በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ወንድም ሄሚን ኪም ከባለቤቱ ከሃቢን ጋር፣ ግዋንግጁ አውራጃ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት

ታኅሣሥ 7, 2022
ደቡብ ኮሪያ

የደቡብ ኮሪያ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የቅጣት ባሕርይ እንዳለው ያጋለጠ የፍርድ ቤት ሙግት

የደቡብ ኮሪያ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የቅጣት ባሕርይ እንዳለው ያጋለጠ የፍርድ ቤት ሙግት

በደቡብ ኮሪያ የሚገኘው የግዋንግጁ አውራጃ ፍርድ ቤት ታኅሣሥ 8, 2022 የወንድም ሄሚን ኪምን ክስ ለመመልከት ቀጠሮ ይዟል። ሄሚን፣ አገሪቱ የዘረጋችው አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የቅጣት ባሕርይ እንዳለው በመግለጽ አገልግሎቱን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ የመጀመሪያው ሰው ነው። ሄሚን እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ እስራት ሊፈረድበትና የወንጀል መዝገብ ሊያዝበት ይችላል።

ሦስት ዓመት የሚፈጀው የደቡብ ኮሪያ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት በዓለም ላይ ረጅም ከሚባሉት አንዱ ነው፤ ወታደራዊ አገልግሎቱ ከሚፈጀው ጊዜ እጥፍ ይበልጣል። አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የሚሰጡት ሰዎች ሦስቱን ዓመት የሚያሳልፉበት ሁኔታ ከእስር ተለይቶ አይታይም፤ ወህኒ ቤቶች ውስጥ ባሉ ማደሪያዎች ውስጥ የቁም እስረኛ የሆኑ ያህል ነው፤ ጥብቅ ክልከላዎችም አሉባቸው። በመሆኑም የደቡብ ኮሪያ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት እውነተኛ ነው ለማለት አያስደፍርም፤ እንዲያውም ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች “አማራጭ ቅጣት” ብለው ጠርተውታል።

ሰኔ 28, 2018 የደቡብ ኮሪያ የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤት፣ የኮሪያ ሕገ መንግሥት በሕሊናቸው ምክንያት ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችን መብት እንደሚያከብር በመግለጽ ታሪካዊ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፤ ከዚያም አማራጭ የሲቪል አገልግሎትን በሕግ ለሚያረቅቀው ሕግ አውጪ አካል እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጠ፦ “አማራጭ አገልግሎቱ የሚወስደው ጊዜ ከመርዘሙ ወይም ሥራው ከመክበዱ የተነሳ በሕሊናቸው ምክንያት አገልግሎቱን ለመስጠት የመረጡት ሰዎች እንኳ አስቸጋሪ ከሆነባቸው ዓላማውን ይስታል፤ እንዲሁም ቅጣት ብቻ ይሆናል፤ ሌሎች መሠረታዊ መብቶቻቸው እንዲጣሱ ሊያደርግም ይችላል።”

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በ1998 ያሳለፈውን የአቋም መግለጫ ተከትሎ አማራጭ አገልግሎት ሊያሟላቸው የሚገቡ ዓለም አቀፍ መሥፈርቶች ተደንግገዋል። ዜጎቻቸው ወታደራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስገድዱ አገራት በሕሊናቸው ምክንያት ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ላልሆኑ ዜጎች አማራጭ አገልግሎት እንዲያዘጋጁ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል፤ ይህ አገልግሎት “ማኅበረሰቡን የሚጠቅም ሆኖም የቅጣት ባሕርይ የሌለው” ሊሆን እንደሚገባ ተጠቁመዋል።

ሄሚን የወንጀል ክስ ሲመሠረትበት ይህ የመጀመሪያው አይደለም። መስከረም 2020 የደቡብ ኮሪያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሕሊና ምክንያት ከወታደራዊ አገልግሎት ነፃ እንዲሆን በመፍረድ ከክስ ነፃ አድርጎታል። ከሳምንታት በኋላ አማራጭ የሲቪል አገልግሎት ለመስጠት አመለከተ። አገልግሎት እንዲሰጥ የተጠራው እስከ የካቲት 7, 2022 ድረስ ጠብቆ ነው። ሆኖም አሁን ያለው አማራጭ የሲቪል አገልግሎት የቅጣት ባሕርይ እንዳለው በጥንቃቄ ካጤነ በኋላ ፈቃደኛ አለመሆኑን በአክብሮት ገልጿል።

ፍርድ ቤቱ ለሄሚን ከፈረደለት መንግሥት፣ አማራጭ አገልግሎቱን ከዓለም አቀፍ መሥፈርቶች ጋር ለማስማማት ማስተካከያ ለማድረግ ሊነሳሳ ይችላል። ይህ ማስተካከያ በጥቅሉ ማኅበረሰቡንም ሆነ የደቡብ ኮሪያ ወንድሞቻችንን እና ቤተሰቦቻቸውን በእጅጉ እንደሚጠቅም የታወቀ ነው። እስከዚያው ግን ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ በይሖዋ መታመናቸውን እንዲቀጥሉና “በትዕግሥትና በደስታ ሁሉንም ነገር በጽናት [እንዲቋቋሙ]” ይሖዋን እንለምነዋለን።—ቆላስይስ 1:11