በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ሴቶች አገልጋይ መሆን ይችላሉ?

በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ሴቶች አገልጋይ መሆን ይችላሉ?

አዎን፣ እንዲያውም በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሴት አገልጋዮች አሉ። እነዚህ ሴቶች የአምላክን መንግሥት ምሥራች የሚሰብኩ ታላቅ ሠራዊት ናቸው። በ⁠መዝሙር 68:11 (የ1980 ትርጉም) ላይ የሚገኘው ስለ እነዚህ አገልጋዮች የሚገልጽ ትንቢት “እግዚአብሔር ትእዛዝ ሰጠ፤ ብዙ ሴቶችም ዜናውን አሰራጩ” ይላል።

ይሁንና የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሴት አገልጋዮችና በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉ ሴት የሃይማኖት አስተማሪዎች የሚያከናውኑት ሥራ ተመሳሳይ አይደለም። በሁለቱ መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ። የይሖዋ ምሥክር የሆኑትና በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉት ሴት አገልጋዮች የሚለያዩት በየትኞቹ መንገዶች ነው?

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሁለቱ ቡድኖች የሚያስተምሯቸው ሰዎች የተለያዩ ናቸው። ሴት የሃይማኖት አስተማሪዎች በተለይም በሕዝብ ክርስትና ውስጥ ያሉ ሴት አስተማሪዎች በጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡ ሲሆን በዋነኝነት የሚያስተምሩት የሃይማኖታቸው ተከታይ የሆኑ ሰዎችን ነው። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሴት አገልጋዮች ግን በዋነኝነት የሚያስተምሩት ከጉባኤው ውጭ ማለትም ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ወይም በሌሎች ቦታዎች ሲሰብኩ የሚያገኟቸውን ሌሎች ሰዎች ነው።

የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሴት አገልጋዮች በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ ካሉት ሴት አገልጋዮች የሚለዩበት ሁለተኛው መንገድ ደግሞ በጉባኤ ውስጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው። በሕዝበ ክርስትናና በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ ያሉ ሴት አገልጋዮች ምዕመኖቻቸውን ይመራሉ፤ እንዲሁም የሃይማኖታቸውን ቀኖና ለምዕመኖቻቸው ያስተምራሉ። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሴት አገልጋዮች ግን በጉባኤ ውስጥ የተጠመቀ ወንድ ባለበት አያስተምሩም። በጉባኤ ውስጥ የሚያስተምሩት የተሾሙ ወንዶች ብቻ ናቸው።—1 ጢሞቴዎስ 3:2፤ ያዕቆብ 3:1

መጽሐፍ ቅዱስ ጉባኤውን የመምራት ኃላፊነት የተሰጣቸው፣ ወንዶች ብቻ እንደሆኑ ይናገራል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደ እሱ የበላይ ተመልካች ለሆነው ለቲቶ በጻፈለት ደብዳቤ ላይ የተናገረውን ሐሳብ ልብ በል፦ “አንተን በቀርጤስ የተውኩበት ምክንያት . . . በየከተማው ሽማግሌዎችን እንድትሾም ነው።” አክሎም ጳውሎስ እያንዳንዱ ሽማግሌ ወይም የተሾመ ወንድ “ከክስ ነፃ የሆነ [እንዲሁም] የአንዲት ሚስት ባል” ሊሆን እንደሚገባ ተናግሯል። (ቲቶ 1:5, 6) ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይም እንደሚከተለው በማለት ተመሳሳይ ሐሳብ አስፍሯል፦ “የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር ማንኛውም ሰው መልካም ሥራን ይመኛል። ስለዚህ የበላይ ተመልካች የማይነቀፍ፣ የአንዲት ሚስት ባል፣ . . . ለማስተማር ብቃት ያለው [ሊሆን ይገባል]።”—1 ጢሞቴዎስ 3:1, 2

ጉባኤውን የመምራት ኃላፊነት ለወንዶች ብቻ የተሰጠው ለምንድን ነው? ጳውሎስ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሴት ዝም እንድትል እንጂ እንድታስተምር ወይም በወንድ ላይ ሥልጣን እንዲኖራት አልፈቅድም። ምክንያቱም በመጀመሪያ የተፈጠረው አዳም ነው፤ ከዚያም ሔዋን ተፈጠረች።” (1 ጢሞቴዎስ 2:12, 13) ወንድና ሴት የተፈጠሩበት የጊዜ ቅደም ተከተል በራሱ አምላክ የማስተማርና የመምራት ኃላፊነትን ለወንዶች የሰጠው ለምን እንደሆነ ይጠቁማል።

የይሖዋ አገልጋዮች የመሪያቸውን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ ይከተላሉ። ደቀ መዝሙሩ ሉቃስ ስለ ኢየሱስ አገልግሎት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበከና እያወጀ ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር ይጓዝ ነበር።” ከጊዜ በኋላ፣ የኢየሱስ ተከታዮች እሱ የሰጣቸውን ተመሳሳይ ተልእኮ ለመወጣት ‘ምሥራቹን እየተናገሩ ከመንደር ወደ መንደር በመሄድ ክልሉን አዳርሰዋል።’—ሉቃስ 8:1፤ 9:2-6

በዛሬ ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ኢየሱስ የተናገረውን የሚከተለውን ትንቢት ለመፈጸም በሥራው በቅንዓት እየተካፈሉ ነው፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14