በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ንድፍ አውጪ አለው?

ካርፔንተር አንት የተባለው ጉንዳን አንቴናውን የሚያጸዳበት መንገድ

ካርፔንተር አንት የተባለው ጉንዳን አንቴናውን የሚያጸዳበት መንገድ

 አንድ ነፍሳት መብረር፣ የሆነ ነገር ላይ መውጣትና አካባቢውን መቃኘት እንዲችል የግድ ንጽሕናውን መጠበቅ ይኖርበታል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ጉንዳን አንቴናው ከቆሸሸ አቅጣጫውን መቀየስ፣ ከሌሎች ጉንዳኖች ጋር የመልእክት ልውውጥ ማድረግና ማሽተት አስቸጋሪ ይሆንበታል። በመሆኑም “የቆሸሹ ነፍሳትን ፈጽሞ አታገኙም” በማለት የሥነ እንስሳት ተመራማሪ የሆኑት አሌክሳንደር ሃክማን ተናግረዋል። አክለውም “እነዚህ ነፍሳት በላያቸው ላይ የሚጣበቀውን ቆሻሻ ማስወገድ የሚችሉበት ዘዴ አላቸው” ብለዋል።

 እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ሃክማንና የሥራ ባልደረቦቻቸው ካርፔንተር አንት (ካምፖኖተስ ሩፊፊመር) የተባለው የጉንዳን ዝርያ አንቴናውን ለማጽዳት በሚጠቀምበት ዘዴ ላይ ጥናት አድርገዋል። ይህ ጉንዳን በአንቴናው ላይ የተጣበቁትን የተለያየ መጠን ያላቸው ቆሻሻዎች ለማጽዳት እግሩን አጥፎ እንደ መቆንጠጫ ያለ ቅርጽ በመፍጠር ሁለቱንም አንቴናዎቹን በመቆንጠጫው መሃል እንደሚያሳልፍ ደርሰውበታል። በእግሩ ላይ ያሉት ዘርዘር ብለው የበቀሉ ፀጉሮች ትላልቅ መጠን ያላቸውን ቆሻሻዎች ያራግፋሉ። አነስ ያሉት ቆሻሻዎች ደግሞ በእግሩ ላይ ባሉት ጥቅጥቅ ያሉ ፀጉሮች አማካኝነት ይጸዳሉ፤ በእነዚህ ፀጉሮች መካከል ያለው ክፍተት በጉንዳኑ አንቴና ላይ ያሉት ፀጉሮች ካላቸው ውፍረት ጋር ተመጣጣኝ ነው። በጣም ትናንሽ የሆኑት ማለትም የሰው ፀጉር አንድ ሰማንያኛ የሚያህል መጠን ያላቸው ቆሻሻዎች ደግሞ ይበልጥ ጥቅጥቅ ባሉት ፀጉሮች አማካኝነት ይወገዳሉ።

 ካርፔንተር አንት የተባለው ጉንዳን አንቴናውን ሲያጸዳ

 ሃክማንና የሥራ ባልደረቦቻቸው ጉንዳኖች አንቴናቸውን ለማጽዳት የሚጠቀሙበት ዘዴ፣ በኢንዱስትሪው መስክ ሥራ ላይ ሊውል እንደሚችል ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በጣም ትንሽ የሚባለው ቆሻሻ እንኳ ረቂቅ የሆኑ የኤሌክትሮኒክ ዕቃዎችን (ማይክሮኤሌክትሮኒክ ኮምፖነንትስ) እና በከፊል ኮረንቲ የሚያስተላልፉ መሣሪያዎችን (ሴሚኮንዳክተርስ) ሊያበላሽ ይችላል፤ በመሆኑም ይህ ዘዴ እነዚህን መሣሪያዎች ንጽሕናውን በጠበቀ መንገድ ለማምረት ይረዳል።

 ምን ይመስልሃል? ካርፔንተር አንት የተባለው የጉንዳን ዝርያ አንቴናውን ለማጽዳት የሚጠቀምበት ውጤታማ ዘዴ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?