በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ ምክር

ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ ምክር

በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙን አንዳንዶቹ ችግሮች ቶሎ መፍትሔ የማይገኝላቸውና ለዓመታት የሚዘልቁ ናቸው፤ ችግሩ መኖሩን እንኳ ሳናስተውለው ሥር ሊሰድ ይችላል። ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን በቀላሉ የማይወገዱ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችለን ምክር ይሰጠናል? እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

ከልክ ያለፈ ጭንቀት

ሮዚ እንዲህ ብላለች፦ “ክፉ ክፉውን እያሰብኩና ገና ያልተከሰቱ መጥፎ ነገሮችን በአእምሮዬ እየሳልኩ ከመጠን በላይ የምጨነቅባቸው ጊዜያት ነበሩ።” ታዲያ ሮዚን የረዷት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ናቸው? አንዱ ማቴዎስ 6:34 ሲሆን ጥቅሱ “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት። እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው” ይላል። ሮዚ፣ ኢየሱስ የተናገረው ይህ ሐሳብ ስለ ነገ መጨነቋን እንድታቆም እንደረዳት ገልጻለች። አክላም “አሁን የሚያስጨንቁኝ ብዙ ችግሮች እያሉ፣ ገና ስላልተፈጸሙና ምናልባትም ላይፈጸሙ ስለሚችሉ ነገሮች እያሰብኩ መጨነቄ ተገቢ እንዳልሆነ ተገንዝቤያለሁ” ብላለች።

ያስሚንም ብዙ ጊዜ በጭንቀት ትዋጥ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ከጭንቀቴ ብዛት ስቅስቅ ብዬ የማለቅስባቸው ቀናት ነበሩ፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር ይነጋል። ወደ አእምሮዬ የሚመጡት አሉታዊ ሐሳቦች ሕይወቴን እየተቆጣጠሩት እንደሆነ ይሰማኝ ነበር።” ይህን ችግር ለመፍታት የረዳት የትኛው ጥቅስ ነው? በ1 ጴጥሮስ 5:7 ላይ የሚገኘው “የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ [በአምላክ] ላይ ጣሉ” የሚለው ሐሳብ እንደጠቀማት ትናገራለች። ያስሚን እንዲህ ብላለች፦ “ወደ ይሖዋ አዘውትሬ መጸለዬን የቀጠልኩ ሲሆን እሱም ለጸሎቴ መልስ ሰጥቶኛል። በመሆኑም ከትከሻዬ ላይ ከባድ ሸክም የወረደልኝ ያህል ሆኖ ተሰምቶኛል። አልፎ አልፎ አሉታዊ ሐሳቦች ወደ አእምሮዬ የሚመጡ ቢሆንም አሁን ምን ማድረግ እንዳለብኝ አውቃለሁ።”

ዛሬ ነገ የማለት ልማድ

ኢዛቤላ የምትባል አንዲት ወጣት እንዲህ ትላለች፦ “ዛሬ ነገ ማለት በዘር የሚወረስ ነገር ይመስለኛል፤ ምክንያቱም አባቴም ይኸው ችግር አለበት። ዘና ለማለት ወይም ቴሌቪዥን ለመመልከት ስል ብቻ አስፈላጊ ነገሮችን ለሌላ ጊዜ አስተላልፋለሁ። ዛሬ ነገ ማለት ጎጂ ልማድ ነው፤ በራሳችን ላይ ውጥረት የሚጨምር ከመሆኑም ሌላ ጥራት የጎደለው ሥራ እንድንሠራ ያደርገናል።” ኢዛቤላን የረዳት በ2 ጢሞቴዎስ 2:15 ላይ የሚገኘው መመሪያ ነው፤ ጥቅሱ “ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚገባውና ምንም የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ አድርገህ ራስህን በአምላክ ፊት ለማቅረብ የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ” ይላል። ኢዛቤላ “ዛሬ ነገ በማለቴ የተነሳ ይሖዋ በሥራዬ እንዲያፍር አልፈለግሁም” ብላለች። ይህች ወጣት በአሁኑ ወቅት ትልቅ ለውጥ አድርጋለች።

በተመሳሳይም ኬልሲ እንዲህ ብላለች፦ “በተወሰነ ጊዜ መጠናቀቅ ያለበት ሥራ ይኖረኝና እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ሳስተላልፈው እቆያለሁ። በኋላ ላይ አለቅሳለሁ፣ እንቅልፍ አጣለሁ እንዲሁም እጨነቃለሁ። ይህ ልማድ እየጎዳኝ ነበር።” ኬልሲን የረዳት በምሳሌ 13:16 ላይ የሚገኘው “ብልህ ሰው ተግባሩን በእውቀት ያከናውናል፤ ሞኝ ሰው ግን የገዛ ራሱን ሞኝነት ይገልጣል” የሚለው ሐሳብ ነው። በዚህ ጥቅስ ላይ በማሰላሰሏ ምን ትምህርት እንዳገኘች ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “አስተዋይ መሆንና አስቀድሞ እቅድ ማውጣት ብልህነት ነው። አሁን፣ ማከናወን ያሉብኝን ነገሮች ፕሮግራም የማሰፍርበት ማስታወሻ ደብተር ጠረጴዛዬ ላይ አስቀምጣለሁ፤ ይህም ባለቀ ሰዓት ከመሯሯጥ ይልቅ ሥራዎቼን በፕሮግራም እንዳከናውን ረድቶኛል።”

ብቸኝነት

ኪርስተን “ባለቤቴ እኔንና አራት ትናንሽ ልጆቻችንን ጥሎን ሄደ” ብላለች። ኪርስተንን የረዳት የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ነው? ምሳሌ 17:17 “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው” ይላል። ይህ ጥቅስ ኪርስተን እንደ እሷ ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎችን እርዳታ እንድትጠይቅ አነሳሳት። ይህን ማድረጓ እንዴት እንደጠቀማት ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ጓደኞቼ እኔን ለመርዳት ተረባረቡ! አንዳንድ ጊዜ የምግብ ሸቀጣ ሸቀጦችን እንዲሁም አበባ ደጃፌ ላይ ተቀምጦ አገኝ ነበር። ሦስት ጊዜ ቤት ስንቀይር ወዳጆቼ ተሰባስበው በመምጣት እኔንና ልጆቼን አግዘውናል። አንድ ሰው ደግሞ ሥራ እንዳገኝ ረዳኝ። ጓደኞቼ ምንጊዜም ከጎኔ አልተለዩም።”

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ዴልፊንም በተመሳሳይ ከብቸኝነት ስሜት ጋር ትታገል ነበር። ዴልፊን ያሏትን ነገሮች ሁሉ ባጣችበት ጊዜ ምን እንደተሰማት ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “ሌሎች ሰዎች አስደሳች ሕይወት ሲመሩ እኔ ግን ከሩቅ ሆኜ ከመታዘብ ውጪ ምንም ማድረግ እንደማልችል ይሰማኝ ነበር። በብቸኝነት ስሜት ተውጬ ነበር።” ዴልፊንን ከረዷት ጥቅሶች አንዱ መዝሙር 68:6 ሲሆን ጥቅሱ “አምላክ ብቸኛ ለሆኑ ሰዎች መኖሪያ ቤት ይሰጣቸዋል” ይላል። እንዲህ በማለት ትናገራለች፦ “ጥቅሱ የሚናገረው በአሁኑ ወቅት ቃል በቃል ቤት ስለማግኘት ብቻ አይደለም። አምላክ በመንፈሳዊ ሁኔታ ቤት እንደሚሰጠን ተገንዝቤያለሁ፤ በሌላ አባባል እሱን ከሚወዱ ሰዎች ጋር እውነተኛ ወዳጅነት መመሥረትና መቀራረብ እንዲሁም ተረጋግተን መኖር እንድንችል ያደርገናል። ከሌሎች ጋር ለመቀራረብ ግን መጀመሪያ ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረብ እንዳለብኝ አስተዋልኩ። በዚህ ረገድ ደግሞ መዝሙር 37:4 ጠቅሞኛል፤ ጥቅሱ ‘በይሖዋ ሐሴት አድርግ፤ እሱም የልብህን መሻት ይሰጥሃል’ ይላል።”

ዴልፊን እንዲህ ብላለች፦ “ከይሖዋ ጋር ያለኝን ዝምድና ይበልጥ ማጠናከር እንዳለብኝ ገባኝ። ይሖዋ ተወዳዳሪ የሌለው ወዳጅ ነው። ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ለመቀራረብ እንድችል ደግሞ ከእነሱ ጋር ሆኜ ማድረግ የምችላቸውን ነገሮች በዝርዝር ጻፍኩ። በተጨማሪም በሌሎች መልካም ጎን ላይ ማተኮርንና ስህተቶቻቸውን ችላ ብዬ ማለፍን ተማርኩ።”

እርግጥ ነው፣ አምላክን የሚያገለግሉ ጓደኞችም ቢሆኑ ፍጹማን አይደሉም። የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ማንኛውም ሰው ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ይሁን እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኙት ሥልጠና በተቻለ መጠን ሌሎችን እንዲረዱ ያነሳሳቸዋል። እንዲህ ዓይነት ጓደኞች ማፍራት ብልህነት ነው። ሆኖም በዛሬው ጊዜ መፍትሔ የሌላቸው ችግሮች ሊደርሱብን ለምሳሌ ከባድ የጤና እክል ሊያጋጥመን አሊያም የምንወደውን ሰው በሞት ልናጣ እንችላለን፤ ታዲያ በዚህ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ሊረዱን ይችላሉ?

የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሥራ ላይ ማዋል ጥሩ ወዳጆች ለማግኘት ያስችልሃል