቤተሰቡ፣ ለሕይወቱና አልፎ ተርፎም ለአምላክ ሲል መጠጡን እንዲተው ትማጸነዋለች፤ የአልኮል ሱሰኛው ግን እንደዚያም ሆኖ መጠጡን አይተውም። የሚወስደውን መጠጥ ለመቆጣጠር የምታደርገው ጥረት በተደጋጋሚ ሲከሽፍ በጣም ትበሳጫለች፤ ይህን የማድረግ ብቃት እንደሌላት ሆኖም ይሰማታል። ፍርሃት፣ ቁጣ፣ የጥፋተኝነት ስሜት፣ ጭንቀትና የመረበሽ ስሜት ሊያድርባት እንዲሁም በራስ የመተማመን መንፈስ ሊጎድላት ይችላል።

4 የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ወላጅ ያላቸው ልጆችም የአልኮል ሱሰኝነት ከሚያስከትለው ችግር ነፃ አይደሉም። አንዳንዶቹ አካላዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ሌሎቹ ደግሞ በፆታ ተነውረዋል። ወላጃቸው የአልኮል ሱሰኛ የሆነው በእነሱ ምክንያት እንደሆነ በማሰብ ራሳቸውን ሊወቅሱ ይችላሉ። ብዙውን ጊዜ የአልኮል ሱሰኛው ተለዋዋጭ ጠባይ ሌሎችን እንዳያምኑ ያደርጋቸዋል። በቤት ውስጥ እየተፈጸመ ስላለው ነገር በነፃነት መናገር ስለማይችሉ ስሜታቸውን አፍነው የመያዝ ልማድ ያዳብራሉ፤ ይህ ደግሞ ብዙውን ጊዜ አካላዊ ጉዳት ያስከትላል። (ምሳሌ 17:​22) እንዲህ ዓይነቶቹ ልጆች ካደጉም በኋላ በራሳቸው የማይተማመኑ ወይም ለራሳቸው አክብሮት የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ።

ቤተሰቡ ምን ሊያደርግ ይችላል?

5. የአልኮል ሱስን መቆጣጠር የሚቻለው እንዴት ነው? ይህስ ከባድ የሆነው ለምንድን ነው?

5 ምንም እንኳ ብዙ ባለሙያዎች የአልኮል ሱስ ፈውስ የሌለው ችግር እንደሆነ ቢናገሩም ከአልኮል ሙሉ በሙሉ በመራቅ ከሱሱ መላቀቅ እንደሚቻል አብዛኞቹ ይስማሙበታል። (ከ⁠ማቴዎስ 5:​29 ጋር አወዳድሩ።) ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ የአልኮል ሱሰኛው ችግር እንዳለበት አምኖ ስለማይቀበል ፈቃደኛ ሆኖ እርዳታ እንዲቀበል ማድረጉ እንዲህ እንደምናወራው ቀላል አይደለም። ሆኖም የቤተሰቡ አባላት የአልኮል ሱሱ በእነሱ ላይ ያሳደረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም አንዳንድ እርምጃዎችን ሲወስዱ የአልኮል ሱሰኛው ችግር እንዳለበት ሊገነዘብ ይችላል። የአልኮል ሱሰኞችንና ቤተሰቦቻቸውን የመርዳት ልምድ ያካበቱ አንድ ሐኪም እንዲህ ብለዋል:- “ቤተሰቡ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን በተቻለው መጠን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ለማከናወን መጣሩ ይበልጥ ጠቃሚ ይመስለኛል። የአልኮል ሱሰኛው በእሱና በተቀረው ቤተሰቡ መካከል ምን ያህል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ እያደር ግልጽ እየሆነለት ይሄዳል።”

6. የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ሰው ያለባቸው ቤተሰቦች ከሁሉ የተሻለ ምክር የሚያገኙት ከየት ነው?

6 በቤተሰባችሁ ውስጥ የአልኮል ሱሰኛ ካለ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር ሕይወታችሁን ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንድትመሩ ሊረዳችሁ ይችላል። (ኢሳይያስ 48:​17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17) የተለያዩ ቤተሰቦች የአልኮል ሱስን በተሳካ መንገድ መቋቋም እንዲችሉ የረዷቸውን አንዳንድ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንመልከት።

7. አንድ የቤተሰብ አባል የአልኮል ሱሰኛ ከሆነ ተጠያቂው ማን ነው?

7 ጥፋቱን ሁሉ በራሳችሁ ላይ አታላኩ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሸክም ይሸከማል፤’ እንዲሁም “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” ሲል ይናገራል። (ገላትያ 6:​5፤ ሮሜ 14:​12) የአልኮል ሱሰኛው ተጠያቂዎቹ የቤተሰቡ አባላት እንደሆኑ አድርጎ ለመናገር ይሞክር ይሆናል። ለምሳሌ ያህል “ባታበሳጩኝ አልጠጣም ነበር” ሊል ይችላል። ሌሎቹ በዚህ አባባሉ የሚስማሙ ሆነው ከተገኙ በጠጪነቱ እንዲገፋበት እያበረታቱት ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ሁኔታዎች ለችግር ቢያጋልጡን ወይም ደግሞ ሌሎች ሰዎች አግባብ ያልሆነ ድርጊት ቢፈጽሙብን እንኳ የአልኮል ሱሰኞችን ጨምሮ ሁላችንም ለምናደርገው ነገር ተጠያቂዎች ነን።​—⁠ከፊልጵስዩስ 2:​12 ጋር አወዳድሩ።

8. የአልኮል ሱሰኛው የራሱ ችግር ያስከተላቸውን መዘዞች ራሱ እንዲወጣ መርዳት የሚቻልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

8 የአልኮል ሱሰኛውን ሁልጊዜ ጠጪነቱ ከሚያስከትልበት መዘዝ መታደግ እንዳለባችሁ ሆኖ ሊሰማችሁ አይገባም። ስለ ቁጡ ሰው የተነገረ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ የአልኮል ሱሰኛ በሆነ ሰውም ላይ በእኩል ደረጃ ሊሠራ ይችላል:- “አንድ ጊዜ ከችግሩ ልታወጣው ብትሞክር፣ ሌላ ጊዜም እንዲሁ ማድረግህ አይቀርም።” (ምሳሌ 19:​19 የ1980 ትርጉም) የአልኮል ሱሰኛው ጠጪነቱ የሚያስከትለውን መዘዝ እንዲቀምስ አድርጉት። ያዝረከረከውን ነገር ሁሉ ራሱ ያስተካክል፤ ወይም ደግሞ ከጠጣ በኋላ በነጋታው ጠዋት ራሱ ለአሠሪው ይደውል።

9, 10. የአልኮል ሱሰኛ ያለባቸው ቤተሰቦች እርዳታ ማግኘት የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? በተለይ ደግሞ የማንን እርዳታ ለማግኘት መጣር አለባቸው?

9 የሌሎችን እርዳታ ተቀበሉ። ምሳሌ 17:​17 “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል” ሲል ይናገራል። በቤተሰባችሁ ውስጥ የአልኮል ሱሰኛ ካለ መከራ ይኖራል። እርዳታ ያስፈልጋችኋል። ‘ከእውነተኛ ወዳጆች’ እርዳታ ለማግኘት አታመንቱ። (ምሳሌ 18:​24) ችግሩን የሚረዱ ወይም ደግሞ ተመሳሳይ ሁኔታ የገጠማቸውን ሰዎች ማነጋገራችሁ ማድረግ ያለባችሁንና ማድረግ የሌለባችሁን ነገር በተመለከተ ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክሮች እንድታገኙ ሊረዳችሁ ይችላል። ሆኖም ሚዛናዊ መሆን ይኖርባችኋል። ማነጋገር ያለባችሁ እምነት የምትጥሉባቸውንና ‘ምሥጢራችሁን’ የሚጠብቁ ሰዎችን ነው።​—⁠ምሳሌ 11:​13

10 በክርስቲያን ሽማግሌዎች የመታመንን ልማድ አዳብሩ። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች ትልቅ የመጽናኛ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ የጎለመሱ ወንዶች የአምላክን ቃል በሚገባ የተማሩ ከመሆናቸውም በላይ መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በሥራ በመተርጎም ረገድ ጥሩ ልምድ ያካበቱ ናቸው። “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ” ሆነው ሊገኙ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 32:​2) ክርስቲያን ሽማግሌዎች መላውን ጉባኤ ጎጂ ከሆኑ ተጽዕኖዎች የሚጠብቁ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ችግር ያለባቸውን ግለሰቦች ያጽናናሉ፣ ያነቃቃሉ፣ እንዲሁም በግል እርዳታ ይሰጣሉ። እነሱ በሚሰጡት እርዳታ ሙሉ በሙሉ ተጠቀሙ።

11, 12. የአልኮል ሱሰኛ ላለባቸው ቤተሰቦች ከሁሉ የተሻለውን እርዳታ የሚሰጠው ማን ነው? ይህ እርዳታ የሚሰጠውስ እንዴት ነው?

11 ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ይሖዋ ኃይል እንዲሰጣችሁ ጠይቁት። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፣ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” ሲል በጋለ ስሜት ያረጋግጥልናል። (መዝሙር 34:​18) የአልኮል ሱሰኛ ከሆነ የቤተሰብ አባል ጋር አብራችሁ መኖራችሁ በሚያሳድርባችሁ ተጽዕኖ የተነሳ ልባችሁ በሐዘን ቢደቆስ ወይም መንፈሳችሁ ቢጎዳ ‘ይሖዋ ቅርብ’ መሆኑን ማወቅ ይኖርባችኋል። ቤተሰባችሁ ምን ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለ ያውቃል።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​6, 7

12 ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የተናገረውን ማመናችሁ ጭንቀትን ለመቋቋም ሊረዳችሁ ይችላል። (መዝሙር 130:​3, 4፤ ማቴዎስ 6:​25-34፤ 1 ዮሐንስ 3:​19, 20) የአምላክን ቃል ማጥናታችሁና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በሕይወታችሁ ውስጥ በሥራ ላይ ማዋላችሁ በየዕለቱ የሚያጋጥማችሁን ችግር እንድትቋቋሙ “ከወትሮው የላቀ ኃይል” ሊያስታጥቃችሁ የሚችለውን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እርዳታ እንድታገኙ ያስችላችኋል።​—⁠2 ቆሮንቶስ 4:​7 NW *

13. ብዙ ቤተሰቦችን የሚያነጋው ሁለተኛው ችግር ምንድን ነው?

13 አልኮልን አላግባብ መጠቀም ብዙ ቤተሰቦችን የሚያናጋ ሌላ ችግር ማለትም በቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት መፈጸምን ሊያስከትል ይችላል።

በቤተሰብ አባላት ላይ የሚፈጸም ጥቃት የሚያስከትለው ጉዳት

14. በቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት መፈጸም የተጀመረው መቼ ነው? በዛሬው ጊዜ በዚህ ረገድ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

14 በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የጥቃት እርምጃ የተፈጸመው የአንድ ቤተሰብ አባላት በሆኑት በሁለቱ ወንድማማቾች ማለትም በቃየልና በአቤል መካከል ነው። (ዘፍጥረት 4:​8) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ዘር፣ በቤተሰብ አባላት ላይ በሚፈጸም የተለያየ ዓይነት ጥቃት ሲሠቃይ ቆይቷል። ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ባሎች፣ በባሎቻቸው ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ ሚስቶች፣ ትንንሽ ልጆቻቸውን ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የሚደበድቡ ወላጆችና በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን የሚያንገላቱ ትልልቅ ልጆች አሉ።

15. የቤተሰብ አባላት በሚፈጸምባቸው ጥቃት ስሜታቸው የሚጎዳው እንዴት ነው?

15 በቤተሰብ አባላት ላይ የሚፈጸም ጥቃት አካላዊ ጠባሳ ብቻ ጥሎ የሚያልፍ አይደለም። አንዲት ባሏ ይደበድባት የነበረች ሚስት እንዲህ ብላለች:- “ልትቋቋሙት የሚገባ ከባድ የጸጸትና የውርደት ስሜት ይሰማችኋል። አብዛኛውን ጊዜ አስፈሪ ቅዠት ውስጥ እንደነበራችሁ አድርጋችሁ በማሰብ ጠዋት አልጋችሁ ውስጥ መቆየት ትፈልጋላችሁ።” በራሳቸው ላይ ጥቃት የተፈጸመባቸው ወይም ደግሞ በሌሎች የቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት ሲፈጸም ያዩ ልጆች ወደፊት ካደጉ በኋላ እነርሱም በራሳቸው ቤተሰብ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ሊፈጽሙ ይችላሉ።

16, 17. በስሜት ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ምንድን ነው? የቤተሰብ አባላት በዚህ የሚነኩት እንዴት ነው?

16 በቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት የሚፈጸመው በመደብደብ ብቻ አይደለም። ብዙውን ጊዜ ጥቃቱ የሚሰነዘረው በቃላት ነው። ምሳሌ 12:​18 [የ1980 ትርጉም] “ያለ ጥንቃቄ የተነገረ ቃል እንደ ሰይፍ ያቆስላል” ሲል ይገልጻል። መሳደብና መጮኽ፣ እንዲሁም ሁልጊዜ መተቸት፣ ማዋረድና አካላዊ ጥቃት ለመሰንዘር መዛት በቤተሰብ አባላት ላይ ‘የሚያቆስል’ ጥቃት ከሚፈጸምባቸው መንገዶች መካከል የሚደመሩ ናቸው። በስሜት ላይ የሚሰነዘር ጥቃት የሚያስከትለው ቁስል የማይታይ ከመሆኑም በላይ ብዙውን ጊዜ የሌሎችን ትኩረት ሳያገኝ ይቀራል።

17 ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ ልጆችን ዘወትር በመተቸት እንዲሁም ችሎታቸውን፣ እውቀታቸውን ወይም ደግሞ ዋጋማነታቸውን ዝቅ በማድረግ በስሜታቸው ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት ነው። እንዲህ ዓይነቱ በቃላት የሚሰነዘር ጥቃት የአንድን ልጅ ቅስም ሊሰብረው ይችላል። ሁሉም ልጆች ተግሣጽ እንደሚያስፈልጋቸው አይካድም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ “ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው” ሲል ለአባቶች ጥብቅ መመሪያ ይሰጣል።​—⁠ቆላስይስ 3:​21

በቤተሰብ አባላት ላይ የሚፈጸምን ጥቃት ማስወገድ የሚቻልበት መንገድ

እርስ በርስ የሚዋደዱና የሚከባበሩ ክርስቲያን ባልና ሚስት በመካከላቸው የሚፈጠረውን አለመግባባት ወዲያውኑ ለመፍታት ጥረት ያደርጋሉ

18. በቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት የመፈጸም ሐሳብ የሚጸነሰው የት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ድርጊት ለማቆም የሚያስችለው ነገር ምን እንደሆነ ይናገራል?

18 በቤተሰብ አባላት ላይ ጥቃት የመፈጸም ሐሳብ የሚጸነሰው በልብና በአእምሮ ውስጥ ነው፤ ወደ ድርጊት የሚያሸጋግረን በውስጣችን የምናስበው ነገር ነው። (ያዕቆብ 1:​14, 15) ጥቃቱን ማቆም እንዲቻል ጥቃቱን የሚሰነዝረው ግለሰብ አስተሳሰቡን መለወጥ አለበት። (ሮሜ 12:​2) እንዲህ ማድረግ ይቻላልን? አዎ፣ ይቻላል። የአምላክ ቃል ሰዎችን የመለወጥ ኃይል አለው። እንደ “ምሽግ” የጠነከሩ ጎጂ አስተሳሰቦችን መንግሎ ማውጣት ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 10:​4፤ ዕብራውያን 4:​12) ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲህ ዓይነቶቹን ሰዎች ሙሉ በሙሉ እንዲለወጡ ሊረዳቸው የሚችል በመሆኑ አዲስ ሰውነት እንደሚለብሱ ተገልጿል።​—⁠ኤፌሶን 4:​22-24፤ ቆላስይስ 3:​8-10

19. አንድ ክርስቲያን የትዳር ጓደኛውን እንዴት መመልከትና መያዝ አለበት?

19 ለትዳር ጓደኛችሁ ሊኖራችሁ የሚገባ አመለካከት። የአምላክ ቃል “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። የገዛ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል” ይላል። (ኤፌሶን 5:​28) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ባል ሚስቱን “ልክ እንደ ተሰባሪ ዕቃ በክብር” ሊይዛት እንደሚገባ ይገልጻል። (1 ጴጥሮስ 3:​7 NW) ሚስቶች “ባሎቻቸውን የሚወዱ” እንዲሆኑና ለባሎቻቸው “ጥልቅ አክብሮት” እንዲኖራቸው ተመክረዋል። (ቲቶ 2:​4፤ ኤፌሶን 5:​33 NW) ፈሪሃ አምላክ ያለው የትኛውም ባል ሚስቱን እየደበደበም ሆነ በቃላት እያቆሰለ አከብራታለሁ ብሎ ሊናገር እንደማይችል የታወቀ ነው። በባሏ ላይ የምትጮኽ፣ ባሏን በአሽሙር የምትዘልፍ ወይም ዘወትር የምትነቅፍ ሚስት ባሏን እንደምትወድና እንደምታከብር ልትናገር አትችልም።

20. ወላጆች ልጆቻቸውን በተመለከተ በማን ፊት ተጠያቂዎች ናቸው? ወላጆች ከልጆቻቸው ተገቢ ያልሆነ ነገር መጠበቅ የሌለባቸውስ ለምንድን ነው?

20 ለልጆች ሊኖራችሁ የሚገባ ትክክለኛ አመለካከት። ልጆች የወላጆቻቸው ፍቅርና ትኩረት ያሻቸዋል። የአምላክ ቃል፣ ልጆች ‘የይሖዋ ስጦታና የእርሱ ዋጋ’ እንደሆኑ ይናገራል። (መዝሙር 127:​3) ወላጆች በይሖዋ ፊት ይህን ስጦታ በእንክብካቤ የመያዝ ኃላፊነት አለባቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ‘ልጅነት ጠባይና’ ስለ ልጆች “ስንፍና” ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 13:​11፤ ምሳሌ 22:​15) ወላጆች ልጆቻቸው አስተዋይነት የጎደለው ድርጊት ሲፈጽሙ ቢመለከቱ ሊገረሙ አይገባም። ወጣቶች ዐዋቂዎች አይደሉም። ወላጆች አንድ ልጅ ዕድሜው፣ ያደገበት ቤተሰብ ሁኔታና ችሎታው ከሚፈቅድለት በላይ የሆነ ነገር ሊጠብቁበት አይገባም።​—⁠ዘፍጥረት 33:​12-14ን ተመልከቱ።

21. ለአረጋውያን ወላጆች ሊኖረን የሚገባው አምላካዊ አመለካከትና አያያዝ ምንድን ነው?

21 ለአረጋውያን ወላጆች ሊኖራችሁ የሚገባው አመለካከት። ዘሌዋውያን 19:​32 “በሽበታሙ ፊት ተነሣ፣ ሽማግሌውንም አክብር” ይላል። በዚህ መንገድ የአምላክ ሕግ አረጋውያንን እንድናከብርና ከፍ አድርገን እንድንመለከት ያበረታታል። አረጋዊው ወላጅ በቀላሉ የማይረካ ሲሆን ወይም ደግሞ በሽተኛ ከሆነ፣ ከዚያም አልፎ ደግሞ የመንቀሳቀስም ሆነ የማሰብ ችሎታው ዘገምተኛ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱን ክብር መስጠት ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ያም ሆኖ ግን ልጆች ‘ለወላጆቻቸው ብድራት መመለስ እንዳለባቸው’ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 5:​4) ይህ አረጋውያን ወላጆችን በክብር መያዝ አልፎ ተርፎም በገንዘብ መደጎም ማለት ሊሆን ይችላል። አረጋውያን ወላጆችን በአካላዊ ሁኔታም ሆነ በሌላ መንገድ ማንገላታት መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያዝዘን ነገር ጋር ፈጽሞ የሚጋጭ ነው።

22. በቤተሰብ አባላት ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለማስወገድ ቁልፍ የሆነ ሚና የሚጫወተው ባሕርይ ምንድን ነው? ይህን ባሕርይ ማሳየት የሚቻለውስ እንዴት ነው?

22 ራስን የመግዛት ባሕርይ አዳብሩ። ምሳሌ 29:​11 “ሰነፍ ሰው ቁጣውን ሁሉ ያወጣል፤ ጠቢብ ግን በውስጡ ያስቀረዋል” ይላል። መንፈስህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው? ብስጭት በውስጣችሁ ሥር እንዲሰድ ከመፍቀድ ይልቅ በመካከላችሁ የተፈጠረውን አለመግባባት ወዲያውኑ ለመፍታት ጥረት አድርጉ። (ኤፌሶን 4:​26, 27) ራሳችሁን መቆጣጠር እንደተሳናችሁ ከተሰማችሁ ከአካባቢው ዞር ለማለት ሞክሩ። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ራስን የመግዛት ባሕርይ እንድታፈሩ ይረዳችሁ ዘንድ ጸልዩ። (ገላትያ 5:​22, 23) ወጣ ብሎ በእግር መንሸራሸር ወይም ደግሞ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መሥራት ስሜታችሁን ለመቆጣጠር ሊረዳችሁ ይችላል። (ምሳሌ 17:​14, 27) ‘ለቁጣ የዘገያችሁ’ ለመሆን ጥረት አድርጉ።​—⁠ምሳሌ 14:​29

መለያየት ወይስ አብሮ መኖር?

23. አንድ የክርስቲያን ጉባኤ አባል ምንም የንስሐ ፍሬ ሳያሳይ የቤተሰብ አባላቱን መደብደብን ጨምሮ በተደጋጋሚ የቁጣ ውርጅብኝ የሚያወርድባቸው ከሆነ ምን እርምጃ ሊወሰድበት ይችላል?

23 መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሚያወግዛቸው ሥራዎች ብሎ ከፈረጃቸው ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ‘ጥል፣ ክርክርና ቁጣ’ ሲሆኑ “እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት” እንደማይወርሱ ይገልጻል። (ገላትያ 5:​19-21) ስለዚህ ክርስቲያን ነኝ እያለ በሚያደርገው ነገር ምንም የጸጸት ስሜት ሳይሰማው በተደጋጋሚ ጊዜያት በትዳር ጓደኛውም ሆነ በልጆቹ ላይ የቁጣ ውርጅብኝ የሚያወርድ፣ ምናልባትም ደግሞ ከዚያም አልፎ የሚማታ ከክርስቲያን ጉባኤ ሊወገድ ይችላል። (ከ⁠2 ዮሐንስ 9, 10 ጋር አወዳድሩ።) በዚህ መንገድ ጉባኤው አግባብ ያልሆነ ድርጊት ከሚፈጽሙ ሰዎች የጠራ ይሆናል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 5:​6, 7፤ ገላትያ 5:​9

24. (ሀ) አግባብ ያልሆነ ድርጊት የሚፈጸምባቸው የትዳር ጓደኞች ምን ለማድረግ ሊመርጡ ይችላሉ? (ለ) አሳቢ የሆኑ ጓደኞችና ሽማግሌዎች አግባብ ያልሆነ ድርጊት የሚፈጸምበትን ባለ ትዳር እንዴት ሊረዱት ይችላሉ? ሆኖም ምን ማድረግ የለባቸውም?

24 ምንም ዓይነት የመለወጥ ምልክት በማያሳይ ክፉ የትዳር ጓደኛ በየጊዜው እየተደበደቡ ያሉ ክርስቲያኖችስ ምን ማድረግ ይችላሉ? አንዳንዶቹ የራሳቸው የሆነ ምክንያት ስላላቸው አግባብ ያልሆነ ድርጊት ከሚፈጽምባቸው የትዳር ጓደኛቸው ጋር መቆየት መርጠዋል። ሌሎቹ ግን አካላዊ፣ አእምሯዊና መንፈሳዊ ጤንነታቸው አልፎ ተርፎም ሕይወታቸው አስጊ ሁኔታ ላይ እንደወደቀ ስለተሰማቸው ከትዳር ጓደኛቸው መለየት መርጠዋል። በራሱ የቤተሰብ አባል ጥቃት የሚፈጸምበት ሰው በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ወቅት የሚወስደው እርምጃ በይሖዋ ፊት የሚወስነው የራሱ የግል ውሳኔ ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:​10, 11) አሳቢ የሆኑ ጓደኞች፣ ዘመዶች ወይም ደግሞ ክርስቲያን ሽማግሌዎች እርዳታና ምክር ሊሰጡ ይችላሉ፤ ሆኖም ግለሰቡ ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ እንዲወስድ ሊጫኑት አይገባም። ይህ የራሱ ወይም የራሷ የግል ውሳኔ ነው።​—⁠ሮሜ 14:​4፤ ገላትያ 6:​5

ጎጂ ችግሮች የሚወገዱበት ጊዜ

25. ይሖዋ ለቤተሰብ ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

25 ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን በጋብቻ ሲያጣምራቸው ቤተሰቦች በአልኮል ሱስ፣ በሌሎች ላይ በሚፈጸም ጥቃትና እነዚህን በመሳሰሉ ጎጂ ችግሮች እንዲፈራርሱ አስቦ አልነበረም። (ኤፌሶን 3:​14, 15) ቤተሰብ የተቋቋመው ፍቅርና ሰላም የሰፈነበትና እያንዳንዱ አባል አእምሯዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶቹ የሚሟሉበት ቦታ እንዲሆን ታስቦ ነው። ኃጢአት ከተፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ ግን የቤተሰብ ሕይወት በፍጥነት እየተበላሸ ሄዷል።​—⁠ከ⁠መክብብ 8:​9 ጋር አወዳድሩ።

26. ይሖዋ ካወጣቸው ብቃቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር የሚጥሩ ሁሉ ምን ዓይነት ጊዜ ይጠብቃቸዋል?

26 የሚያስደስተው ግን ይሖዋ ለቤተሰብ ያለው ዓላማ ያልተለወጠ መሆኑ ነው። ሰዎች ‘የሚያስፈራቸው ሳይኖር ተዘልለው የሚቀመጡበት’ አዲስ ሰላማዊ ዓለም እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል። (ሕዝቅኤል 34:​28) በዚያ ጊዜ የአልኮል ሱሰኝነት፣ በቤተሰብ አባላት ላይ የሚፈጸም ጥቃትና በአሁኑ ጊዜ ቤተሰቦችን እያፈራረሱ ያሉ ሌሎች ችግሮች የተረሱ ነገሮች ይሆናሉ። ሰዎች ፍርሃታቸውንና ስቃያቸውን ለመደበቅ ብለው ሳይሆን በሚያገኙት ‘ብዙ ሰላም በመደሰት’ ፊታቸው በፈገግታ ይሞላል።​—⁠መዝሙር 37:​11

^ አን.3 የአልኮል ሱሰኛውን በተባዕታይ ጾታ የገለጽነው ቢሆንም እዚህ ላይ የተጠቀሱት መሠረታዊ ሥርዓቶች የአልኮል ሱሰኛ በሆኑ ሴቶችም ላይ ይሠራሉ።

^ አን.12 በአንዳንድ አገሮች ለአልኮል ሱሰኞችና ለቤተሰቦቻቸው የባለሙያ እርዳታ የሚሰጡ የሕክምና ማዕከሎች፣ ሆስፒታሎችና ከዚህ ሱስ ለመላቀቅ የሚረዱ ፕሮግራሞች አሉ። በእንዲህ ዓይነቱ እርዳታ መጠቀም አለመጠቀሙ የግል ውሳኔ ነው። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተሻለው ሕክምና ይኼኛው ነው ብሎ ሐሳብ አያቀርብም። ይሁን እንጂ አንድ ሰው እርዳታ ለማግኘት በሚጥርበት ጊዜ ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚያስጥሱ ነገሮች እንዳይፈጽም መጠንቀቅ አለበት።