በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ ከመና እና ከድርጭት ውጭ ሌላ የሚበሉት ነገር ነበራቸው?

እስራኤላውያን በምድረ በዳ ውስጥ በነበሩባቸው 40 ዓመታት በዋነኝነት የሚበሉት መና ነበር። (ዘፀ. 16:35) ከዚህም ሌላ ይሖዋ ሁለት ጊዜ ድርጭት ሰጥቷቸዋል። (ዘፀ. 16:12, 13፤ ዘኁ. 11:31) ያም ቢሆን እስራኤላውያን የሚያገኟቸው ሌሎች የተወሰኑ የምግብ ዓይነቶችም ነበሩ።

ለምሳሌ ይሖዋ ሕዝቦቹን ምግብና ውኃ ወደሚያገኙበት “የማረፊያ ቦታ” የመራቸው ጊዜ ነበር። (ዘኁ. 10:33) ከእነዚህ ቦታዎች አንዱ “12 የውኃ ምንጮችና 70 የዘንባባ ዛፎች” ያሉበት በኤሊም የሚገኘው የበረሃ ገነት ነበር። እነዚህ የዘንባባ ዛፎች የቴምር ዛፍ ሳይሆኑ አይቀሩም። (ዘፀ. 15:27) ፕላንትስ ኦቭ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “በተለያዩ ቦታዎች የሚበቅለው [የቴምር ዛፍ] በረሃ ውስጥ ዋነኛ የምግብ ምንጭ ነው፤ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ምግብ፣ ዘይትና መጠለያ ይሰጣል።”

እስራኤላውያን፣ በአሁኑ ጊዜ ፌራን ተብሎ የሚጠራው ሰፊ የበረሃ ገነት ጋ ሲደርሱም ቆመው ሊሆን ይችላል፤ ይህ የበረሃ ገነት የፌራን ሸለቆ ክፍል ነው። a ዲስከቨሪንግ ዘ ወርልድ ኦቭ ዘ ባይብል የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው “ይህ ሸለቆ ወይም ደረቅ ወንዝ 130 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን በሲና ከሚገኙት ረጅም፣ ውብና ታዋቂ ሸለቆዎች አንዱ ነው። ሸለቆው ውስጥ ከመነሻው ተነስተን 45 ኪሎ ሜትር ገደማ ከተጓዝን በኋላ 4.8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውንና በቴምር ዛፎች የተሞላውን ውቡን የፌራን የበረሃ ገነት እናገኛለን፤ ይህ ቦታ የሚገኘው ከባሕር ወለል በላይ 610 ሜትር ላይ ነው። በሲና ውስጥ ያለ ኤደን ሊባል ይችላል። በዚያ አካባቢ ካሉት በሺዎች የሚቆጠሩ የቴምር ዛፎች የተነሳ ከጥንት ዘመን አንስቶ ብዙ ሰዎች እዚህ መኖር ጀምረዋል።”

በፌራን የበረሃ ገነት የሚገኙት የቴምር ዛፎች

እስራኤላውያን ከግብፅ ሲወጡ ሊጥ፣ ቡሃቃና ምናልባትም የተወሰነ እህልና ዘይት ይዘው ነበር። እርግጥ እነዚህ ነገሮች ቶሎ እንዳለቁ ጥያቄ የለውም። በተጨማሪም ሕዝቡ “መንጎችና ከብቶች ይኸውም እጅግ ብዙ እንስሳ” ይዘው ወጥተው ነበር። (ዘፀ. 12:34-39) ይሁንና በረሃው ውስጥ ያለው የአየር ሁኔታ አስከፊ ስለሆነ ብዙዎቹ እንስሳት ሞተው መሆን አለበት። አንዳንዶቹን እንስሳት በልተዋቸው ሊሆን ይችላል፤ ሌሎቹን ደግሞ መሥዋዕት አድርገው አቅርበዋቸው ይሆናል፤ ምናልባትም አንዳንዶቹን የሠዉአቸው ለሐሰት አማልክት ሊሆን ይችላል። b (ሥራ 7:39-43) ያም ቢሆን እስራኤላውያን የተወሰኑ እንስሳትን ያረቡ ነበር። ይሖዋ፣ ሕዝቡ እምነት በማጣታቸው ምክንያት “ልጆቻችሁ በምድረ በዳ ለ40 ዓመት እረኞች ይሆናሉ” በማለት የተናገረው ሐሳብ ይህን ያሳያል። (ዘኁ. 14:33) በመሆኑም ከከብቶቻቸው ወተትና ሥጋ አግኝተው ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ምግቡ ሦስት ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን ለ40 ዓመት ያህል ለማኖር የሚበቃ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። c

እንስሳቱ ምግብና ውኃ ያገኙት ከየት ነው? d በወቅቱ በዚያ አካባቢ የነበረው የዝናብም ሆነ የዕፀዋት መጠን ከአሁኑ የበለጠ ሊሆን ይችላል። ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ከ3,500 ዓመታት በፊት በዓረቢያ የነበረው የውኃ መጠን በአሁኑ ጊዜ ካለው የተሻለ ነው። በአንድ ወቅት ወንዝ የነበራቸው በርካታ ጥልቅ ሸለቆዎችና ደረቅ ወንዞች መኖራቸው በጥንት ዘመን የውኃ ጅረት ሊፈጥር የሚችል በቂ ዝናብ እንደነበረ ያረጋግጣል።” ያም ቢሆን ምድረ በዳው ደረቅና አስፈሪ ቦታ ነበር። (ዘዳ. 8:14-16) ይሖዋ በተአምራዊ መንገድ ውኃ ባይሰጣቸው ኖሮ እስራኤላውያኑም ሆነ እንስሶቻቸው ያለጥርጥር ያልቁ ነበር።—ዘፀ. 15:22-25፤ 17:1-6፤ ዘኁ. 20:2, 11

ሙሴ ለእስራኤላውያን እንደነገራቸው፣ ይሖዋ መና የመገባቸው “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ ሊኖር እንደማይችል” ሊያሳውቃቸው ስለፈለገ ነው።—ዘዳ. 8:3

a የግንቦት 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 24-25⁠ን ተመልከት።

b መጽሐፍ ቅዱስ፣ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ውስጥ ለይሖዋ የእንስሳት መሥዋዕት ያቀረቡባቸውን ሁለት አጋጣሚዎች ይጠቅሳል። የመጀመሪያው የክህነት ሥርዓቱ በተቋቋመበት ጊዜ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በፋሲካ በዓል ዕለት ነው። ሁለቱም የተከናወኑት እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ በወጡ በሁለተኛው ዓመት ማለትም በ1512 ዓ.ዓ. ነው።—ዘሌ. 8:14–9:24፤ ዘኁ. 9:1-5

c በ40 ዓመቱ የምድረ በዳ ጉዞ መገባደጃ አካባቢ እስራኤላውያን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳትን በምርኮ ወስደው ነበር። (ዘኁ. 31:32-34) ያም ቢሆን፣ ወደ ተስፋይቱ ምድር እስከገቡበት ጊዜ ድረስ መና መብላታቸውን ቀጥለዋል።—ኢያሱ 5:10-12

d እንስሳት መና ይበሉ እንደነበር የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም፤ ምክንያቱም እስራኤላውያን መና እንዲወስዱ የታዘዙት በሰዎች ቁጥር ልክ ነበር። —ዘፀ. 16:15, 16