በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንደ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ሁሉ ጠንክሮ መሥራትም ለአሁኑም ሆነ ለወደፊት ሕይወትህ ይጠቅምሃል

ለወጣቶች

11፦ ታታሪ መሆን

11፦ ታታሪ መሆን

ምን ማለት ነው?

ታታሪ ሰዎች ከሥራ አይሸሹም። ከዚህ ይልቅ የሚሠሩት ሥራ በሌሎች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዓይነት ባይሆን እንኳ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላትና ሌሎችን ለመርዳት ስለሚያስችላቸው ሥራቸውን በትጋት ያከናውናሉ።

አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ወደድንም ጠላን፣ ሁላችንም ልንወጣቸው የሚገቡ በርካታ ኃላፊነቶች አሉብን። ጠንክሮ መሥራት የማይፈልጉ ሰዎች በሞሉበት በዚህ ዓለም ታታሪ ሠራተኛ መሆንህ ይጠቅምሃል።—መክብብ 3:13

“ጠንክሮ መሥራት ለራሳችን ያለን አክብሮት እንዲጨምርና ውስጣዊ እርካታ እንድናገኝ እንደሚያደርግ መገንዘብ ችያለሁ። ይህ ደግሞ ሥራዬን ይበልጥ እንድወደው አድርጎኛል። ጥሩ የሥራ ልማድ ማዳበር መልካም ስም ለማትረፍም ይረዳናል።”—ሬየን

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በትጋት ያከናወኑት ነገር ሁሉ ጥቅም ያስገኛል።”—ምሳሌ 14:23

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ቀጥሎ የተገለጹትን ምክሮች ተግባራዊ በማድረግ ለሥራ አዎንታዊ አመለካከት አዳብር።

ሥራህን በሚገባ ለማከናወን ጥረት አድርግ። ቤት ውስጥ የታዘዝከውን ሥራም ሆነ ከትምህርት ቤት የተሰጠህን የቤት ሥራ ወይም ተቀጥረህ የምትሠራውን ሥራ ስታከናውን ከልብህ ለመሥራት ጥረት አድርግ። አንድን ሥራ ጥሩ አድርገህ ስለሠራኸው ብቻ ረክተህ አትቀመጥ፤ ከዚህ ይልቅ ከአሁኑ በተሻለ ፍጥነትና ጥራት መሥራት የምትችልበትን መንገድ ፈልግ። በሥራው ይበልጥ እየተካንክ ስትሄድ ሥራውን ይበልጥ እየወደድከው ትሄዳለህ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በሥራው የተካነን ሰው አይተሃል? በነገሥታት ፊት ይቆማል፤ ተራ በሆኑ ሰዎች ፊት አይቆምም።”—ምሳሌ 22:29

ሥራህ ሌሎችንም እንደሚጠቅም አስብ። ምንጊዜም ቢሆን ኃላፊነትህን በጥሩ ሁኔታ ስትወጣ ሌሎች ሰዎች መጠቀማቸው አይቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ ቤት ውስጥ የተሰጡህን ሥራዎች በትጋት ከሠራህ ለቤተሰብህ አባላት ሸክም ታቀልላቸዋለህ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

ከሚጠበቅብህ በላይ ሥራ። የታዘዝከውን ብቻ ከመሥራት ይልቅ ከሚጠበቅብህ በላይ ለመሥራት ጥረት አድርግ። አንድን ነገር ሌሎች ስላዘዙህ ሳይሆን በራስህ ተነሳስተህ በማከናወን ራስህን ማዘዝ እንደምትችል ማሳየት ትችላለህ።—ማቴዎስ 5:41

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የምታደርገው መልካም ነገር በራስህ ፈቃድ እንጂ በግዴታ እንዳይሆን አንተ ሳትስማማ ምንም ነገር ማድረግ አልፈልግም።”—ፊልሞና 14

ሚዛናዊ ሁን። ታታሪ ሰዎች ሰነፍ አይደሉም ሲባል የሥራ ሱሰኞች ይሆናሉ ማለት አይደለም። ለሥራቸውም ሆነ ለመዝናኛ ተገቢውን ቦታ በመስጠት ከሁለቱም ደስታ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ።

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል።”—መክብብ 4:6