በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ለትኋን ቤት አይለቀቅም!

‘ለትኋን ቤት አይለቀቅም!

ትኋኖችን ለማጥፋት የሚደረገው ትግል በሃያኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ የተሳካ ይመስል ነበር። አንዳንድ ሰዎች ትኋኖችን የሚያውቁት በስም ብቻ ነበር። በ1970ዎቹ ዓመታት ግን ትኋኖችን ለማጥፋት ዋነኛ መሣሪያ የነበረው ዲ ዲ ቲ የተባለ ኬሚካል መርዛማና ሥነ ምሕዳርን የሚጎዳ በመሆኑ ብዙ አገሮች ይህ ኬሚካል ጥቅም ላይ እንዳይውል ወሰኑ።

ሌሎች የተባይ ማጥፊያ ኬሚካሎች የነበሩ ቢሆንም እያደር ግን በእነዚህ ኬሚካሎች ተጠቅሞ ትኋኖችን ማጥፋት አዳጋች እየሆነ መጣ። በተጨማሪም ሰዎች ከበፊቱ ይበልጥ ከቦታ ወደ ቦታ ስለሚጓጓዙ ሳይታወቃቸው ትኋኖችን በየቦታው እንዲሰራጩ አደረጉ። በመሆኑም ስለ ትኋን ቁጥጥር በ2012 የወጣ አንድ ዘገባ እንደገለጸው “ባለፉት 12 ዓመታት ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በካናዳ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በአያሌ የአውሮፓ አገሮች፣ በአውስትራሊያና በአንዳንድ የአፍሪካ ክፍሎች ትኋኖች እንደገና መታየት እንደጀመሩ ሪፖርት ተደርጓል።”

በሞስኮ፣ ሩሲያ ትኋኖች እንደተገኙ የሚገልጹ ሪፖርቶች በቅርቡ በአንድ ዓመት ውስጥ በአሥር እጥፍ ጨምረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በሌላኛው ጫፍ በምትገኘው በአውስትራሊያ ከ1999 ወዲህ ባሉት ዓመታት ትኋን እንዳገኙ ሪፖርት ያደረጉ ሰዎች ቁጥር 5,000 በመቶ ጨምሯል!

አንዳንድ ሰዎች ወደ ሱቆች፣ ትያትር ቤቶች ወይም ሆቴሎች ሲሄዱ ሳይታወቃቸው ትኋኖችን ይዘው ይመለሳሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ አንድ የሆቴል አስተዳዳሪ፣ ወደ ሆቴሉ የሚመጡ ሰዎች ቢፈተሹ “ትኋኖች መገኘታቸው አይቀርም” በማለት ተናግሯል። ይኸው አስተዳዳሪ አክሎም “አሁን አሁን በዚህ ሥራ ላይ እስካለን ድረስ ከትኋኖች ጋር መታገል የግድ ነው” ብሏል። ትኋኖችን ማጥፋት ይህን ያህል አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው? ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? ቤትህ ውስጥ ትኋን ካገኘህ እነሱን ለማጥፋትና እንዳይመለሱ ለማድረግ ምን እርምጃዎች መውሰድ ትችላለህ?

አልሞት ባይ ተጋዳይ ጥቃቅን ፍጥረታት

እድገቱን የጨረሰ ትኋን ርዝመቱ 5 ሚሊ ሜትር ገደማ ይሆናል

ትኋኖች ከድፍን ምስር ብዙም የማይበልጡና ጠፍጣፋ ሰውነት ያላቸው በመሆናቸው የትም ቦታ መደበቅ ይችላሉ። በፍራሽ፣ በቤት ዕቃዎች፣ በኤሌክትሪክ ሶኬቶች አልፎ ተርፎም በስልክ ውስጥ ጭምር ሊኖሩ ይችላሉ። ትኋኖች ብዙውን ጊዜ የሚኖሩት ከአልጋዎችና ከመቀመጫዎች ከ3 እስከ 6 ሜትር ባለው ርቀት ላይ ነው። ለምን? ምግብ ወደሚያገኙበት ቦታ ይኸውም ወደ ሰዎች ለመቅረብ ነው። *

ትኋኖች ብዙውን ጊዜ የሰዎችን ደም የሚመጡት ሰዎቹ ሲተኙ ነው። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ሰዎች ትኋን ሲነክሳቸው አይታወቃቸውም፤ ምክንያቱም ለ10 ደቂቃ ያህል ያለማቋረጥ የሰዎቹን ደም መምጠጥ እንዲችሉ ትኋኖቹ የሚያደነዝዝ ነገር ይረጩባቸዋል። ትኋኖች የሚመገቡት በሳምንት አንድ ጊዜ ቢሆንም ለብዙ ወራት ምንም ሳይመገቡ መኖር እንደሚችሉ ታውቋል።

እርግጥ ነው፣ ከወባ ትንኞችና ከአንዳንድ ነፍሳት በተለየ መልኩ ትኋኖች በሽታ አያሰራጩም። ይሁን እንጂ ሰውነታችን ላይ ትኋን የነከሰን ቦታ ሊያሳክከንና ሊያብጥ ይችላል፤ ከዚህም ሌላ ብዙ ሰዎች በትኋን መነከሳቸው በራሱ ይረብሻቸዋል። ትኋን የነከሳቸው ሰዎች እንቅልፍ ሊያጡና የኃፍረት ስሜት ሊሰማቸው አልፎ ተርፎም ትኋኖቹ ከጠፉ በኋላ እንኳ ትኋን የነከሳቸው ሊመስላቸው ይችላል። ከሴራ ሊዮን የመጣ አንድ ዘገባ ትኋኖችን “ሰላም እና እንቅልፍ የሚነሱ ነገሮች” በማለት የጠራቸው ሲሆን “የትኋን መኖር አሳፋሪ ነገር እንደሆነ ተደርጎ” እንደሚቆጠር ይገልጻል።

ትኋኖች ወደ ቤታችሁ እንዳይገቡ ተጠንቀቁ

ሻንጣችሁን ፈትሹ

ትኋኖች ሁሉንም ሰው ሊያጠቁ ይችላሉ። ሳይባዙ ከተደረሰባቸው ግን በቀላሉ ማጥፋት ይቻላል። ስለዚህ በቤት ውስጥም ሆነ በጉዞ ላይ ስትሆኑ ትኋኖች መኖራቸውን የሚያሳዩ ምልክቶችን ለይታችሁ እወቁ። በቤት ዕቃዎችና በዘኮሎዎች ላይ እንዲሁም በሻንጣ ውስጥ ሰሊጥ የሚያህሉ ጥቃቅን እንቁላሎች እና የደም ጠብታዎች መኖራቸውን ፈትሹ። እነዚህን ነገሮች በደንብ ማየት እንድትችሉ በእጅ ባትሪ ተጠቀሙ።

ክፍተቶችንና ስንጥቆችን ድፈኑ

ትኋኖች አመቺ መደበቂያ እንዳያገኙ አድርጉ። ግድግዳ ላይ እንዲሁም የበር መቃንና ጉበን ላይ ያሉ ክፍተቶችንና ስንጥቆችን ድፈኑ። ትኋኖች የሚመጡት በንጽሕና ጉድለት ባይሆንም ቤታችሁን አዘውትራችሁ የምታጸዱና እንዳይዝረከረክ የምትጠነቀቁ ከሆነ ትኋኖች መኖራቸውን በቀላሉ ማወቅና ማጥፋት ይቻላል። ሆቴል ውስጥ በምታርፉበት ጊዜ ትኋኖች ይዛችሁ እንዳትመለሱ ሻንጣችሁን መሬት ላይ ወይም አልጋ ላይ አታስቀምጡ።

ትኋኖች ቤታችሁ ውስጥ ካሉ

አዘውትራችሁ አጽዱ

ቤታችሁ ወይም ያረፋችሁበት ሆቴል ውስጥ ትኋን ብታገኙ ልትረበሹ አልፎ ተርፎም ልትሸማቀቁ ትችላላችሁ። ዴቭና ባለቤቱ ለእረፍት በሄዱበት ወቅት ትኋን ነከሳቸው። ዴቭ “በጣም ተሸማቅቀን ነበር” ብሏል። “ቤት ስንመለስ ለጓደኞቻችንና ለቤተሰቦቻችን ምን እንላለን? ሰውነታቸውን ቢያሳክካቸው ወይም ቆዳቸው ቢቆጣ እኛ ቤት የሆነ ተባይ እንደነከሳቸው ያስቡ ይሆን?” ብለን ተጨነቅን። እንዲህ ቢሰማችሁ የሚገርም ባይሆንም ኃፍረት የሌሎችን እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ እንድትሉ አያድርጋችሁ። በኒው ዮርክ ሲቲ የሚገኘው ኸልዝ ኤንድ ሜንታል ሃይጂን ዲፓርትመንት “ትኋኖችን ማጥፋት ከባድ ቢሆንም ፈጽሞ የማይቻል ነገር ግን አይደለም” ብሏል።

ቤታችሁ ውስጥ ትኋኖች መኖራቸውን ፈትሹ፤ እንዲሁም አመቺ መደበቂያ እንዳያገኙ አስፈላጊ እርምጃ ውሰዱ

ያም ቢሆን ግን ትኋኖችን ማጥፋት ተፈታታኝ እንደሆነ አትዘንጉ። ቤታችሁ ውስጥ ትኋን ካገኛችሁ የተባይ ማጥፊያ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን እርዳታ ጠይቁ። ቀደም ሲል የተጠቀሱት የተባይ ማጥፊያ ኬሚካሎች በአሁኑ ጊዜ ጥቅም ላይ ባይውሉም ባለሙያዎቹ ሌሎች ውጤታማ ዘዴዎችን አቀናጅተው ሊጠቀሙ ይችላሉ። ስለ ነፍሳት የሚያጠኑ ዲኒ ሚለር የተባሉ ተመራማሪ “[የሕንፃው] ኃላፊ እና የተባይ ማጥፊያ ድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ነዋሪዎቹም ትኋኖችን ለማጥፋት እኩል ትብብር ሊያደርጉ ይገባል” ብለዋል። እናንተም የባለሙያዎቹን መመሪያዎች በመከተልና አስፈላጊ የሆኑ ጥንቃቄዎችን በማድረግ የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላላችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ ‘ለትኋን ቤታችሁን አትለቁም!’

^ አን.7 ስለ ነፍሳት የሚያጠኑ ተመራማሪዎች፣ ትኋኖች የቤት እንስሳትን ጨምሮ የሌሎች አጥቢ እንስሳትንና የሰዎችን ደም እንደሚመገቡ ይገልጻሉ።