በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

3ኛው ቁልፍ​—ዘወትር እንቅስቃሴ አድርግ

3ኛው ቁልፍ​—ዘወትር እንቅስቃሴ አድርግ

3ኛው ቁልፍ​—ዘወትር እንቅስቃሴ አድርግ

“የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ክኒን ቢሆን ኖሮ በዓለም ላይ ሐኪሞች ለታካሚዎቻቸው በብዛት የሚያዙት መድኃኒት ይሆን ነበር።” (ኤሞሪ የሕክምና ዩኒቨርሲቲ) ለጤንነታችን ልናደርግ ከምንችላቸው ነገሮች ሁሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማድረግን ያህል ጠቀሜታ ያላቸው ነገሮች ቢኖሩ በጣም ጥቂት ናቸው።

◯ የሰውነት እንቅስቃሴ አድርግ። እንቅስቃሴ የተሞላበት ሕይወት መምራት ይበልጥ ደስተኞች እንድንሆን፣ አጥርተን እንድናስብ፣ የበለጠ ጉልበት እንዲኖረን፣ በሥራችን ይበልጥ ፍሬያማ እንድንሆንና ተገቢ አመጋገብ ሲታከልበት ደግሞ ክብደታችንን እንድንቆጣጠር ይረዳናል። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን የሚያሳምም ወይም ከመጠን ያለፈ መሆን አያስፈልገውም። በሳምንት ውስጥ በተወሰኑ ቀናት አዘውትሮ መጠነኛ የሰውነት እንቅስቃሴ ለማድረግ ጊዜ መመደብ በጣም ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ልብህ በፍጥነት እስኪመታና እስኪያልብህ ድረስ ሶምሶማ መሮጥህ፣ ፈጠን ፈጠን እያልክ መራመድህ፣ ብስክሌት መንዳትህ እንዲሁም በሌሎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች መካፈልህ ይበልጥ ጽናት እንድታዳብር ብሎም በልብ በሽታና በአንጎል ውስጥ ደም በመፍሰስ ችግር እንዳትጠቃ ሊረዳህ ይችላል። እንዲህ ያለውን የኤሮቢክስ ስፖርት መጠነኛ ከሆነ የክብደት ማንሳትና ከጂምናስቲክ ስፖርቶች ጋር አጣምረህ መሥራትህ አጥንቶችህ፣ ጡንቻዎችህ ብሎም እጅና እግሮችህ እንዲጠነክሩ ይረዳሃል። በተጨማሪም ምግብ በሰውነት ውስጥ በቀላሉ እንዲንሸራሸር ያስችላል፤ ይህ ደግሞ ክብደትን ለመቆጣጠር ይረዳል።

◯ በእግርህ ሂድ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በሁሉም ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ሰዎች ጠቃሚ ሲሆን ይህን ለማድረግ የግድ የአንድ ጂምናዚየም አባል መሆን አያስፈልግም። መኪና፣ አውቶቡስ ወይም ሊፍት ከመጠቀም ይልቅ በእግር መሄድህ ጥሩ ጅምር ሊሆንልህ ይችላል። ወደምትሄድበት ቦታ በእግርህ መጓዝ ስትችል ለምን መኪና ትጠብቃለህ? ምናልባትም ፈጥነህ ትደርስ ይሆናል። ወላጆች፣ ልጆቻችሁ የሰውነት እንቅስቃሴ የሚጠይቁ ጨዋታዎችን ከተቻለ ከቤት ውጭ እንዲጫወቱ አበረታቷቸው። እንዲህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ እንደ ቪዲዮ ጌሞች ያሉ ተቀምጠው ከሚጫወቷቸው ጨዋታዎች በተለየ አካላቸውን የሚያጠነክርላቸው ሲሆን ሰውነታቸው ቀልጣፋ እንዲሆንም ይረዳቸዋል።

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የምትጀምርበት ዕድሜ ምንም ይሁን ምን መጠነኛ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ልትጠቀም ትችላለህ። በዕድሜ ከገፋህ ወይም የጤና ችግር ካለብህ እንዲሁም የሰውነት እንቅስቃሴ አድርገህ የማታውቅ ከሆነ እንቅስቃሴውን እንዴት ብትጀምር እንደሚሻል ሐኪም ማማከርህ ብልህነት ነው። ዋናው ነገር መጀመርህ ነውና ጀምር! ቀስ በቀስ እየጨመረ የሚሄድና በልኩ የሚደረግ የሰውነት እንቅስቃሴ በዕድሜ የገፉትንም እንኳ የጡንቻና የአጥንት ጥንካሬያቸውን ለመጠበቅ ሊረዳቸው ይችላል። በተጨማሪም አረጋውያን የመውደቅ አደጋ እንዳያጋጥማቸው ሊረዳቸው ይችላል።

በዚህ መጽሔት የመጀመሪያ ርዕስ ላይ የተጠቀሰውን ሩስታምን የረዳው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ነው። ከሰባት ዓመታት በፊት እሱና ሚስቱ በሳምንት ውስጥ አምስቱን ቀን ጧት ጧት መሮጥ ጀመሩ። ሩስታም እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ላይ ስፖርቱን ላለመቀጠል ሰበብ እናቀርብ ነበር። ይሁን እንጂ አብሮን የሚሮጥ ሰው ማግኘታችን እንዳናቋርጥ ረድቶናል። አሁን በጣም የምንደሰትበት ልማድ ሆኗል።”

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አስደሳች ማድረግ ይቻላል