በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አስደናቂ የምሕንድስና ጥበብ የሚታይባቸው የሮም የውኃ ማስተላለፊያዎች

አስደናቂ የምሕንድስና ጥበብ የሚታይባቸው የሮም የውኃ ማስተላለፊያዎች

በጥንት ዘመን ከተሠሩት አስደናቂ የምሕንድስና ሥራዎች መካከል የሮም የውኃ ማስተላለፊያ መስመሮች ይገኙበታል። ሴክስተስ ዩልየስ ፍራንታይነስ (ከ35 እስከ 103 ዓ.ም. ገደማ) የተባለው አገረ ገዢና የሮም የውኃ አቅርቦት ኃላፊ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ውኃ በብዛት የሚያልፍባቸውን እነዚህን እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የግንባታ ሥራዎች፣ ምንም ጥቅም ሳይኖራቸው እንዲሁ ከቆሙት ፒራሚዶች ወይም ታዋቂ ቢሆኑም ምንም እርባና ከሌላቸው የግሪክ ሕንጻዎች ጋር እስቲ አወዳድሯቸው!” *

የውኃ ማስተላለፊያ መስመሮች ያስፈለጉበት ምክንያት

የጥንት ከተሞች አብዛኛውን ጊዜ የሚቆረቆሩት ውኃ በብዛት በሚገኝበት አካባቢ ነው፤ የሮምም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። መጀመሪያ ላይ ከተማዋ ውኃ የምታገኘው ከታይበር ወንዝ እንዲሁም በአቅራቢያዋ ካሉ ምንጮች እና የውኃ ጉድጓዶች ነበር። ከአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ወዲህ ግን የሮም ነዋሪዎች ቁጥር በፍጥነት ማሻቀብ ጀመረ፤ በዚህ የተነሳ የከተማዋ የውኃ ፍጆታም በዚያው ልክ ጨመረ።

ቤታቸው ድረስ ውኃ የሚመጣላቸው ነዋሪዎች ጥቂት ስለነበሩ ሮማውያን በመቶዎች የሚቆጠሩ የግል እና የሕዝብ መታጠቢያ ቤቶችን ገነቡ። በሮም ከተማ ውስጥ የተገነባው የመጀመሪያው የሕዝብ መታጠቢያ ቤት፣ ውኃ የሚያገኘው አኳ ቪርጎ ከተባለ በ19 ዓ.ዓ. ተሠርቶ ከተጠናቀቀ የውኃ ማስተላለፊያ መስመር ነው። ይህን የውኃ ማስተላለፊያ የገነባው ማርከስ አግሪፓ የተባለው ሀብታም ሰው የአውግስጦስ ቄሳር የቅርብ ወዳጅ ሲሆን ይህ ሰው የሮምን የውኃ ማስተላለፊያ መስመሮች ለማሻሻል እና የውኃ አቅርቦቱን ለማስፋፋት አብዛኛውን ጥሪቱን አፍስሷል።

በተጨማሪም መታጠቢያ ቤቶቹ የሕዝብ መሰብሰቢያ ማዕከል ነበሩ፤ እንዲያውም ትላልቆቹ መታጠቢያ ቤቶች መናፈሻ እና ቤተ መጻሕፍት ነበራቸው። ከመታጠቢያ ቤቶቹ የሚወጣው ውኃ ወደ ቆሻሻ ማስወገጃ ቱቦዎች ይገባል፤ ከዚያም ከመታጠቢያ ቤቶቹ ጋር ከተገነቡት መጸዳጃ ቤቶች የሚወጣውን ቆሻሻ እያጠበ ይሄዳል።

ግንባታ እና ጥገና

“የሮም የውኃ ማስተላለፊያ መስመሮች” ሲባል ቶሎ የሚመጡልህ ብዙ ርቀት በሚሸፍን ቦታ ላይ የተገነቡት ግዙፍ የሆኑ ቅስቶች ናቸው? እንደ እውነቱ ከሆነ፣ እነዚህ ቅስቶች ከአጠቃላዩ የውኃ ማስተላለፊያ መስመር 20 በመቶውን ቢይዙ ነው፤ አብዛኛው የመስመሩ ክፍል የሚገኘው መሬት ውስጥ ነው። ይህ መሆኑ  ወጪ ቆጣቢ ከመሆኑም በላይ ቱቦዎቹ በነፋስ እንዳይሸረሸሩ ይረዳል፤ በተጨማሪም በግንባታው ሳቢያ የእርሻ መሬት ወይም የመኖሪያ ሰፈሮች እንዳይነኩ ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል በ140 ዓ.ዓ. ተሠርቶ የተጠናቀቀው አኳ ማርኪያ የተባለው የውኃ ማስተላለፊያ 92 ኪሎ ሜትር ገደማ ርዝመት ያለው ቢሆንም ቅስቶቹ የተገነቡበት ቦታ በአጠቃላይ 11 ኪሎ ሜትር ቢሸፍን ነው።

መሐንዲሶች አንድ የውኃ ማስተላለፊያ መስመር ለመገንባት ሲያስቡ መጀመሪያ ላይ ሊጠቀሙበት ያሰቡት የውኃ አካል ያለውን ሁኔታ ይገመግማሉ፤ ይህን የሚያደርጉት የውኃውን ንጽሕና፣ የፍሰት መጠኑን እና የውኃውን ጣዕም በመመልከት ነው። በተጨማሪም ከዚህ የውኃ አካል የሚጠጡት የአካባቢው ሰዎች ያላቸውን የጤንነት ሁኔታ ያጣራሉ። ውኃው የሚወሰድበት ቦታ ከተመረጠ በኋላ መሬት የሚቀይሱ ሰዎች ውኃው በየት በኩል ቢያልፍ የተሻለ እንደሆነ ብሎም ምን ያህል እያጋደለ መሄድ እንዳለበት ያሰላሉ፤ እንዲሁም ቱቦው ምን ያህል መጠንና ርዝመት ሊኖረው እንደሚገባ ይወስናሉ። የጉልበት ሥራውን የሚያከናውኑት ባሮች ሳይሆኑ አይቀሩም። አንድን የውኃ ማስተላለፊያ መስመር ገንብቶ ለማጠናቀቅ በተለይ ደግሞ ቅስቶችን መገንባት የሚያስፈልግ ከሆነ በርካታ ዓመታት ሊወስድ ይችላል፤ ይህም ብዙ ወጪ ያስወጣል።

ከዚህም ሌላ የማስተላለፊያ መስመሮቹን መጠገንና መጠበቅ ያስፈልግ ነበር። በአንድ ወቅት ይህንን ሥራ ለማከናወን 700 የሚያህሉ ሰዎች ተቀጥረው ነበር። የውኃ ማስተላለፊያ መስመሮቹ የተሠሩት ለጥገና አመቺ በሆነ መንገድ ነው። ለምሳሌ ያህል በመሬት ውስጥ የሚገኙት ቱቦዎች ጋር ለመድረስ አመቺ እንዲሆን ከላይ ቀዳዳዎች ይሠራሉ። ከፍተኛ ጥገና በሚያስፈልግበት ጊዜ መሐንዲሶቹ ውኃው ለተወሰነ ጊዜ በሌላ አቅጣጫ እንዲሄድ ያደርጋሉ።

በከተማይቱ ውስጥ የነበሩ የውኃ ማስተላለፊያዎች

በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መጀመሪያ አካባቢ በሮም ከተማ ውስጥ 11 ዋና ዋና የውኃ ማስተላለፊያዎች ነበሩ። አኳ አፒያ ተብሎ የሚጠራው የመጀመሪያው የውኃ ማስተላለፊያ ተገንብቶ የተጠናቀቀው በ312 ዓ.ዓ. ነው፤ ከ16 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ይህ ማስተላለፊያ ሙሉ በሙሉ የሚያልፈው በመሬት ውስጥ ነው ማለት ይቻላል። አኳ ክላውዲያ የተባለው የውኃ ማስተላለፊያ ደግሞ 69 ኪሎ ሜትር ገደማ ርዝመት የነበረው ሲሆን የዚህ ማስተላለፊያ የተወሰነ ክፍል አሁንም ድረስ አለ፤ ቅስቶቹ የተገነቡበት ቦታ አጠቃላይ ርዝመት 10 ኪሎ ሜትር ያህል ነው፤ ከቅስቶቹ መካከል ብዙዎቹ 27 ሜትር ከፍታ ነበራቸው!

የከተማይቱ የውኃ ማስተላለፊያዎች ምን ያህል መጠን ያለው ውኃ ማስተላለፍ ይችሉ ነበር? በጣም ብዙ! ለምሳሌ ያህል፣ ቀደም ሲል የተጠቀሰው አኳ ማርኪያ የተባለው የውኃ መስመር በየቀኑ 190 ሚሊዮን ሊትር የሚሆን ውኃ ያስተላልፍ ነበር። ውኃው ከተማይቱ ጋ ሲደርስ ወደ ማጠራቀሚያዎች ይገባና በተለያዩ መስመሮች አማካኝነት ወደ ሌሎች ማጠራቀሚያዎችና የውኃ አቅርቦት ወደሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ይሄዳል፤ ይህ የሚሆነው በስበት ኃይል አማካኝነት ነው። የሮም የውኃ አቅርቦት በጣም እያደገ ከመሄዱ የተነሳ በአንድ ወቅት የከተማዋ ነዋሪዎች በነፍስ ወከፍ ከ1,000 ሊትር የሚበልጥ ውኃ ማግኘት ይችሉ እንደነበር ይገመታል።

የሮማ ግዛት እየተስፋፋ ሲመጣ “የውኃ ማስተላለፊያ ግንባታዎችም የሮማ ግዛት በተስፋፋበት አቅጣጫ ሁሉ መሄድ ጀመሩ” በማለት ሮማን አክዊደክት ኤንድ ዎተር ሰፕላይ የተባለው መጽሐፍ ተናግሯል። በዛሬው ጊዜም እንኳ ሰሜን አፍሪካን፣ ስፔንን፣ ትንሹ እስያን እና ፈረንሳይን የሚጎበኙ ሰዎች በጥንታዊዎቹ የውኃ ማስተላለፊያዎች ላይ በሚታየው አስደናቂ የምሕንድስና ጥበብ እጅግ ይደነቃሉ።

^ አን.2 የውኃ ማስተላለፊያ መስመሮችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሠሩት ሮማውያን አይደሉም። የጥንቶቹ ሕንዶች፣ አሦራውያን፣ ግብፃውያን እና ፋርሳውያን በዚህ ረገድ ይቀድሟቸዋል።