በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቴክኖሎጂ የሚያሳድረው ተጽዕኖ—​በትዳርህ ላይ

ቴክኖሎጂ የሚያሳድረው ተጽዕኖ—​በትዳርህ ላይ

ቴክኖሎጂ በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ሲውል ባለትዳሮች ይበልጥ እንዲቀራረቡ ይረዳል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ባልና ሚስት የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን ተጠቅመው በቀን ውስጥ በፈለጉት ሰዓት መነጋገር ይችላሉ።

ይሁንና አንዳንድ ባለትዳሮች ቴክኖሎጂን አላግባብ በመጠቀማቸው ምክንያት የሚከተሉት ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፦

  • አብረው የሚያሳልፉት ጊዜ ያጣሉ።

  • የግድ አስፈላጊ ባይሆንም ሥራቸውን ቤት ይዘው ይመጣሉ።

  • እርስ በርስ ያለመተማመን ችግር ያጋጥማቸዋል፤ አንዳንዶቹም ታማኝነታቸውን ያጎድላሉ።

ማወቅ የሚኖርብህ ነገር

አብራችሁ የምታሳልፉት ጊዜ

ማይክል የተባለ አንድ ባለትዳር እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንድ ጊዜ ከባለቤቴ ጋር በአካል አብረን ብንሆንም በመንፈስ አብራኝ አይደለችም። ስልኳን እየጎረጎረች ‘እስካሁን የተላኩልኝን መልእክቶች የማይበት አጋጣሚ አላገኘሁም’ ትላለች።” ጆናታን የተባለ ባል ደግሞ “እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ሥር ባለትዳሮች በአካል አብረው ቢሆኑም ብዙ ኪሎ ሜትሮች ተራርቀው ያሉ ያህል ነው” በማለት ተናግሯል።

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ከትዳር ጓደኛህ ጋር እየተነጋገርክ ሳለህ በስልክ ጥሪ ወይም በሞባይል መልእክቶች ምክንያት በተደጋጋሚ ውይይታችሁን ለማቋረጥ ትገደዳለህ?—ኤፌሶን 5:33

ሥራ

የአንዳንድ ሰዎች የሥራ ባሕርይ በተፈለጉበት ጊዜ ሁሉ መገኘትን ይጠይቃል። ሌሎች ግን እንዲህ ያለ አስገዳጅ ሁኔታ ባያጋጥማቸውም ከሥራ ሰዓት በኋላ ሥራቸውን ለማቆም ይቸገራሉ። ሊ የተባለ አንድ ባለትዳር እንዲህ ሲል በሐቀኝነት ተናግሯል፦ “ከባለቤቴ ጋር አብሬ ለማሳለፍ በመደብኩት ጊዜ ላይ ከሥራ ጋር የተያያዙ የስልክ ጥሪዎች ወይም መልእክቶች ይደርሱኛል። እነዚህን የስልክ ጥሪዎች ወይም መልእክቶች አለመመለስ ይከብደኛል።” ጆይ የተባለች አንዲት ባለትዳር ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “የምሠራው ከቤት ሆኜ ነው፤ ስለዚህ ሥራዬ ሁሌም አብሮኝ አለ ማለት ይቻላል። በዚህ ረገድ ሚዛናዊ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠይቃል።”

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የትዳር ጓደኛህ ስታነጋግርህ ሙሉ ትኩረት ሰጥተህ ታዳምጣታለህ?—ሉቃስ 8:18

ታማኝነት

አንድ ጥናት እንደጠቆመው በባለትዳሮች መካከል ለሚነሳው ግጭት አንዱ የተለመደው ምክንያት በማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ረገድ አለመተማመን ነው። በጥናቱ ላይ ከተካፈሉት ሰዎች መካከል አሥር በመቶ የሚሆኑት ኢንተርኔት ላይ የለጠፏቸውን አንዳንድ ነገሮች ከትዳር ጓደኛቸው እንደሚደብቁ ተናግረዋል።

በእርግጥም ማኅበራዊ ሚዲያ “ለባለትዳሮች የፈንጂ ቀጠና” ብሎም “ወደ ምንዝር የሚመራ አመቺ መንገድ” ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። ከዚህ አንጻር የፍቺ ጠበቃዎች በዛሬው ጊዜ በባለትዳሮች መካከል ለሚፈጸመው ፍቺ ማኅበራዊ ሚዲያ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት መግለጻቸው አያስገርምም።

ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ከተቃራኒ ፆታ ጋር የምታደርገውን ግንኙነት ከትዳር ጓደኛህ ትደብቃለህ?—ምሳሌ 4:23

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር ለይ

ምግብ በአግባቡ የማይበላ ሰው ጤናማ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም። በተመሳሳይም ከትዳር ጓደኛው ጋር ጊዜ የማያሳልፍ ሰው ጤናማ ትዳር ይዞ ለመቀጠል ይቸገራል።—ኤፌሶን 5:28, 29

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10

ቴክኖሎጂ በትዳርህ ላይ ችግር እንዳይፈጥር ከዚህ በታች ከተጠቀሱት ነጥቦች መካከል የትኞቹን ሥራ ላይ ልታውሉ እንደምትችሉ ከትዳር ጓደኛህ ጋር ተወያዩ፤ ወይም የራሳችሁን ሐሳቦች ጻፉ።

  • በቀን ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ አብሮ መመገብ

  • የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻችንን የማንጠቀምበት ጊዜ መመደብ

  • አብረን ለየት ያሉ ነገሮችን የምናደርግበት ጊዜ መመደብ

  • ማታ ላይ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻችንን መዝጋት ወይም ከመኝታችን ማራቅ

  • በቀን ውስጥ ለ15 ደቂቃ ያህል በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ሳንረበሽ አብረን ማውራት

  • ከኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻችን ላይ የኢንተርኔት አገልግሎትን የምናጠፋበት የተወሰነ ጊዜ መመደብ