በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የኮሎምቢያ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት

ሰኔ 9, 2021
ኮሎምቢያ

የኮሎምቢያ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት የአንዲትን ወጣት ሃይማኖታዊ ነፃነት አስከበረ

የኮሎምቢያ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት የአንዲትን ወጣት ሃይማኖታዊ ነፃነት አስከበረ

የኮሎምቢያ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት ሚያዝያ 7, 2021 ባስተላለፈው ውሳኔ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ለአካለ መጠን ባትደርስም የምትወስደውን ሕክምና በተመለከተ የራሷን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳላት ገለጸ። ታማሚዋ ደም መውሰድ የማይጠይቅ ሕክምና እንዲሰጣት ጠይቃ ነበር። በተጨማሪም የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤቱ ለአካለ መጠን ባይደርሱም የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ ብቃት ያላቸው ወጣቶች የሚሞሉት የሕክምና መመሪያ ካርድ ሕጋዊ ተቀባይነት እንዳለው ተናግሯል፤ ከዚህም ሌላ ወላጆቹ የልጆቻቸውን የሕክምና ፍላጎት ችላ እንዳሉ ሊቆጠር እንደማይገባ ገልጿል።

እህት ዳኒዬላ ካይሴዶ ከወላጆቿ ጋር

ግንቦት 27, 2020 እህት ዳኒዬላ ካይሴዶ ከባድ የደም ካንሰር እንዳለባት ታወቀ፤ በወቅቱ 16 ዓመቷ ነበር። የሕክምና ባለሙያዎች የኬሞቴራፒ ሕክምና ስትወስድ ደም ሊሰጣት እንደሚገባ ገለጹ። ዳኒዬላ በወቅቱ ተዳክማ የነበረ ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነቷ የተነሳ ደም እንደማትወስድ ለሕክምና ባለሙያዎቹ በአክብሮት ገለጸችላቸው።—የሐዋርያት ሥራ 15:29

ሰኔ 24, 2020 የኮሎምቢያ የቤተሰብ ደህንነት ተቋም ዳኒዬላ ፈቃደኛ ባትሆንም የሕክምና ባለሙያዎቹ ደም እንዲሰጧት ፈቃድ ሰጣቸው። በተጨማሪም ተቋሙ ዳኒዬላ የሥነ ልቦና ምርመራ እንድታደርግ አዘዘ። ምርመራው ዳኒዬላ የምትወስደውን ሕክምና በተመለከተ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችል አእምሯዊና ሥነ ልቦናዊ ብስለት እንዳላት አረጋገጠ። ከዚህም ሌላ ምርመራው ዳኒዬላ ደም ላለመውሰድ የወሰነችው ሌሎች ገፋፍተዋት እንዳልሆነ፣ ከዚህ ይልቅ በሃይማኖታዊ አቋሟ ላይ ተመሥርታ በራሷ ተነሳሽነት ይህን ውሳኔ እንዳደረገች አረጋግጧል።

የበታቹ ፍርድ ቤት ዳኒዬላ ለአካለ መጠን ባትደርስም እንደ አዋቂ ተቆጥራ ደም ላለመውሰድ የመወሰን መብት እንዳላት በየነ። ሆኖም ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ፣ ሐኪሟ ደም የግድ ሊሰጣት እንደሚገባ ካመነ ደም ሊሰጣት እንደሚችል የሚገልጽ ውሳኔ አስተላለፈ። ዳኒዬላ ደም ያለመውሰድ መብቷን ለማስከበር ስትል በወላጆቿ እርዳታ ለሕገ መንግሥት ፍርድ ቤቱ ይግባኝ ለማለት ወሰነች።

የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤቱ ባሳለፈው የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ሃይማኖታዊ ነፃነትን ማክበር ‘ግለሰቦች ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና እንደሚያስጠብቅና ለእሱ በነፃነት አምልኮ እንዲያቀርቡ እንደሚያስችል’ በመግለጽ የዳኒዬላን መብት አስከብሯል። በተጨማሪም ዳኒዬላ በግዴታ ደም ቢሰጣት ከአምላክ ጋር ያላትን ሰላማዊ ግንኙነት እንደሚነካባት እንዲሁም መብቷንና ክብሯን እንደሚጋፋ ገለጸ። ከዚህም ሌላ ውሳኔው ዳኒዬላ ያለደም የሚሰጡ ሕክምናዎችን የመቀበል መብት እንዳላት ገልጿል።

በዚህ ወሳኝ ብይን መሠረት የሕክምና ባለሙያዎች፣ ለአካለ መጠን ባይደርሱም እንደ አዋቂ መወሰን የሚችሉ የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን ከሃይማኖታዊ እምነታቸው ጋር የሚስማማ ሕክምና የመምረጥ መብት የማክበር ግዴታ አለባቸው። በዚህ ክስ ላይ ከተካፈሉት ጠበቆች አንዱ እንዲህ ብሏል፦ “የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤቱ ያደረገው ውሳኔ፣ ልጆች ያላቸው በሕይወት የመኖር መብት ሰብዓዊ ክብር ከማግኘት መብት ተለይቶ ሊታይ እንደማይችል ያረጋግጣል። በመሆኑም ልጆች ክብራቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ከተፈለገ ሃይማኖታዊ አቋማቸው ሊከበርላቸው ይገባል፤ ዳኞችና ሐኪሞች በሃይማኖታዊ እምነታቸው ባይስማሙም ማለት ነው።”

ዳኒዬላ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቱ ያደረገውን ውሳኔ ከሰማች በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “ከሁሉ በላይ ያስደሰተኝ የይሖዋ ስም መከበሩ ነው። ያጋጠመኝ ሁኔታ ይሖዋ ማንኛውንም ፈተና ለእሱ ያለንን ፍቅር ለማሳየት ወደሚያስችል አጋጣሚ መቀየር እንደሚችል አስተምሮኛል።”

የዳኒዬላ ጤንነት እየተሻሻለ ነው፤ ግሩም ሕክምናም እያገኘች ነው። ነሐሴ 2021 በአቅኚዎች ትምህርት ቤት ትካፈላለች። አምላካችን ይሖዋ ወጣቶች በምግባራቸው ሲያከብሩት በእጅጉ እንደሚደሰት እርግጠኞች ነን።—መዝሙር 148:12, 13