በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታደርጉት መዋጮ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እንዴት ነው?

የክልል ስብሰባውን በቴሌቪዥንና በሬዲዮ መከታተል

የክልል ስብሰባውን በቴሌቪዥንና በሬዲዮ መከታተል

ነሐሴ 1, 2021

 የ2020 የክልል ስብሰባ ታሪካዊ ነበር፤ የክልል ስብሰባ ተቀርጾ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንተርኔት ሲሰራጭ የመጀመሪያ ጊዜው ነበር! ሆኖም በማላዊና በሞዛምቢክ የሚኖሩ አብዛኞቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የክልል ስብሰባውን የተከታተሉት ያለኢንተርኔት ነበር። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

 የበላይ አካሉ የአስተባባሪዎች ኮሚቴ እና የትምህርት ኮሚቴ በማላዊ እና በሞዛምቢክ የክልል ስብሰባው በቴሌቪዥንና በሬዲዮ እንዲተላለፍ ለየት ያለ ፈቃድ ሰጡ። ለመሆኑ እንዲህ ያለ ዝግጅት ማድረግ ያስፈለገው ለምንድን ነው? በዓለም ላይ የኢንተርኔት ዋጋ ውድ ከሆነባቸው አገሮች አንዷ ማላዊ ናት፤ በመሆኑም ኢንተርኔት መጠቀም የሚችሉት ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። የማላዊ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ዊልያም ቹምቢ ሁኔታውን ሲያብራራ እንዲህ ብሏል፦ “ይህን መንፈሳዊ ምግብ ለወንድሞችና ለእህቶች ማድረስ የምንችልበት ብቸኛ መንገድ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን መጠቀም ነበር።” በዚያው በማላዊ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ የሚያገለግለው ሉካ ሲቤኮ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ፕሮግራሙን በቴሌቪዥንና በሬዲዮ መከታተል ባንችል ኖሮ በቅርንጫፍ ቢሯችን ክልል ውስጥ ከክልል ስብሰባው ጥቅም ማግኘት የሚችሉት ጥቂት ወንድሞች ብቻ ይሆኑ ነበር።” በሞዛምቢክም ኢንተርኔት ማግኘት ቀርቶ ስብሰባውን ለማየት የሚያስችል የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ያላቸው ወንድሞች እንኳ በጣም ጥቂት ናቸው።

የተደረገው ዝግጅት

 በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ የጉባኤ ስብሰባዎችን በአንዳንድ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች አስቀድመን ማሰራጨት ጀምረን ነበር። a ወንድሞቻችን ወደ እነዚህ ጣቢያዎች ሄደው የክልል ስብሰባውን ለማስተላለፍ ተጨማሪ የአየር ሰዓት እንዲሰጧቸው ጠየቁ።

 በማላዊ ያሉ ወንድሞቻችን አንድ ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። ብዙውን ጊዜ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ጣቢያዎች ለደንበኞቻቸው ከአንድ ሰዓት በላይ የአየር ሰዓት አይሰጡም። ምክንያቱም ፕሮግራሙ ከረዘመ አድማጮች ሊሰላቹ እንደሚችሉ ያስባሉ። ሆኖም ወንድሞቻችን የምናከናውነው ሥራ ማኅበረሰቡን እንደሚጠቅም አብራሩላቸው። በወረርሽኙ ምክንያት እንቅስቃሴያችን በተገደበበት ወቅትም ለማኅበረሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስን ምሥራች እንደምናደርስ ገለጹላቸው፤ ይህ መልእክት ሰዎች ጥሩ ዜጎች እንዲሆኑና ደስተኛ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖራቸው የሚረዳ ነው። የጣቢያዎቹ ኃላፊዎች ይህን ሲሰሙ ለወንድሞች ተጨማሪ የአየር ሰዓት ለመስጠት ተስማሙ።

 በማላዊ የክልል ስብሰባው በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያና በአንድ የሬዲዮ ጣቢያ ተሰራጭቷል፤ ሁለቱም ጣቢያዎች አገር አቀፍ የአየር ሽፋን ያላቸው ሲሆን በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች ተደራሽ ናቸው። በሞዛምቢክ ደግሞ የክልል ስብሰባው በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያና በ85 የሬዲዮ ጣቢያዎች ተሰራጭቷል።

 በሁለቱም አገሮች የክልል ስብሰባውን በቴሌቪዥን ለማሰራጨት በድምሩ 28,227 የአሜሪካ ዶላር፣ በሬዲዮ ለማሰራጨት ደግሞ 20,000 የአሜሪካ ዶላር ገደማ ወስዷል። ለሬዲዮ ጣቢያዎቹ የወጣው ገንዘብ እንደ ጣቢያዎቹ የአየር ሽፋን የተለያየ ነበር፤ ለትናንሽ ጣቢያዎች ከ15 ዶላር ጀምሮ የተከፈለ ሲሆን አገር አቀፍ ተደራሽነት ላለው ጣቢያ ደግሞ 2,777 የአሜሪካ ዶላር ተከፍሏል።

 ወንድሞቻችን በመዋጮ የተገኘውን ገንዘብ ለመቆጠብ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በማላዊ ከጣቢያዎቹ ጋር በመደራደር እስከ 30 በመቶ የሚደርስ ቅናሽ ማግኘት ተችሏል። በመሆኑም 1,711 የአሜሪካ ዶላር መቆጠብ ችለናል። በሞዛምቢክ ያሉ አንዳንድ ጣቢያዎች፣ ሐቀኛ በመሆንና ጊዜውን ጠብቆ ገንዘብ በመክፈል ረገድ ጥሩ ስም ስላተረፍን ዋጋ ሊቀንሱልን ፈቃደኞች ሆነዋል።

የምስጋና ቃላት

 ወንድሞች በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የክልል ስብሰባውን መከታተል በመቻላቸው በጣም አመስጋኝ ናቸው። በማላዊ የሚኖር ፓትሪክ የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “በበላይ አካሉ ውስጥ የሚያገለግሉ ወንድሞቻችን በወረርሽኙ ወቅት ልዩ የሆነ አሳቢነት ስላሳዩን ልናመሰግናቸው እንወዳለን።” በዚያው በማላዊ የሚኖረው አይዛክ የተባለ ወንድም ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “ሌላ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ስለሌለን የይሖዋ ድርጅት የክልል ስብሰባውን በሬዲዮ ማዳመጥ የምንችልበት ዝግጅት በማድረጉ በጣም አመስጋኞች ነን። ይህ ዝግጅት ስለተደረገልን መላው ቤተሰቤ ከክልል ስብሰባው መጠቀም ችሏል። ዝግጅቱ ይሖዋ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር እንድንመለከት አድርጎናል።”

 በሞዛምቢክ የሚኖር አንድ አስፋፊ ለመጀመሪያ ጊዜ በክልል ስብሰባ ላይ የተገኘው በ2020 ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የክልል ስብሰባውን በቴሌቪዥን ለማየት የተደረገልን ዝግጅት ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ አስገንዝቦኛል። ወረርሽኙ መንፈሳዊ ምግብ እንዳያቀርብልን አላገደውም፤ እንዲያውም ሳሎናችን ድረስ አቅርቦልናል። በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለውን ፍቅር ማየት ችያለሁ። እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘሁ አረጋግጦልኛል።”

 ዋይሰን የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ታማኙ ባሪያ በወረርሽኙ ወቅት በተለያዩ መንገዶች እንክብካቤ ስላደረገልን ማመስገን እፈልጋለሁ። የክልል ስብሰባው በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን እንዲተላለፍ ዝግጅት መደረጉ በድሃ አገር ውስጥ ተቸግረን የምንኖረው በርካታ ሰዎች የክልል ስብሰባውን እንድናገኝና ከስብሰባው መጠቀም እንድንችል ረድቶናል።”

 የአስተባባሪዎች ኮሚቴና የትምህርት ኮሚቴ የ2021 የክልል ስብሰባዎችም በአንዳንድ አካባቢዎች በቴሌቪዥንና በሬዲዮ እንዲሰራጩ ለየት ያለ ፈቃድ ሰጥተዋል። በዚህ መልኩ ስብሰባውን ማሰራጨት የሚጠይቀውን ወጪ የምንሸፍነው እንዴት ነው? ለዓለም አቀፉ ሥራ በሚደረገው መዋጮ አማካኝነት ነው፤ እንዲህ ካሉት መዋጮዎች አብዛኞቹ የሚደረጉት donate.mt711.com ላይ በሚገኙት የተለያዩ አማራጮች አማካኝነት ነው። በልግስና ለምታደርጉት መዋጮ ከልብ እናመሰግናለን።

a በ2020 መጀመሪያ አካባቢ የአስተባባሪዎች ኮሚቴ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የጉባኤ ስብሰባዎች በቴሌቪዥንና በሬዲዮ እንዲሰራጩ ፈቃድ ሰጥቶ ነበር። ይህ ዝግጅት የኢንተርኔት ወይም የስልክ አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው ወይም አቅማቸው ባለመፍቀዱ ምክንያት የራሳቸውን ጉባኤ መካፈል ወይም JW ስትሪም መጠቀም የማይችሉ ክርስቲያኖችን ጠቅሟል። ይሁንና ይህ ዝግጅት የተደረገው ከራሳቸው ጉባኤ ጋር ስብሰባ ማድረግ ለሚችሉ አስፋፊዎች አይደለም።