በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

ሁለተኛ ትዳር እንዲሰምር ማድረግ

ሁለተኛ ትዳር እንዲሰምር ማድረግ

ኼርማን፦ * “የመጀመሪያዋ ባለቤቴ በካንሰር ከመሞቷ በፊት በትዳር ውስጥ 34 ዓመታት አሳልፈናል። ከሊንዳ ጋር ከተጋባን በኋላ ሊንዳ ሁልጊዜ ከመጀመሪያዋ ሚስቴ ጋር እንደማወዳድራት ይሰማት ጀመር። ይባስ ብሎ ደግሞ የቀድሞ ጓደኞቼ ስለ ሟቿ ባለቤቴ ግሩም ባሕርያት ብዙ ጊዜ ያወሩ ነበር፤ ይህም ሊንዳን ያስከፋታል።”

ሊንዳ፦ “ከኼርማን ጋር ከተጋባን በኋላ ባለቤቴም ሆነ ሌሎች ሰዎች መቼም ቢሆን የቀድሞ ሚስቱን ያህል እንደማይወዱኝ ይሰማኝ ነበር። የቀድሞ ሚስቱ በጣም ተወዳጅ፣ ደርባባና ጨዋ ሴት ነበረች። ‘ባለቤቴ ከእሷ ጋር የነበረው ዓይነት ቅርርብ በእኔና በእሱ መካከል ሊኖር ይችል ይሆን?’ እያልኩ አንዳንድ ጊዜ አስባለሁ።”

ሊንዳ ከመጀመሪያ ባሏ ጋር በፍቺ ተለያይታለች። ኼርማንም ሆነ ሊንዳ በጋብቻ በመጣመራቸው ደስተኞች ናቸው። ያም ቢሆን በመጀመሪያ ትዳር ወቅት ጨርሶ ያልነበሩ ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሁለተኛ ትዳር ላይ ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ሁለቱም ይስማማሉ። *

ለሁለተኛ ጊዜ ትዳር መሥርተህ ከሆነ ስለ አዲሱ ትዳርህ ምን ይሰማሃል? ከባለቤቷ ጋር ከተፋታች ከሦስት ዓመታት በኋላ እንደገና ትዳር የመሠረተች ታማራ የምትባል አንዲት ሴት እንዲህ ትላለች፦ “ለመጀመሪያ ጊዜ ስታገቡ ትዳራችሁን እንደ ዕድሜ ልክ ጥምረት ስለምታዩት ልዩ ስሜት ይኖራችኋል። ሁለተኛ ትዳር ስትመሠርቱ ግን እንደዚህ ዓይነት ስሜት ላይኖራችሁ ይችላል፤ ምክንያቱም የመጀመሪያው ትዳራችሁ መፍረሱን ማስታወሳችሁ አይቀርም።”

እንደዚያም ሆኖ ሁለተኛ ትዳር የመሠረቱ በርካታ ጥንዶች ዘላቂ የሆነ ደስታ ማግኘት ችለዋል። ትዳራቸው የሰመረ እንዲሆን  በማድረግ ረገድ ተሳክቶላቸዋል፤ ስለዚህ እናንተም ሊሳካላችሁ ይችላል! ግን እንዴት? በሁለተኛ ትዳር ውስጥ የሚያጋጥሙ ሦስት የተለመዱ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እንዴት ሊረዱ እንደሚችሉ እስቲ እንመልከት። *

ተፈታታኝ ሁኔታ 1፦ የቀድሞ ትዳርህ ትዝታ በአሁኑ ትዳርህ ላይ ችግር እንዳይፈጥር የምታደርገው ጥረት

በደቡብ አፍሪካ የምትኖረው ኤለን እንዲህ ብላለች፦ “ከቀድሞ ባለቤቴ ጋር ስላሳለፍነው ጊዜ ያሉኝን ትዝታዎች ጨርሶ ከአእምሮዬ ልሰርዛቸው አልችልም፤ በተለይ ከእሱ ጋር ለእረፍት ወደሄድንባቸው ቦታዎች ከአሁኑ ባሌ ጋር ስንሄድ የድሮ ትዝታዎች ይመጡብኛል። አንዳንድ ጊዜ ሳላስበው የአሁኑን ባለቤቴን ከቀድሞ የትዳር ጓደኛዬ ጋር ማወዳደር እጀምራለሁ።” በሌላ በኩል ደግሞ የትዳር ጓደኛህ ከዚህ በፊት አግብታ ከነበረና ስለ ቀድሞ ባሏ አዘውትራ የምታወራ ከሆነ ቅር ሊልህ ይችላል።

ሁለታችሁን የሚያቀራርቧችሁ ትዝታዎች እንዲኖሯችሁ ለማድረግ ጣሩ

የመፍትሔ ሐሳብ፦ አንተም ሆንክ የትዳር ጓደኛህ የመጀመሪያውን ትዳራችሁን ሙሉ በሙሉ ልትረሱት እንደማትችሉ ተገንዘቡ፤ በተለይ ደግሞ ከቀድሞ የትዳር ጓደኛችሁ ጋር በጋብቻ ብዙ ዓመታት ካሳለፋችሁ ትዝታው በቀላሉ ከአእምሯችሁ ላይጠፋ ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች የአሁኑን የትዳር ጓደኛቸውን ተሳስተው በቀድሞው የትዳር ጓደኛቸው ስም ጠርተው እንደሚያውቁ ተናግረዋል! እንዲህ ያለ ወይም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ቢያጋጥማችሁ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ “የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ” በማለት ይመክራል።—1 ጴጥሮስ 3:8

የትዳር ጓደኛሽ ስለ ቀድሞ ባለቤቱ ሲናገር መቅናትና ስለ እሷ ጨርሶ እንዳያነሳ መከልከል ተገቢ አይደለም። የትዳር ጓደኛሽ ከቀድሞ ባለቤቱ ጋር ስላሳለፈው ሕይወት ማውራት ከፈለገ ስሜቱን እንደምትረጂለት በሚያሳይ መንገድ አዳምጪው። በተጨማሪም ከቀድሞ የትዳር ጓደኛው ጋር እያወዳደረሽ እንደሆነ በማሰብ አትከፊ። ሁለተኛ ትዳሩን ከመሠረተ አሥር ዓመት የሆነው ኢየን እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴ ኬይትሊን ስለ ቀድሞ ባለቤቴ እንዳላነሳ በፍጹም ከልክላኝ አታውቅም። ከዚህ ይልቅ ስለ ቀድሞ ባለቤቴ ማውራቴ ዛሬ ስላለኝ ባሕርይ ይበልጥ ለመረዳት እንደሚያስችላት ይሰማታል።” እንዲያውም እንዲህ ዓይነቱ ጭውውት ከአዲሱ የትዳር ጓደኛሽ ጋር ያለሽን ወዳጅነት ለማጠናከር ሊረዳሽ ይችላል።

የአሁኗ የትዳር ጓደኛህ ባሏት ለየት ያሉ መልካም ባሕርያት ላይ ትኩረት አድርግ። እውነት ነው፣ የአሁኗ ባለቤትህ የቀድሞ የትዳር ጓደኛህ የነበሯት ዓይነት ባሕርያት ወይም ችሎታዎች አይኖሯት ይሆናል። በሌላ በኩል ግን የአሁኗ ባለቤትህ የተሻለች የምትሆንባቸው አቅጣጫዎች ይኖራሉ። ስለዚህ የአሁኗን የትዳር ጓደኛህን ‘ከሌላ ሰው ጋር ከማነጻጸር’ ይልቅ እሷን እንድትወዳት ባደረጉህ ነገሮች ላይ ቆም ብለህ በማሰብና እነዚህን በማድነቅ ትዳርህን ለማጠናከር ጥረት አድርግ። (ገላትያ 6:4) ለሁለተኛ ጊዜ ያገባ ኤድመንድ የሚባል አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ከሁለት የተለያዩ ሰዎች ጋር የምትመሠርቱት ጓደኝነት አንድ እንዳልሆነ ሁሉ የመጀመሪያ ትዳራችሁና ሁለተኛው ትዳራችሁም ተመሳሳይ ሊሆኑ አይችሉም።”

ታዲያ ስለ ቀድሞ ትዳርህ ያሉህ አስደሳች ትዝታዎች አሁን በመሠረትከው ትዳር ውስጥ ችግር እንዳይፈጥሩ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? ጃሬድ እንዲህ ብሏል፦ “የመጀመሪያው ትዳሬ፣ እኔና የቀድሞ ባለቤቴ አንድ ላይ ሆነን እንደጻፍነው ግሩም መጽሐፍ እንደሆነ በአንድ ወቅት ለአሁኗ ባለቤቴ ገለጽኩላት። አልፎ አልፎ ያንን መጽሐፍ እየገለጥኩ ያሳለፍናቸውን አስደሳች ትዝታዎች አነብብ ይሆናል። ይሁን እንጂ የምኖረው በዚያ መጽሐፍ ውስጥ አይደለም። ከዚህ ይልቅ እኔና የአሁኗ ባለቤቴ አንድ ላይ ሆነን የራሳችንን መጽሐፍ እየጻፍን ሲሆን አሁን የምኖረውም በዚህኛው መጽሐፍ ውስጥ ነው፤ በዚህኛው ሕይወቴ ደስተኛ ነኝ።”

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ስለ ቀድሞ ትዳርህ ሲነሳ ቅር ይላት እንደሆነ የአሁኗን ባለቤትህን ጠይቃት። ስለ ቀድሞዋ የትዳር ጓደኛህ ማንሳት ጥሩ የማይሆንባቸውን ጊዜያት ለማስተዋል ሞክር።

ተፈታታኝ ሁኔታ 2፦ አዲሷ የትዳር ጓደኛህ ከማታውቃቸው የቀድሞ ወዳጆችህ ጋር ያለህ ግንኙነት

ከቀድሞ ሚስቱ ጋር ከተፋታ ከስድስት ዓመታት በኋላ ሁለተኛ ትዳር የመሠረተው ካቭየር እንዲህ ብሏል፦ “ከተጋባን በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ባለቤቴ፣ አንዳንዶቹ ጓደኞቼ እያንዳንዱን እርምጃዋን እንደሚከታተሉና እየፈተኗት እንዳሉ ይሰማት ነበር።” ሊዮ የሚባል አንድ ባል ያጋጠመው ሁኔታ ደግሞ የተለየ ነው። “የባለቤቴን የቀድሞ ባል ምን ያህል እንደሚወዱትና እሱ ባለመኖሩ እንደሚያዝኑ እኔው ፊት የሚናገሩ ሰዎች ነበሩ!” ብሏል።

የመፍትሔ ሐሳብ፦ ራስህን በጓደኞችህ ቦታ አድርገህ ለማሰብ ሞክር። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኢየን እንዲህ ብሏል፦ “የቀድሞ ጓደኞች፣ የሚያውቁት ሰው ከሌላ ሰው ጋር ተጣምሮ ማየት በጣም ሊያሳዝናቸውና የማይዋጥ ነገር ሊሆንባቸው እንደሚችል ይሰማኛል።” ስለዚህ ‘ምክንያታዊ ለመሆንና ለሰው ሁሉ ገርነት ለማሳየት’ ጥረት አድርግ። (ቲቶ 3:2) ጓደኞችህ እና የቤተሰብህ አባላት ከሁኔታው ጋር ወዲያውኑ እንዲላመዱ አትጠብቅባቸው። ሁለተኛ ትዳር ስትመሠርት በጓደኞችህ ረገድም ለውጥ ማድረግ  ሊያስፈልግህ ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ካቭየር፣ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እሱና ባለቤቱ ከሁለቱም የቀድሞ ጓደኞች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እንደገና ማጠናከር እንደቻሉ ገልጿል። “ይሁን እንጂ ሁለታችንም የምንቀርባቸው አዳዲስ ጓደኞችን ለማፍራትም ጥረት የምናደርግ ሲሆን ይህም ጠቅሞናል” ብሏል።

ከቀድሞ ጓደኞችህ ጋር ጊዜ ስታሳልፍ የትዳር ጓደኛህን ስሜት ከግምት አስገባ። ለምሳሌ ያህል፣ በጭውውት መሃል ስለ ቀድሞ የትዳር ጓደኛህ ቢነሳ ዘዴኛና አስተዋይ በመሆን የአሁኗ ባለቤትህ ችላ እንደተባለች እንዳይሰማት ለማድረግ ሞክር። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ያለ ጥንቃቄ የተነገረ ቃል እንደ ሰይፍ ያቈስላል፤ በጥበብ የተነገረ ቃል ግን ይፈውሳል” ይላል።—ምሳሌ 12:18 የ1980 ትርጉም

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ ከማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ አንተንም ሆነ የትዳር ጓደኛህን እንድትጨነቁ ሊያደርጓችሁ የሚችሉ ሁኔታዎችን አስቀድማችሁ አስቡ። ጓደኞችህ የሚያነሷቸውን ጥያቄዎችና ስለ ቀድሞ ትዳርህ የሚሰነዝሯቸውን ሐሳቦች በምን መንገድ ብትመልሱ የተሻለ እንደሚሆን ከባለቤትህ ጋር አስቀድማችሁ ተወያዩ።

ተፈታታኝ ሁኔታ 3፦ የቀድሞ የትዳር ጓደኛህ ለአንተ ታማኝ ስላልነበረች አዲሷን ባለቤትህን ማመን ሊከብድህ ይችላል

የመጀመሪያ ሚስቱ ጥላው የሄደችው አንድሩ “‘እንደገና ባገባ አዲሷ ባለቤቴም ብትከዳኝስ’ የሚለው ሐሳብ በጣም ያስፈራኝ ነበር” በማለት ይናገራል። ከጊዜ በኋላ የአሁኗን ሚስቱን ራይሊን አገባ። “‘ለራይሊ እንደ ቀድሞ ባሏ እሆንላት ይሆን?’ የሚለው ነገር ብዙውን ጊዜ ያሳስበኝ ነበር። እንዲያውም እንደማልመጥናት በማሰብ ሌላ ሰው ወድዳ ጥላኝ እንዳትሄድ እጨነቅ ነበር” ብሏል።

የመፍትሔ ሐሳብ፦ የሚያሳስብህን ነገር ለትዳር ጓደኛህ በግልጽ ንገራት። “ምክር ሲጓደልም ዕቅድ ይፋለሳል” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 15:22) አንድሩና ራይሊ መመካከራቸው ወይም የልባቸውን አውጥተው መነጋገራቸው እያደር እንዲተማመኑ ረድቷቸዋል። አንድሩ “ችግሮች ቢያጋጥሙን ፍቺን እንደ አማራጭ መፍትሔ አድርጌ ጨርሶ እንደማላስብ ለራይሊ ነገርኳት” ብሏል፤ “ራይሊም እንደዚሁ እንደምታስብ አረጋገጠችልኝ። በጊዜ ሂደት ሙሉ በሙሉ ላምናት ችያለሁ።”

የአሁኗን የትዳር ጓደኛህን የቀድሞ ባለቤቷ ከድቷት ከሆነ ደግሞ በአንተ እንድትተማመን ለማድረግ የምትችለውን ሁሉ አድርግ። ለምሳሌ ያህል፣ የመጀመሪያ ትዳራቸው በፍቺ የፈረሰው ሚሼልና ሳቢን ከቀድሞ የትዳር ጓደኞቻቸው ጋር የሚገናኙበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ጉዳዩን አንዳቸው ለሌላው ለመንገር ተስማምተዋል። ሳቢን “እንዲህ ለማድረግ መስማማታችን በመካከላችን ጥርጣሬ እንዳይኖርና እንድንተማመን ረድቶናል” ብላለች።—ኤፌሶን 4:25

እንዲህ ለማድረግ ሞክሩ፦ በአካል፣ በስልክ ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት ከተቃራኒ ፆታ ጋር ብቻችሁን የምትገናኙባቸውን አጋጣሚዎች ለመቀነስ ጥረት አድርጉ።

ሁለተኛ ትዳር የመሠረቱ ብዙ ሰዎች ትዳራቸው ሰምሯል፤ የእናንተም ትዳር ሊሰምር ይችላል። ደግሞም ከመጀመሪያው ትዳራችሁ ጋር ሲነጻጸር አሁን ስለ ራሳችሁ የተሻለ እውቀት አላችሁ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው አንድሩ “ከራይሊ ጋር ትዳር በመመሥረቴ ይህ ነው የማይባል ማጽናኛ አግኝቻለሁ” ይላል። “ከተጋባን 13 ዓመታት ያለፉ ሲሆን የጠበቀ ግንኙነት አለን፤ ሁለታችንም ይህን ፈጽሞ ልናጣው አንፈልግም።”

^ አን.3 ስሞቹ ተቀይረዋል።

^ አን.5 የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች እና ትዳራቸው በፍቺ የፈረሰ ሰዎች የሚኖራቸው ስሜት የተለያየ እንደሆነ የታወቀ ነው። በዚህ ርዕስ ሥር የሚገኙት ሐሳቦች ሁለቱም ዓይነት ሁኔታዎች ያጋጠሟቸው ሰዎች ለሁለተኛ ጊዜ የሚመሠርቱት ትዳር የሰመረ እንዲሆን ይረዳሉ። በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ እንደገና ስላገባው ወገን ስንጠቅስ የተጠቀምነው በተባዕታይ ፆታ ቢሆንም ነጥቦቹ ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

^ አን.7 የእንጀራ ልጆችን በማሳደግ ረገድ ስለሚያጋጥሙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለማወቅ፣ በይሖዋ ምሥክሮች በሚዘጋጀው ንቁ! መጽሔት የሚያዝያ 2012 እትም ላይ “የእንጀራ ልጆችን ማሳደግ—ስኬታማ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?” በሚለው ርዕስ ሥር ያሉትን ተከታታይ ርዕሶች ተመልከት።

ራስህን እንዲህ እያልህ ጠይቅ . . .

  • የአሁኗ የትዳር ጓደኛዬ በጣም የማደንቃቸው ምን ልዩ ባሕርያት አሏት?

  • ስለ መጀመሪያው ትዳሬ ከተነሳ ለአሁኗ ባለቤቴ ያለኝን ፍቅር ለማረጋገጥና እንደማከብራት ለማሳየት ምን ማድረግ እችላለሁ?