በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ አሥራ ሦስት

ከሠራው ስህተት ተምሯል

ከሠራው ስህተት ተምሯል

1, 2. (ሀ) ዮናስ በራሱም ሆነ በመርከበኞቹ ላይ ምን ችግር እንዲፈጠር አደረገ? (ለ) የዮናስን ታሪክ መመርመራችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

ዮናስ፣ የሚሰማውን የሚረብሽ ድምፅ ዝም ማሰኘት ቢችል ደስ ባለው ነበር። ዮናስን የረበሸው የመርከቧ ሸራ በተወጠረባቸው ገመዶች መካከል የሚያልፈው ኃይለኛ ነፋስ የሚፈጥረው ፉጨትና ከመርከቧ ጋር እየተላተመ ሳንቃዋን የሚያንቃቃው ኃይለኛ ማዕበል ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይበልጥ ያስጨነቀው የመርከቧ አዛዥና ሠራተኞች መርከቧን ከመስመጥ ለማዳን ሲታገሉ የሚያሰሙት ጩኸትና ሁካታ ነበር። ዮናስ እነዚህ ሁሉ ሰዎች በእሱ ምክንያት ሊያልቁ እንደሆነ ተሰምቶታል።

2 ዮናስ እንዲህ ያለ አጣብቂኝ ሁኔታ ውስጥ ሊገባ የቻለው እንዴት ነው? ከአምላኩ ከይሖዋ ጋር ካለው ግንኙነት ጋር በተያያዘ አንድ ከባድ ስህተት ሠርቷል። የሠራው ስህተት ምን ነበር? የፈጸመው ስህተት ፈጽሞ ሊስተካከል የማይችል ነበር? ከእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ብዙ የምንማረው ነገር አለ። ለምሳሌ ያህል፣ የዮናስ ታሪክ ጠንካራ እምነት ያላቸው ሰዎችም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ስህተት ሊሠሩ እንዲሁም የፈጸሙትን ስህተት ሊያርሙ እንደሚችሉ እንድናስተውል ይረዳናል።

ከገሊላ የተነሳ ነቢይ

3-5. (ሀ) ብዙ ሰዎች ስለ ዮናስ ሲያስቡ ቶሎ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ምንድን ነው? (ለ) ስለ ዮናስ የኋላ ታሪክ ምን የምናውቀው ነገር አለ? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ሐ) ዮናስ የነቢይነት አገልግሎቱን ማከናወን ከባድ ወይም አስቸጋሪ ሆኖበት ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

3 ሰዎች ስለ ዮናስ ሲያስቡ ቶሎ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው ደካማ ጎኑ ይኸውም ሳይታዘዝ መቅረቱ ወይም ግትርነቱ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ስለዚህ ሰው ልናውቀው የሚገባ ብዙ ነገር አለ። ዮናስ የይሖዋ አምላክ ነቢይ ሆኖ እንዲያገለግል መመረጡን ልብ ልንል ይገባል። ታዲያ ታማኝ ወይም ጻድቅ ባይሆን ኖሮ ይሖዋ እንዲህ ላለው ከባድ ኃላፊነት ይመርጠው ነበር?

ዮናስ ከደካማ ጎኑ ይበልጥ ጎልተው የሚታዩ መልካም ባሕርያት አሉት

4 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ዮናስ የኋላ ታሪክ ብዙ የሚገልጸው ነገር የለም። (2 ነገሥት 14:25ን አንብብ።) ዮናስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ካደገባት ከናዝሬት አራት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ የምትገኘው የጋትሔፌር ከተማ ሰው ነው። * ዮናስ ነቢይ ሆኖ ያገለገለው አሥሩን ነገዶች ያቀፈውን የእስራኤልን መንግሥት ይገዛ በነበረው በዳግማዊ ኢዮርብዓም የግዛት ዘመን ነበር። ኤልያስ ከኖረ ረጅም ጊዜ ያለፈ ሲሆን በእሱ እግር የተተካው ኤልሳዕም ቢሆን በኢዮርብዓም አባት የግዛት ዘመን ሞቷል። ይሖዋ በእነዚህ ነቢያት ተጠቅሞ የበኣልን አምልኮ ያስወገደ ቢሆንም እስራኤላውያን ዳግመኛ ሆን ብለው የአምላክን ትእዛዝ መጣስ ጀምረው ነበር። በዚያን ዘመን ምድሪቱ የምትተዳደረው ‘በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር ያደርግ’ በነበረ ንጉሥ ነበር። (2 ነገ. 14:24) ስለሆነም ዮናስ አገልግሎቱን ማከናወን ከባድ ወይም አስቸጋሪ እንደሚሆንበት ጥርጥር የለውም። ያም ሆኖ ኃላፊነቱን በታማኝነት ተወጥቷል።

5 ይሁንና አንድ ቀን በዮናስ ሕይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ተከሰተ። ዮናስ ከይሖዋ አንድ ተልእኮ ተቀበለ፤ ሆኖም ይህን ተልእኮ መወጣት በጣም ከባድ ሆኖበት ነበር። ይሖዋ የሰጠው ተልእኮ ምን ነበር?

‘ወደ ነነዌ ሂድ’

6. ይሖዋ ለዮናስ ምን ተልእኮ ሰጠው? ይህ ተልእኮ አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

6 ይሖዋ ዮናስን “ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ፣ በእርሷ ላይ ስበክ፤ ክፋቷ በእኔ ፊት ወጥቶአልና” አለው። (ዮናስ 1:2) ይህ ተልእኮ አስቸጋሪ ሊሆን የሚችልበትን ምክንያት መረዳት አያዳግትም። የነነዌ ከተማ በስተ ምሥራቅ 800 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ የምትገኝ ሲሆን በእግር ተጉዞ ወደዚች ከተማ ለመድረስ አንድ ወር ገደማ ይፈጅ ነበር። ይሁን እንጂ ጉዞው ከሚያስከትለው ውጣ ውረድ ይበልጥ ዮናስን ሊያሳስበው የሚችል ሌላም ጉዳይ ነበር። ዮናስ በነነዌ ለሚኖሩት በጣም ክፉና አረመኔ የሆኑ አሦራውያን የይሖዋን የፍርድ መልእክት ማወጅ ነበረበት። የአምላክ ሕዝቦች እንኳ ለመልእክቱ ጥሩ ምላሽ ካልሰጡ ከእነዚህ አረማውያን ምን ደህና ነገር ሊጠብቅ ይችላል? አንድ የይሖዋ አገልጋይ ብቻውን በጣም ሰፊ በሆነችውና ‘የደም ከተማ’ ተብላ በተጠራችው በነነዌ እንዴት የተሳካ ሥራ ሊያከናውን ይችላል?—ናሆም 3:1, 7

7, 8. (ሀ) ዮናስ ይሖዋ ከሰጠው ተልእኮ ለመሸሽ ምን ያህል ቆርጦ ነበር? (ለ) ዮናስ ፈሪ ነበር ብለን ለመደምደም መቸኮል የሌለብን ለምንድን ነው?

7 ዮናስ እነዚህ ነገሮች ሳያሳስቡት እንደማይቀሩ ልንጠብቅ እንችላለን። በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ቢኖር ግን ሸሽቶ መሄዱን ነው። ይሖዋ ያዘዘው ወደ ምሥራቅ እንዲሄድ ቢሆንም እሱ ግን ወደ ምዕራብ አቅጣጫ የቻለውን ያህል ርቆ ተጓዘ። ከዚያም ኢዮጴ ወደተባለች የወደብ ከተማ በመውረድ ወደ ተርሴስ የምትሄድ መርከብ ተሳፈረ። አንዳንድ ምሁራን ተርሴስ የምትገኘው በስፔን እንደነበር ይገልጻሉ። ይህ እውነት ከሆነ ዮናስ መጓዝ የፈለገው ከነነዌ 3,500 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ ስፍራ ነበር ማለት ነው። በታላቁ ባሕር ላይ ከአንዱ ጫፍ ተነስቶ ወደ ሌላኛው ጫፍ የሚደረገው እንዲህ ያለው ጉዞ አንድ ዓመት ያህል ሊፈጅ ይችል ነበር! ዮናስ ይሖዋ ከሰጠው ተልእኮ ለመሸሽ ያን ያህል ቆርጦ ነበር!—ዮናስ 1:3ን አንብብ።

8 ታዲያ ይህ ሁኔታ ዮናስ ፈሪ ነበር ብለን እንድንደመድም ሊያደርገን ይገባል? እንዲህ ብለን ለመደምደም መቸኮል የለብንም። ቀጥለን እንደምንመለከተው ዮናስ አስደናቂ ድፍረት አሳይቷል። ይሁንና ልክ እንደ እኛ ዮናስም ያሉበትን በርካታ ድክመቶች ለማሸነፍ የሚታገል ፍጹም ያልሆነ ሰው ነበር። (መዝ. 51:5) ከእኛ መካከል በፍርሃት ርዶ የማያውቅ ማን አለ?

9. አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ስለሰጠን ተልእኮ ምን ሊሰማን ይችላል? በዚህ ጊዜስ የትኛውን ሐቅ ማስታወስ ይኖርብናል?

9 አንዳንድ ጊዜ አምላክ፣ አስቸጋሪ ብሎም ፈጽሞ የማይቻል የሚመስል ነገር እንድናደርግ ሊጠይቀን ይችላል። ሁሉም ክርስቲያኖች እንዲያከናውኑት የሚጠበቅባቸው የአምላክን መንግሥት ምሥራች የመስበኩ ሥራ እንኳ በጣም ከባድ ሆኖ ይታየን ይሆናል። (ማቴ. 24:14) ኢየሱስ “በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል” በማለት የተናገረውን ሐቅ በቀላሉ ልንዘነጋ እንችላለን። (ማር. 10:27) ይህን ሐቅ የዘነጋንባቸው አጋጣሚዎች ካሉ ዮናስ ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መረዳት አያዳግተንም። ይሁን እንጂ ዮናስ መሸሹ ምን መዘዝ አስከተለበት?

ይሖዋ ታዛዥ ያልሆነውን ነቢይ ገሠጸው

10, 11. (ሀ) ዮናስ የጭነት መርከቧ ወደቡን ለቃ ስትሄድ ምን ተስፋ አድርጎ ሊሆን ይችላል? (ለ) መርከቧም ሆነች የመርከቧ ሠራተኞች ምን አደገኛ ሁኔታ ገጠማቸው?

10 ዮናስ መርከቧ ውስጥ ገብቶ ተደላድሎ ሲቀመጥ በዓይነ ሕሊናችን ይታየን ይሆናል፤ ይህች መርከብ የፊንቄያውያን የጭነት መርከብ ሳትሆን አትቀርም። የመርከቧ አዛዥና ሠራተኞች መርከቧን አስነስተው ወደቡን ለቀው ለመሄድ ሲሯሯጡ ዮናስ በአንክሮ ይመለከት ጀመር። የባሕሩ ዳርቻ ቀስ በቀስ እየራቀና ከዓይን እየጠፋ ሲሄድ ዮናስ በጣም ሲያስጨንቀው ከነበረው አደገኛ ሁኔታ እንዳመለጠ ሆኖ ሳይሰማው አልቀረም። ሆኖም ድንገት የአየሩ ሁኔታ መቀያየር ጀመረ።

11 ባሕሩ እጅግ አስፈሪ በሆነ ዐውሎ ነፋስ መናወጥ የጀመረ ሲሆን የተነሳው ማዕበል በአሁኑ ጊዜ ያሉ መርከቦችን እንኳ ሊያሰምጥ የሚችል ነበር። በማዕበል በሚናወጠው በዚያ ሰፊ ባሕር ላይ ኢምንት ሆና የምትታየው ይህች ከእንጨት የተሠራች መርከብ ይህን አደገኛ ሁኔታ ምን ያህል ተቋቁማ መቆየት ትችል ይሆን? ዮናስ ከጊዜ በኋላ እንደጻፈው ይሖዋ ‘በባሕሩ ላይ ታላቅ ነፋስን እንደላከ’ በወቅቱ ተረድቶ ነበር? ይህን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ይሁንና መርከበኞቹ ወደየአማልክታቸው መጮኽ ሲጀምሩ ተመልክቷል፤ እነዚህ የሐሰት አማልክት ደግሞ ምንም ሊረዷቸው እንደማይችሉ ያውቃል። (ዘሌ. 19:4) ዘገባው ‘መርከቢቱ ልትሰበር ተቃረበች’ በማለት ይገልጻል። (ዮናስ 1:4) ሆኖም ዮናስ ከአምላክ እየሸሸ ሳለ እንዴት ወደ እሱ ሊጸልይ ይችላል?

12. (ሀ) ዮናስ ማዕበሉ እያናወጣቸው ባለበት ሰዓት መተኛቱ ግዴለሽ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለን ለመፍረድ መቸኮል የሌለብን ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ለ) ይሖዋ የችግሩ መንስኤ ማን መሆኑን ለይቶ ያሳወቀው እንዴት ነው?

12 ምንም ነገር ማድረግ እንደማይችል የተሰማው ዮናስ ወደ ታችኛው የመርከቧ ክፍል ሄዶ ተኛ። ከዚያም ጭልጥ ያለ እንቅልፍ ወሰደው። * የመርከቧም አዛዥ ሄዶ ዮናስን ከተኛበት ከቀሰቀሰው በኋላ እንደ ሌሎቹ ሰዎች ሁሉ እሱም አምላኩን እንዲማጸን ነገረው። መርከበኞቹ ይህን ኃይለኛ ማዕበል ያመጣባቸው አንድ መለኮታዊ ኃይል እንደሆነ ስለተሰማቸው ከተሳፋሪዎቹ መካከል ለዚህ ችግር የዳረጋቸውን ሰው ለማወቅ ሲሉ ዕጣ ተጣጣሉ። ዕጣው አንድ በአንድ ሲወጣና ሌሎቹ ሰዎች ሁሉ ጥፋተኞች አለመሆናቸው እየታወቀ ሲሄድ ዮናስ ልቡ በፍርሃት ሳይቀልጥ አይቀርም። ብዙም ሳይቆይ እውነታው ገሃድ ወጣ። ማዕበሉ እንዲነሳም ሆነ ዕጣው በዮናስ ላይ እንዲወጣ ያደረገው ይሖዋ ነበር!—ዮናስ 1:5-7ን አንብብ።

13. (ሀ) ዮናስ ለመርከበኞቹ ምን ተናዘዘ? (ለ) ዮናስ መርከበኞቹ ምን እንዲያደርጉ ነገራቸው? ለምንስ?

13 ዮናስ ለመርከበኞቹ ሁሉንም ነገር ግልጽልጽ አድርጎ ነገራቸው። ሁሉን ቻይ የሆነው የይሖዋ አምላክ አገልጋይ መሆኑን ገለጸላቸው። ለዚህ ሁሉ ችግር የተዳረጉት ዮናስ ከዚህ አምላክ በመሸሹና እሱን በማስቆጣቱ እንደሆነ ነገራቸው። ሰዎቹ ይህን ሲሰሙ በጣም ደነገጡ፤ ዮናስ ሰዎቹ ምን ያህል እንደተሸበሩ ከፊታቸው ላይ ማንበብ ይችል ነበር። መርከቧንም ሆነ የራሳቸውን ሕይወት ለማዳን በእሱ ላይ ምን ቢያደርጉበት እንደሚሻል ጠየቁት። ዮናስ ምን ምላሽ ሰጣቸው? እየተናወጠ ባለው በዚያ ቀዝቃዛ ባሕር ውስጥ ሲሰምጥ ታይቶት ልቡ በፍርሃት ሳይርድ አልቀረም። ይሁን እንጂ ሊያድናቸው እንደሚችል እያወቀ እነዚህ ሁሉ ሰዎች ሲያልቁ እንዴት አስችሎት ዝም ይላል? ስለሆነም “ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንደ መጣባችሁ ዐውቃለሁ፤ አንሥታችሁ ወደ ባሕሩ ጣሉኝ፤ ባሕሩም ጸጥ ይላል” አላቸው።—ዮናስ 1:12

14, 15. (ሀ) ዮናስ ጠንካራ እምነት በማሳየት ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) መርከበኞቹ ዮናስ ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?

14 ፈሪ የሆነ ሰው እንዲህ ሊናገር ይችላል? በፍጹም። በዚህ በጣም አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ ዮናስ እንዲህ ያለ ድፍረትና የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ማሳየቱ ይሖዋን በእጅጉ አስደስቶት መሆን አለበት። እዚህ ላይ ዮናስ ምን ያህል ጠንካራ እምነት እንደነበረው በግልጽ ማየት እንችላለን። እኛም በዛሬው ጊዜ ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት ዮናስ የተወውን ምሳሌ መከተል እንችላለን። (ዮሐ. 13:34, 35) አንድ ሰው ቁሳዊ፣ ስሜታዊ ወይም መንፈሳዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ስናስተውል እሱን ለመርዳት የተቻለንን ያህል ጥረት እናደርጋለን? እንዲህ ስናደርግ ይሖዋ በጣም ይደሰታል!

15 መርከበኞቹ መጀመሪያ ላይ ዮናስን መጣል አለመፈለጋቸው አዝነውለት እንደነበር ያሳያል። ዳሩ ምን ያደርጋል ማዕበሉን ተቋቁመው ለመጓዝ የተቻላቸውን ያህል ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም። ጭራሽ ነፋሱና ማዕበሉ እያየለ ሄደ። በመጨረሻም ዮናስን ወደ ባሕሩ ከመጣል ሌላ ምንም አማራጭ እንደሌላቸው ተገነዘቡ። የዮናስ አምላክ የሆነው ይሖዋ ምሕረት እንዲያደርግላቸው በመማጸን ዮናስን አንስተው ወደ ባሕሩ ወረወሩት።—ዮናስ 1:13-15

ዮናስ መርከበኞቹ ወደ ባሕሩ እንዲጥሉት ስለጠየቃቸው አንስተው ጣሉት

ዮናስ ምሕረት አግኝቶ ከሞት ተረፈ

16, 17. ዮናስ ወደ ባሕሩ ከተጣለ በኋላ ምን ነገሮች እንዳጋጠሙት ግለጽ። (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

16 ዮናስ እየተናወጠ ያለው ባሕር ውስጥ ገባ። ውኃው ላይ ለመንሳፈፍ የተቻለውን ያህል ጥረት እያደረገ ሳለ መርከቧ ባሕሩን እየሰነጠቀች ወደፊት ስትጓዝ ተመልክቶ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ኃይለኛው ማዕበል ወደ ታች ደፈቀው። ከዚያም ቁልቁል እየሰመጠ ሲሄድ እንዳበቃለት ሳይሰማው አይቀርም።

17 ቆየት ብሎ ዮናስ በዚያን ወቅት ምን ተሰምቶት እንደነበር ገልጿል። በአእምሮው ውስጥ ብዙ ሐሳብ ይመላለስ ነበር። በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የይሖዋን ውብ ቤተ መቅደስ ዳግመኛ እንደማያይ በማሰብ በሐዘን ተዋጠ። የተራሮች መሠረት ወደሚገኝበት ወደ ባሕሩ የታችኛው ወለል እንደሰመጠ ተገነዘበ፤ በዚያም የባሕር ዕፅዋት ተብትበው ያዙት። ሁኔታው ሲታይ እዚያው ተቀብሮ የሚቀር ይመስል ነበር።—ዮናስ 2:2-6ን አንብብ።

18, 19. ዮናስ ባሕሩ ውስጥ ከሰመጠ በኋላ ምን አጋጠመው? ምን ዓይነት ፍጡርስ ዋጠው? ይህ እንዲሆን ያደረገውስ ማን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

18 ይህ በእንዲህ እንዳለ በአቅራቢያው አንድ ጠቆር ያለና በጣም ግዙፍ የሆነ ሕይወት ያለው ነገር ሲንቀሳቀስ ተመለከተ። ይህም ፍጡር እየተምዘገዘገ ወደ እሱ መጣ። ከዚያም አንድ ትልቅ አፍ ተከፍቶ ዋጠው!

ይሖዋ “ዮናስን የሚውጥ ትልቅ ዓሣ አዘጋጀ”

19 በዚህ ጊዜ ዮናስ ‘በቃ፣ አበቃልኝ’ ብሎ አስቦ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ምንም አለመሆኑ ሳያስገርመው አልቀረም። አሁንም በሕይወት አለ! በሰውነቱ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰም፤ ሌላው ቀርቶ አየር አጥቶ እንኳ አልታፈነም። መቃብር ውስጥ የገባ ቢሆንም በሕይወት አለ። ይህም በአድናቆት እንዲዋጥ አደረገው። “ዮናስን የሚውጥ ትልቅ ዓሣ” ያዘጋጀው አምላኩ ይሖዋ እንደሆነ ጥርጥር የለውም። *ዮናስ 1:17

20. ዮናስ በትልቅ ዓሣ ውስጥ ሆኖ ካቀረበው ጸሎት ምን ልንማር እንችላለን?

20 ደቂቃዎች አልፈው በሰዓታት ተተኩ። ዮናስ አይቶት በማያውቀው ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሆኖ የተለያዩ ነገሮችን ሲያውጠነጥን ከቆየ በኋላ ወደ ይሖዋ አምላክ ጸለየ። በዮናስ መጽሐፍ ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ጸሎቱ ብዙ የሚገልጸው ነገር አለ። ዮናስ በተደጋጋሚ ጊዜ ከመዝሙር መጽሐፍ መጥቀሱ ጥልቅ የሆነ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት እንደነበረው ያሳያል። በተጨማሪም ግሩም ባሕርይ እንዳለው ይኸውም አመስጋኝ እንደነበር ይጠቁማል። ዮናስ “እኔ ግን በምስጋና መዝሙር፣ መሥዋዕት እሠዋልሃለሁ፤ የተሳልሁትንም እሰጣለሁ፤ ድነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” በማለት ጸሎቱን ደምድሟል።—ዮናስ 2:9

21. ዮናስ አምላክ ስለሚያድንበት መንገድ ምን ትምህርት አገኘ? እኛስ የትኛውን ሐቅ መዘንጋት የለብንም?

21 ዮናስ “በዓሣው ሆድ ውስጥ” ሆኖ ይሖዋ ማንኛውንም ሰው በየትኛውም ጊዜና ቦታ ማዳን እንደሚችል መማር ችሏል። ይሖዋ እዚያ ውስጥ የነበረውን አገልጋዩን እንኳ አድኖታል። (ዮናስ 1:17) የአንድን ሰው ሕይወት በዓሣ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀንና ለሦስት ሌሊት ጠብቆ ማቆየት የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። እንግዲያው ‘ሕይወታችን በአምላክ እጅ’ እንደሆነ ማስታወሳችን በጣም አስፈላጊ ነው። (ዳን. 5:23) ሕይወትም ሆነ እስትንፋስ የሰጠን እሱ ነው። ታዲያ ለዚህ ነገር አመስጋኞች ነን? ይሖዋን ልንታዘዘውስ አይገባም?

22, 23. (ሀ) ዮናስ ምን ያህል አመስጋኝ እንደነበር የሚፈትን ምን ሁኔታ አጋጠመው? (ለ) ስህተት በምንሠራበት ጊዜ ከዮናስ ምን ትምህርት እናገኛለን?

22 ስለ ዮናስስ ምን ማለት ይቻላል? ይሖዋን በመታዘዝ አመስጋኝነቱን በተግባር አሳይቷል? አዎ፣ አሳይቷል። ከሦስት ቀንና ከሦስት ሌሊት በኋላ ዓሣው ዮናስን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ወስዶ “በደረቅ ምድር ላይ ተፋው።” (ዮናስ 2:10) እስቲ አስበው፣ ይህ ሁሉ ከሆነም በኋላ ዮናስ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ለመድረስ ትንሽ እንኳ መዋኘት አላስፈለገውም! እርግጥ ነው፣ ዓሣው የተፋው የትም ይሁን የት ከባሕሩ ዳርቻ ተነስቶ መጓዝ ነበረበት። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ምን ያህል አመስጋኝ እንደሆነ የሚፈተንበት ሁኔታ ተፈጠረ። ዮናስ 3:1, 2 እንዲህ ይላል፦ “የእግዚአብሔርም ቃል ለሁለተኛ ጊዜ እንዲህ ሲል ወደ ዮናስ መጣ፤ ‘ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ሄደህ የምነግርህን መልእክት ስበክላት።’” ታዲያ ዮናስ ምን ያደርግ ይሆን?

23 በዚህ ጊዜ ዮናስ አላቅማማም። ዘገባው “ዮናስም የእግዚአብሔርን ቃል ታዘዘ፤ ወደ ነነዌም ሄደ” ይላል። (ዮናስ 3:3) በእርግጥም ዮናስ ታዟል። ከሠራው ስህተት እንደተማረ በግልጽ መረዳት ይቻላል። በዚህም ረገድ ቢሆን ዮናስ የተወውን የእምነት ምሳሌ መከተል ይኖርብናል። ሁላችንም ኃጢአት እንሠራለን፤ ሁላችንም እንሳሳታለን። (ሮም 3:23) ይሁን እንጂ ተስፋ ቆርጠን ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርገን እንተወዋለን? ወይስ ከስህተታችን ተምረን አምላክን ለመታዘዝ ጥረት እናደርጋለን?

24, 25. (ሀ) ዮናስ በሕይወት ሳለ ምን ወሮታ አግኝቷል? (ለ) ወደፊት ምን በረከት ይጠብቀዋል?

24 ይሖዋ፣ ዮናስ ላሳየው ታዛዥነት ወሮታ ከፍሎታል? እንዴታ! አንደኛ ነገር፣ ዮናስ ከጊዜ በኋላ እነዚያ መርከበኞች መትረፋቸውን ሳይሰማ አይቀርም። ዮናስ ከራሱ ይልቅ እነሱን ለማዳን ሲል እርምጃ ሲወስድ ማዕበሉ ወዲያውኑ ቆመ፤ በዚህ ጊዜ መርከበኞቹ “እግዚአብሔርን እጅግ ፈሩ፤” እንዲሁም ለሐሰት አማልክታቸው ሳይሆን ለይሖዋ መሥዋዕት አቀረቡ።—ዮናስ 1:15, 16

25 ከጊዜ በኋላ ደግሞ ከዚህ በላቀ መንገድ ተክሷል። ኢየሱስ፣ ዮናስ በትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ያሳለፈው ጊዜ እሱ በመቃብር ወይም በሲኦል ውስጥ ለሚያሳልፈው ጊዜ ትንቢታዊ ጥላ እንደሆነ ገልጿል። (ማቴዎስ 12:38-40ን አንብብ።) ዮናስ ትንሣኤ አግኝቶ በምድር ላይ በሚኖርበት ጊዜ እንዲህ ያለ በረከት ማግኘቱን ሲያውቅ ምንኛ ይደሰት ይሆን! (ዮሐ. 5:28, 29) ይሖዋ አንተንም መባረክ ይፈልጋል። ታዲያ አንተም እንደ ዮናስ ከስህተትህ ለመማር እንዲሁም ታዛዥ ለመሆንና የራስህን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ነህ?

^ አን.4 ዮናስ የተወለደው በገሊላ በምትገኝ ከተማ ውስጥ መሆኑ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፤ ምክንያቱም ፈሪሳውያን በአንድ ወቅት ስለ ኢየሱስ ሲናገሩ በእብሪተኝነት መንፈስ “ከገሊላ አንድም ነቢይ እንደማይነሳ መርምረህ ተረዳ” ብለው ነበር። (ዮሐ. 7:52) በርካታ ተርጓሚዎችና ተመራማሪዎች እንደገለጹት ፈሪሳውያን ዝቅ ተደርጋ ከምትታየው ከገሊላ ነቢይ ተነስቶ አያውቅም፣ ወደፊትም አይነሳም የሚል ጭፍን አመለካከት ነበራቸው። ይህ እውነት ከሆነ ፈሪሳውያን ታሪክንም ሆነ ትንቢትን ወደ ጎን ገሸሽ አድርገው ነበር ማለት ነው።—ኢሳ. 9:1, 2

^ አን.12 የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም፣ ዮናስ በተኛበት ወቅት ያንኮራፋ እንደነበር በመግለጽ ምን ያህል ጭልጥ ያለ እንቅልፍ እንደወሰደው ይጠቁማል። ይሁንና ዮናስ መተኛቱ ግዴለሽ እንደነበር የሚያሳይ ምልክት ነው ብለን መደምደም የለብንም፤ ከዚህ ይልቅ አንዳንዶች ስሜታቸው በጣም በሚደቆስበት ጊዜ በእንቅልፍ ሊሸነፉ እንደሚችሉ ማስታወስ ይኖርብናል። ኢየሱስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ በጣም ተጨንቆ በነበረበት ወቅት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ “ከሐዘን የተነሳ ሲያንቀላፉ” ነበር።—ሉቃስ 22:45

^ አን.19 “ዓሣ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል በግሪክኛ “አስፈሪ የባሕር እንስሳ” ወይም “ግዙፍ ዓሣ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ይህ ፍጡር ምን ዓይነት የባሕር እንስሳ እንደሆነ በትክክል ማወቅ ባይቻልም በሜድትራንያን ባሕር ውስጥ ሰውን ሙሉ በሙሉ መዋጥ የሚችሉ ሻርኮች እንዳሉ ማስተዋል ተችሏል። በሌሎች ቦታዎች ከእነዚህ በጣም የሚበልጡ ሻርኮች ይገኛሉ፤ ዌል ሻርክ የተባለው የዓሣ ዝርያ 15 ሜትር ወይም ከዚያ የሚበልጥ ርዝማኔ ሊኖረው ይችላል!