በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ደስታ የሚያስገኝ መንገድ

ፍቅር

ፍቅር

የሰው ልጆች ፍቅር የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ፍቅር ከሌለ ትዳር፣ የቤተሰብ ሕይወት ወይም ጓደኝነት ሊሰምር አይችልም። በመሆኑም ፍቅር ለአእምሮ ጤንነትና ለደስታ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው መባሉ ምክንያታዊ ነው። ለመሆኑ “ፍቅር” ሲባል ምን ማለት ነው?

በተቃራኒ ፆታዎች መካከል ያለው ፍቅር አስፈላጊ እንደሆነ አይካድም። ሆኖም እዚህ ላይ የምንወያየው ስለዚህ ዓይነቱ ፍቅር ሳይሆን ለሌሎች ደህንነት ልባዊ አሳቢነት እንድናሳይ አልፎ ተርፎም ሌሎችን ከራሳችን አስበልጠን እንድንመለከት ስለሚያነሳሳን የላቀ የፍቅር ዓይነት ነው። ይህ ዓይነቱ ፍቅር አምላክ ባወጣቸው መሥፈርቶች የሚመራ ቢሆንም ወዳጃዊ ስሜት የማይንጸባረቅበት አይደለም።

የሚከተሉት ቃላት ፍቅርን ግሩም በሆነ መንገድ ይገልጹታል፦ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። ፍቅር አይቀናም። ጉራ አይነዛም፣ አይታበይም፣ ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም፣ የራሱን ፍላጎት አያስቀድምም፣ በቀላሉ አይበሳጭም። ፍቅር የበደል መዝገብ የለውም። ፍቅር በዓመፅ አይደሰትም፤ ከዚህ ይልቅ ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል። ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ . . . ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል። ፍቅር ለዘላለም ይኖራል።”—1 ቆሮንቶስ 13:4-8

እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር፣ የማይኖርበት ጊዜ ስለሌለ “ለዘላለም ይኖራል” ሊባል ይችላል። እንዲያውም በጊዜ ሂደት ይበልጥ እየጠነከረ ይሄዳል። ደግሞም ታጋሽ፣ ደግና ይቅር ባይ ስለሆነ “ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” ነው። (ቆላስይስ 3:14) በመሆኑም ሰዎች ድክመት ቢኖርባቸውም እንኳ እንዲህ ባለው ፍቅር ላይ የተመሠረተ ዝምድና እስካላቸው ድረስ ጠንካራና ደስታ የሰፈነበት ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል። እስቲ የጋብቻ ጥምረትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ።

‘ፍጹም በሆነ የአንድነት ማሰሪያ’ የተሳሰረ ጥምረት

ኢየሱስ ክርስቶስ ትዳርን ስኬታማ ለማድረግ የሚረዱ ጠቃሚ መመሪያዎችን ሰጥቷል። ለምሳሌ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “‘ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ’ . . . ስለዚህ አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።” (ማቴዎስ 19:5, 6) ከዚህ ጥቅስ ላይ ቢያንስ ሁለት ጠቃሚ መመሪያዎችን ማግኘት እንችላለን።

“ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” በሰዎች መካከል ሊኖር ከሚችለው ጥምረት ሁሉ በጣም ጥብቅ የሆነው የጋብቻ ጥምረት ነው፤ ፍቅር ደግሞ ይህን ጥምረት ከአደጋ ይጠብቀዋል። ምክንያቱም ባልም ሆነ ሚስት ፍቅር ካላቸው ታማኝነታቸውን ከማጉደል ማለትም የትዳር ጓደኛቸው ካልሆነ ሰው ጋር “አንድ አካል” ከመሆን ይርቃሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:16፤ ዕብራውያን 13:4) ለትዳር ጓደኛ ታማኝ አለመሆን መተማመንን የሚያጠፋ ከመሆኑም በላይ ትዳሩን ሊያፈርሰው ይችላል። ልጆች ካሉ ደግሞ ከፍተኛ የስሜት ቀውስ ሊደርስባቸው፣ እንደማይወደዱ ሊሰማቸው ብሎም ፍርሃትና ምሬት ሊያድርባቸው ይችላል።

“አምላክ ያጣመረው።” ጋብቻ ቅዱስ ጥምረት ነው። ይህን ሐቅ የሚገነዘቡ ባልና ሚስት ትዳራቸውን ለማጠናከር ጥረት ያደርጋሉ። በትዳራቸው ውስጥ ችግር ሲያጋጥማቸው ትዳሩን የሚያፈርሱበት ሰበብ አይፈላልጉም። በመካከላቸው ያለው ፍቅር ጠንካራና ችግሮችን ተቋቁሞ ማለፍ የሚችል ነው። እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር “ሁሉን ችሎ [ስለሚያልፍ]” ባለትዳሮች የሚያጋጥማቸውን ችግር በመፍታት ሰላምና አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ ይረዳቸዋል።

ወላጆች በፍቅር ተነሳስተው አንዳቸው የሌላውን ጥቅም የሚያስቀድሙ ከሆነ ልጆቻቸው በእጅጉ ይጠቀማሉ። ጄሲካ የምትባል አንዲት ወጣት ስለ ወላጆቿ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “አባቴና እናቴ በጣም የሚዋደዱና የሚከባበሩ ሰዎች ናቸው። እናቴ በተለይ ከእኛ ከልጆች ጋር በተያያዘ ለአባቴ የምታሳየውን አክብሮት ስመለከት እኔም እንደ እሷ ለመሆን እመኛለሁ።”

ፍቅር የአምላክ ዋነኛ ባሕርይ ነው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐንስ 4:8) ከዚህ አንጻር ይሖዋ “ደስተኛው አምላክ” ተብሎ መጠራቱ አያስገርምም። (1 ጢሞቴዎስ 1:11) እኛም የፈጣሪያችንን ባሕርያት በተለይም ፍቅሩን ለማንጸባረቅ ስንጥር ደስተኞች እንሆናለን። ኤፌሶን 5:1, 2 “የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ፤ . . . በፍቅር መመላለሳችሁን ቀጥሉ” ይላል።