በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 24

ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የሚጻረርን ማንኛውንም የተሳሳተ ሐሳብ አፍርሱ!

ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የሚጻረርን ማንኛውንም የተሳሳተ ሐሳብ አፍርሱ!

“ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የሚጻረሩ የተሳሳቱ ሐሳቦችንና ይህን እውቀት የሚያግድን ማንኛውንም ከፍ ያለ ነገር እናፈርሳለን።”—2 ቆሮ. 10:5

መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን

የትምህርቱ ዓላማ *

1. ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ ለተቀቡ ክርስቲያኖች ምን ማሳሰቢያ ሰጥቷል?

“አትፍቀዱ።” ይህን ማሳሰቢያ የሰጠው ሐዋርያው ጳውሎስ ነው። ጳውሎስ “ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ” ብሏል። (ሮም 12:2) ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የተናገረው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች ነው። ይሁን እንጂ ራሳቸውን ለአምላክ ለወሰኑና በመንፈስ ቅዱስ ለተቀቡ ወንዶችና ሴቶች እንዲህ ያለ ጠንካራ ማሳሰቢያ መስጠት ያስፈለገው ለምንድን ነው?—ሮም 1:7

2-3. ሰይጣን እኛን ከይሖዋ ለማራቅ የሚጥረው እንዴት ነው? እንደ “ምሽግ” ጠንካራ የሆኑና ሥር የሰደዱ አስተሳሰቦችን ለማስወገድ የሚረዳን ምንድን ነው?

2 አንዳንድ ክርስቲያኖች የሰይጣን ዓለም በሚያስፋፋቸው የተሳሳቱ ሐሳቦችና ፍልስፍናዎች እየተማረኩ የነበረ ይመስላል፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ጳውሎስን አሳስቦት ነበር። (ኤፌ. 4:17-19) ማናችንም ብንሆን እንዲህ ባለው ተጽዕኖ ልንሸነፍ እንችላለን። የዚህ ሥርዓት አምላክ የሆነው ሰይጣን እኛን ከይሖዋ ለማራቅ የሚጠቀምባቸው የተለያዩ ዘዴዎች አሉ። ለምሳሌ፣ ከፍ ያለ ቦታ ወይም እውቅና የማግኘት ፍላጎት ካለን በዚህ ይጠቀማል። በሌላ በኩል ደግሞ ያሳለፍነው ሕይወት፣ ባሕላችን እንዲሁም የቀሰምነው ትምህርት በእኛ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ በመጠቀም አስተሳሰባችንን በራሱ መንገድ ለመቅረጽ ይጥራል።

3 ታዲያ እንደ “ምሽግ” ጠንካራ የሆኑና ሥር የሰደዱ አስተሳሰቦችን ከውስጣችን ማስወገድ እንችላለን? (2 ቆሮ. 10:4) ጳውሎስ ምን እንዳለ ልብ እንበል፦ “ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የሚጻረሩ የተሳሳቱ ሐሳቦችንና ይህን እውቀት የሚያግድን ማንኛውንም ከፍ ያለ ነገር እናፈርሳለን፤ እንዲሁም ማንኛውንም ሐሳብ እየማረክን ለክርስቶስ እንዲታዘዝ እናደርጋለን።” (2 ቆሮ. 10:5) በእርግጥም የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን በይሖዋ እርዳታ ከውስጣችን ነቅለን ማውጣት እንችላለን። መርዝን ለማርከስ እንደሚረዳ መድኃኒት ሁሉ የአምላክ ቃልም የሰይጣን ዓለም የሚያሳድረውን እንደ መርዝ ያለ ተጽዕኖ ለማርከስ ያስችለናል።

“አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ”

4. ብዙዎቻችን እውነትን ስንቀበል ምን ዓይነት ለውጥ ማድረግ አስፈልጎናል?

4 መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና እና ይሖዋን ለማገልገል ስትወስን ምን ለውጦች ማድረግ አስፈልጎህ እንደነበረ እስቲ መለስ ብለህ አስብ። ብዙዎቻችን፣ እንፈጽማቸው የነበሩ መጥፎ ድርጊቶችን መተው አስፈልጎናል። (1 ቆሮ. 6:9-11) ይሖዋ እንዲህ ያሉ የኃጢአት ድርጊቶችን እንድንተው ስለረዳን አመስጋኞች ነን!

5. በሮም 12:2 ላይ የተጠቀሱትን የትኞቹን ሁለት እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልገናል?

5 ይሁንና እስካሁን ባደረግነው ለውጥ ረክተን መቀመጥ የለብንም። ከተጠመቅን በኋላ፣ ቀደም ሲል እንፈጽማቸው የነበሩ ከባድ ኃጢአቶችን አንፈጽም ይሆናል፤ ያም ቢሆን ወደ ቀድሞው አኗኗራችን እንድንመለስ ሊፈትኑን የሚችሉ ነገሮችን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለብን። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ “ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ፤ ከዚህ ይልቅ . . . አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ” በማለት መልሱን ይሰጠናል። (ሮም 12:2) ስለዚህ ሁለት እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልገናል። አንደኛ፣ ይህ ዓለም ‘እንዲቀርጸን መፍቀድ’ የለብንም። ሁለተኛ፣ አእምሯችንን በማደስ ‘መለወጥ’ ይኖርብናል።

6. ኢየሱስ በማቴዎስ 12:43-45 ላይ የተናገረው ሐሳብ ምን ትምህርት ይዟል?

6 ጳውሎስ ‘መለወጥ’ ሲል ላይ ላዩን የሚደረግ ለውጥን ብቻ ማመልከቱ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ማንነታችንን ሙሉ በሙሉ የሚቀይር ለውጥን ማመልከቱ ነበር። (“ መለወጥ ወይስ መምሰል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) አእምሯችንን ይኸውም አመለካከታችንን፣ ስሜታችንን እና ውስጣዊ ዝንባሌያችንን ሙሉ በሙሉ መለወጥ ያስፈልገናል። እንግዲያው ሁላችንም እንደሚከተለው ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን፦ ‘ክርስቶስን ለመምሰል ስል የማደርገው ለውጥ እንዲሁ የታይታ ነው? ወይስ ሥር ነቀል ለውጥ እያደረግኩ ነው?’ በሁለቱ መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። ኢየሱስ በማቴዎስ 12:43-45 ላይ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልገን ተናግሯል። (ጥቅሱን አንብብ።) ይህ ጥቅስ አንድ አስፈላጊ ትምህርት ይዞልናል፦ የተሳሳቱ ሐሳቦችን ከአእምሯችን ማስወገድ ብቻውን በቂ አይደለም፤ በምትኩ አእምሯችን አምላክን በሚያስደስቱ ሐሳቦች እንዲሞላ ማድረግ ያስፈልገናል።

“አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ”

7. ውስጣዊ ማንነታችንን መቀየር የምንችለው እንዴት ነው?

7 ዝንባሌያችንን ወይም ውስጣዊ ማንነታችንን መለወጥ የሚቻል ነገር ነው? የአምላክ ቃል ይህን ማድረግ እንደሚቻል ሲገልጽ እንዲህ ይላል፦ “አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ፤ እንዲሁም እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና መልበስ ይኖርባችኋል።” (ኤፌ. 4:23, 24) ስለዚህ ውስጣዊ ማንነታችንን መለወጥ እንችላለን፤ ይህን ማድረግ ቀላል ነው ማለት ግን አይደለም። መጥፎ ምኞቶችን መቆጣጠርና መጥፎ ነገር ከመፈጸም መቆጠብ ብቻውን በቂ አይደለም። ‘አእምሯችንን የሚያሠራውን ኃይል’ መለወጥ ያስፈልገናል። ይህም ምኞታችንን፣ ዝንባሌያችንንና አንድን ነገር ለማድረግ የሚገፋፋንን ስሜት መቀየርን ይጠይቃል። ለዚህ ደግሞ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው።

8-9. የአንድ ወንድም ተሞክሮ ውስጣዊ ማንነታችንን መለወጥ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው?

8 እስቲ የአንድ ወንድምን ምሳሌ እንመልከት፤ ይህ ወንድም ቀደም ሲል ጠበኛ ነበር። ከመጠን በላይ የመጠጣትና የመደባደብ ልማድ ነበረው፤ ይህን ልማዱን ካስተካከለ በኋላ ተጠመቀ፤ ይህም በሚኖርበት ትንሽ ማኅበረሰብ ውስጥ ግሩም ምሥክርነት ለመስጠት አስችሏል። ሆኖም ከተጠመቀ ብዙም ሳይቆይ አንድ ምሽት ላይ ያልጠበቀው ፈተና ገጠመው። አንድ የሰከረ ሰው፣ ወደዚህ ወንድም ቤት መጣና ለጠብ መጋበዝ ጀመረ። መጀመሪያ ላይ ወንድማችን ስሜቱን መቆጣጠር ችሎ ነበር። ሰውየው የይሖዋን ስም መስደብ ሲጀምር ግን በቅርቡ የተጠመቀው ይህ ወንድም ቁጣውን መቆጣጠር አልቻለም። ከቤቱ ወጥቶ ሰውየውን ደበደበው። የዚህ ወንድም ችግር ምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱ የጠበኝነት ዝንባሌውን ለጊዜው ለመቆጣጠር ቢያስችለውም አእምሮውን የሚያሠራው ኃይል ገና አልተለወጠም ነበር። በሌላ አባባል ውስጣዊ ማንነቱ አልተቀየረም ነበር።

9 ሆኖም ይህ ወንድም ተስፋ አልቆረጠም። (ምሳሌ 24:16) ሽማግሌዎች በሚሰጡት እርዳታ እየታገዘ ጥሩ እድገት ማድረጉን ቀጠለ። ውሎ አድሮም የጉባኤ ሽማግሌ መሆን ቻለ። አንድ ምሽት ላይ፣ ከዓመታት በፊት የገጠመው ዓይነት ፈተና አጋጠመው። የስብሰባ አዳራሹ ደጅ ላይ አንድ ሰካራም ከጉባኤ ሽማግሌዎች አንዱን ለመማታት ሲጋበዝ አገኘው። ታዲያ ወንድማችን ምን አደረገ? ሰክሮ የሚንገዳገደውን ሰው በትሕትናና በሰከነ መንፈስ በማነጋገር ሁኔታው እንዲረጋጋ ካደረገ በኋላ ወደ ቤቱ ሸኘው። ወንድማችን እንዲህ እንዲያደርግ የረዳው ምንድን ነው? አእምሮውን የሚያሠራውን ኃይል መለወጥ መቻሉ ነው። ውስጣዊ ማንነቱ ተለውጦ ሰላማዊና ትሑት ሰው መሆን ችሏል፤ ይህ ደግሞ ለይሖዋ ውዳሴ አምጥቷል!

10. ውስጣዊ ማንነታችንን ለመለወጥ ምን ያስፈልጋል?

10 እንደዚህ ያሉ ለውጦች የሚመጡት በአንድ ጀምበር ወይም ያለምንም ጥረት አይደለም። ለዓመታት “ልባዊ ጥረት” ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። (2 ጴጥ. 1:5) በእውነት ውስጥ ረዘም ያለ ጊዜ መቆየታችን ብቻውን ለውጥ ለማድረግ አያስችለንም። ውስጣዊ ማንነታችንን ለመቀየር የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይኖርብናል። እንዲህ ያለ ለውጥ ለማድረግ የሚረዱን መሠረታዊ ነገሮች አሉ። እስቲ አንዳንዶቹን እንመርምር።

አእምሯችንን የሚያሠራውን ኃይል መለወጥ የምንችለው እንዴት ነው?

11. ጸሎት አእምሯችንን የሚያሠራውን ኃይል ለመለወጥ የሚረዳን እንዴት ነው?

11 ጸሎት የመጀመሪያው አስፈላጊ እርምጃ ነው። እኛም እንደ መዝሙራዊው “አምላክ ሆይ፣ ንጹሕ ልብ ፍጠርልኝ፤ በውስጤም ጽኑ የሆነ አዲስ መንፈስ አኑር” ብለን መጸለይ ያስፈልገናል። (መዝ. 51:10) አእምሯችንን የሚያሠራው ኃይል መለወጥ እንዳለበት አምነን መቀበልና ይሖዋ በዚህ ረገድ እንዲረዳን መለመን ይኖርብናል። ይሖዋ ለውጥ ለማድረግ እንደሚረዳን እርግጠኞች እንድንሆን የሚያደርገን ምንድን ነው? ይሖዋ በሕዝቅኤል ዘመን የነበሩትን ልበ ደንዳና እስራኤላውያን በተመለከተ የገባው ቃል፣ እኛንም እንደሚረዳን ለመተማመን ያስችለናል፤ ይሖዋ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ያልተከፋፈለ ልብ እሰጣቸዋለሁ፤ በውስጣቸውም አዲስ መንፈስ አኖራለሁ፤ . . . የሥጋ ልብ [ለአምላክ አመራር ፈጣን ምላሽ የሚሰጥን ልብ ያመለክታል] እሰጣቸዋለሁ።” (ሕዝ. 11:19 ግርጌ) ይሖዋ እነዚያን እስራኤላውያን ለመርዳት ፈቃደኛ ነበር፤ እኛንም ሊረዳን ፈቃደኛ ነው።

12-13. (ሀ) መዝሙር 119:59 እንደሚጠቁመው በምን ላይ ማሰላሰል አለብን? (ለ) ራስህን ምን እያልክ መጠየቅ ይኖርብሃል?

12 ማሰላሰል ሁለተኛው አስፈላጊ እርምጃ ነው። በየቀኑ የአምላክን ቃል ስናነብ፣ ለውጥ ልናደርግባቸው የሚገቡ አስተሳሰቦችና ስሜቶች የትኞቹ እንደሆኑ ጊዜ ወስደን ማሰላሰል ወይም በጥሞና ማሰብ አለብን። (መዝሙር 119:59ን አንብብ፤ ዕብ. 4:12፤ ያዕ. 1:25) ዓለማዊ ፍልስፍናዎች በአስተሳሰባችንና በስሜታችን ላይ ተጽዕኖ አሳድረው እንደሆነ ለማወቅ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ያሉብንን ድክመቶች በሐቀኝነት አምነን መቀበልና ማስተካከያ ለማድረግ በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል።

13 እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በትንሹም ቢሆን በሌሎች የመቅናት ወይም የምቀኝነት ዝንባሌ አለኝ?’ (1 ጴጥ. 2:1) ‘በአስተዳደጌ፣ በትምህርት ደረጃዬ ወይም በሀብቴ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እኩራራለሁ?’ (ምሳሌ 16:5) ‘እኔ ያሉኝ ነገሮች የሌሏቸውን ወይም ከእኔ የተለየ ዘር ያላቸውን ሰዎች ዝቅ አድርጌ እመለከታለሁ?’ (ያዕ. 2:2-4) ‘የሰይጣን ዓለም የሚያቀርባቸው ነገሮች ይማርኩኛል?’ (1 ዮሐ. 2:15-17) ‘የሥነ ምግባር ብልግና እና ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸው መዝናኛዎች ያስደስቱኛል?’ (መዝ. 97:10፤ 101:3፤ አሞጽ 5:15) ራስህን ለመመርመር ለሚያስችሉት ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ፣ ለውጥ ማድረግ ያለብህ በየትኞቹ አቅጣጫዎች እንደሆነ ይጠቁምሃል። እንደ “ምሽግ” ጠንካራ የሆኑና ሥር የሰደዱ አስተሳሰቦችን ከልባችን ስናስወግድ በሰማይ ያለውን አባታችንን እናስደስታለን።—መዝ. 19:14

14. ጥሩ ጓደኞች መምረጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

14 ጥሩ ጓደኞች መምረጥ ሦስተኛው አስፈላጊ እርምጃ ነው። ለእኛ ባይታወቀንም እንኳ ጓደኞቻችን ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል። (ምሳሌ 13:20) በሥራ ቦታም ሆነ በትምህርት ቤት የምናገኛቸው ብዙዎቹ ሰዎች የአምላክ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖረን የሚረዱን አይደሉም። በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ ግን ከሁሉ የተሻሉ ጓደኞች እናገኛለን። “ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች” የምንነቃቃው ወይም የምንነሳሳው በስብሰባዎቻችን ላይ ስንገኝ ነው።—ዕብ. 10:24, 25 ግርጌ

“በእምነት ጸንታችሁ” ኑሩ

15-16. ሰይጣን አስተሳሰባችንን ለመቀየር የሚሞክረው እንዴት ነው?

15 ሰይጣን አስተሳሰባችንን ለመቀየር ቆርጦ እንደተነሳ አንዘንጋ። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው እውነት የሚያሳድረውን በጎ ተጽዕኖ ለማፍረስ፣ ስህተት የሆኑ የተለያዩ ሐሳቦችን ይጠቀማል።

16 ሰይጣን በኤደን ገነት ውስጥ ሔዋንን የጠየቃትን ዓይነት ጥያቄ ዛሬም ያቀርባል፤ ሔዋንን “በእርግጥ አምላክ [እንዲህ] ብሏችኋል?” በማለት ጠይቋት ነበር። (ዘፍ. 3:1) በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው በዚህ ዓለም ውስጥም ጥርጣሬ የሚፈጥሩ እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎች ሲነሱ እንሰማለን፦ ‘በእርግጥ አምላክ ግብረ ሰዶማዊነትን ያወግዛል? በእርግጥ አምላክ ገናን እና ልደትን እንዳታከብሩ ይከለክላል? በእርግጥ አምላካችሁ ደም እንዳትወስዱ ያዛል? በእርግጥ አፍቃሪ የሆነ አምላክ ከተወገዱ ቤተሰቦቻችሁና ጓደኞቻችሁ ጋር እንዳትቀራረቡ ይጠብቅባችኋል?’

17. የምናምንባቸው ነገሮች ትክክል ስለመሆናቸው ጥያቄ ቢፈጠርብን ምን ማድረግ አለብን? በቆላስይስ 2:6, 7 ላይ እንደተገለጸው ይህን ማድረጋችን ምን ጥቅም ያስገኛል?

17 የምናምንባቸው ነገሮች ትክክል ስለመሆናቸው ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ልንሆን ይገባል። ስለምናምንባቸው ነገሮች ለሚፈጠሩብን ጥያቄዎች መልስ ካላገኘን በውስጣችን ጥርጣሬ ሊያቆጠቁጥ ይችላል። እንዲህ ያለው ጥርጣሬ ደግሞ ውሎ አድሮ አስተሳሰባችንን ሊያዛባውና እምነታችንን ሊያጠፋው ይችላል። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብናል? የአምላክ ቃል “ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ” መርምረን ማረጋገጥ እንድንችል አእምሯችንን በማደስ እንድንለውጠው ይመክረናል። (ሮም 12:2) የአምላክን ቃል አዘውትረን በማጥናት፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርናቸውን እውነቶች መርምረን ማረጋገጥ እንችላለን። በተጨማሪም የይሖዋ መሥፈርቶች ትክክል መሆናቸውን እርግጠኞች እንሆናለን። ይህም ጠንካራ ሥር እንዳለው ዛፍ ሥር ሰድደን እና ‘በእምነት ጸንተን ለመኖር’ ያስችለናል።ቆላስይስ 2:6, 7ን አንብብ።

18. የሰይጣን ዓለም የሚያሳድረውን እንደ መርዝ ያለ ተጽዕኖ ማርከስ እንድንችል ምን ይረዳናል?

18 በእምነት ጸንታችሁ ለመኖር የሚያስፈልገውን እርምጃ መውሰድ ያለባችሁ እናንተው ራሳችሁ ናችሁ። ስለዚህ አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ። አዘውትራችሁ ጸልዩ፤ የአምላክን መንፈስ እርዳታ ለማግኘት ይሖዋን ለምኑ። በጥልቀት አሰላስሉ፤ አስተሳሰባችሁንና ዝንባሌያችሁን ሁልጊዜ መርምሩ። ጥሩ ጓደኞች ምረጡ፤ አስተሳሰባችሁን ለመለወጥ የሚረዱ ወዳጆች ይኑሯችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ፣ የሰይጣን ዓለም የሚያሳድረውን እንደ መርዝ ያለ ተጽዕኖ ማርከስ እንዲሁም “ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት የሚጻረሩ የተሳሳቱ ሐሳቦችንና ይህን እውቀት የሚያግድን ማንኛውንም ከፍ ያለ ነገር” ማፍረስ ትችላላችሁ።—2 ቆሮ. 10:5

መዝሙር 50 ራሴን ለአምላክ ለመወሰን ያቀረብኩት ጸሎት

^ አን.5 ያሳለፍነው ሕይወት፣ ባሕላችን እንዲሁም የቀሰምነው ትምህርት በአስተሳሰባችን ላይ ጥሩ ወይም መጥፎ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም። አንዳንድ የተሳሳቱ አመለካከቶች በውስጣችን ሥር ከመስደዳቸው የተነሳ የማንነታችን ክፍል እንደሆኑ አስተውለን ይሆናል። ይህ ርዕስ፣ እንደነዚህ ያሉ መጥፎ ዝንባሌዎችን እንዴት ማስወገድ እንደምንችል ያብራራል።