በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና

ልጆች እና ዘመናዊ ስልኮች—ክፍል 1፦ ልጄ ዘመናዊ ስልክ ሊኖረው ይገባል?

ልጆች እና ዘመናዊ ስልኮች—ክፍል 1፦ ልጄ ዘመናዊ ስልክ ሊኖረው ይገባል?

 ዘመናዊ ስልክ የሚይዙ ልጆች ቁጥር እየጨመረ ነው፤ a ብዙዎቹ ልጆች በስልካቸው አማካኝነት መኝታ ክፍላቸው ውስጥ ያለማንም ቁጥጥር ኢንተርኔት ይጠቀማሉ። ልጃችሁ ዘመናዊ ስልክ እንዲኖረው መፍቀዳችሁ ምን አደጋ ሊኖረው ይችላል? ጥቅሙስ ምንድን ነው? ልጃችሁ ስልኩ ላይ ምን ያህል ሰዓት እንዲያሳልፍ ልትፈቅዱለት ይገባል?

 ማወቅ የሚኖርባችሁ ነገር

 ጥቅሙ

  •   ልጆች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፣ ወላጆችም አእምሯቸው እንዲረጋጋ ያስችላል። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ሁለት ልጆች ያሏት ቤታኒ የተባለች ሴት እንዲህ ብላለች፦ “የምንኖርበት ዓለም አደገኛ ነው። ስለዚህ ልጆች ምንጊዜም ወላጆቻቸውን ማግኘት መቻል አለባቸው።”

     ካተሪን የተባለች እናት ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ አፕሊኬሽኖች ስልካችሁን ከልጃችሁ ስልክ ጋር በማገናኘት ልጃችሁ ያለበትን ቦታ ለማየት ያስችሏችኋል። እንዲያውም እየነዳ ከሆነ ፍጥነቱን እንኳ ማወቅ ትችላላችሁ።”

  •   ለትምህርታቸው ይረዳቸዋል። መሪ የተባለች እናት እንዲህ ብላለች፦ “ልጆች በኢ-ሜይል ወይም በጽሑፍ መልእክት አማካኝነት የቤት ሥራ ይላክላቸዋል፤ እነሱም በዚያው መንገድ ከአስተማሪዎቻቸው ጋር መገናኘት ይችላሉ።”

 አደጋው

  •   ጊዜ ያባክናል። አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች በየቀኑ ለሰዓታት ስልካቸውን ይጠቀማሉ። ወላጆችም ከልጆቻቸው ጋር በመነጋገር የሚያሳልፉትን ጊዜ ያህል ስልካቸውን በመጠቀም ያሳልፋሉ። አንድ አማካሪ እንደገለጹት አንዳንዶቹ ቤተሰቦች “አብረው ቢቀመጡም እንኳ ስልካቸው ላይ ብቻ ከማፍጠጣቸው የተነሳ የሚተዋወቁ አይመስሉም።” b

  •   ፖርኖግራፊ። አንድ ጥናት እንደገለጸው በአሥራዎቹ ዕድሜ ካሉ ወጣቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በየወሩ ፖርኖግራፊ ለማየት ኢንተርኔት ይጠቀማሉ። ይህ ደግሞ ምንም አያስገርምም፤ ምክንያቱም በስልክ አማካኝነት በቀላሉ ፖርኖግራፊ ማግኘት ይቻላል። በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ሁለት ልጆች ያሉት ዊልያም እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆች ለልጃቸው ዘመናዊ ስልክ ሲሰጡት ሳያስቡት ልጃቸው በሄደበት ሁሉ የሚከተለው የፖርኖግራፊ ሱቅ እየከፈቱለት ሊሆን ይችላል።”

  •   ጥገኝነት። ብዙ ሰዎች ከስልካቸው ጋር ስሜታዊ ትስስር ይፈጥራሉ። ስልካቸውን ከአጠገባቸው ሲያጡት እንደሚጨነቁ፣ ግራ እንደሚጋቡና አልፎ ተርፎም እንደሚታመሙ ገልጸዋል። አንዳንድ ወላጆች እንዳስተዋሉት ልጆቻቸው ስልክ ሲጠቀሙ ሥርዓት አልበኛ ይሆናሉ። ካርመን እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ልጄን ላነጋግረው ስሞክር እንዳቋርጠው ስለማይፈልግ ይገላምጠኛል ወይም አጉል መልስ ይሰጠኛል።”

  •   ሌሎች አደጋዎች። ዘመናዊ ስልኮችን መጠቀም በኢንተርኔት አማካኝነት ለሚሰነዘር ጥቃት እና ለሴክስቲንግ ሊያጋልጥ ይችላል፤ በተጨማሪም በመጥፎ አቀማመጥ ወይም አቋቋም አሊያም በእንቅልፍ ማጣት ምክንያት ለሚከሰቱ የተለያዩ የጤና ችግሮች ሊዳርግ ይችላል። አንዳንድ ወጣቶች ወላጆቻቸው እንዲያዩት የማይፈልጉትን ነገር ለመደበቅ የተለያዩ አፕሊኬሽኖችን ይጠቀማሉ፤ እነዚህ አፕሊኬሽኖች ከላይ ሲታዩ ካልኩሌተር ወይም ምንም ጉዳት የሌለው አፕሊኬሽን ይመስላሉ።

     በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ልጅ ያለችው ዳንኤል ሁኔታውን ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ጥሩም ሆነ መጥፎ ኢንተርኔት ላይ ያሉ ነገሮችን በሙሉ በዘመናዊ ስልክ አማካኝነት ማግኘት ይቻላል።”

 መጠየቅ የሚኖርባችሁ ጥያቄዎች

  •   ‘ልጄ ዘመናዊ ስልክ ያስፈልገዋል?

     መጽሐፍ ቅዱስ “ብልህ [ሰው] አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል” ይላል። (ምሳሌ 14:15) ይህን በአእምሯችሁ በመያዝ እንደሚከተለው እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦

     ‘ልጄ በደህንነቱ ወይም በሌላ ምክንያት የተነሳ ዘመናዊ ስልክ ቢኖረው የተሻለ ነው? ጥቅሙን እና አደጋውን በደንብ አመዛዝኛለሁ? ከዘመናዊ ስልክ ሌላ አማራጭ ይኖር ይሆን?’

     ቶድ የተባለ አባት እንዲህ ብሏል፦ “በስልክ ጥሪ ወይም በጽሑፍ መልእክት አማካኝነት ከልጃችን ጋር ለመገናኘት የሚያስችሉ ተራ ስልኮች አሁንም ይገኛሉ። ደግሞም እነዚህ ስልኮች በጣም ርካሽ ናቸው።”

  •   ‘ልጄ ይህን ኃላፊነት ለመቀበል ደርሷል?’

     መጽሐፍ ቅዱስ “የጥበበኛ ሰው ልብ በትክክለኛ መንገድ ይመራዋል” ይላል። (መክብብ 10:2) ይህን በአእምሯችሁ በመያዝ እንደሚከተለው እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦

     ‘ልጄ እምነት የሚጣልበት እንደሆነ እንድተማመን የሚያደርገኝ ምንድን ነው? በነፃነት የመነጋገር ልማድ አለን? ልጄ የሐቀኝነት ችግር አለበት? ለምሳሌ ጓደኞቹን ይደብቀኛል? ልጄ በቴሌቪዥን፣ በታብሌት፣ በላፕቶፕ ወይም በሌሎች የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አጠቃቀሙ ረገድ ራሱን እንደሚገዛ አሳይቷል?’ ሰሪና የተባለች እናት እንዲህ ብላለች፦ “ዘመናዊ ስልክ በጣም ጠቃሚ መሣሪያ ቢሆንም አደገኛም ነው። ልጃችሁን ገና በለጋ ዕድሜው ምን ዓይነት ኃላፊነት እየጫናችሁበት እንዳለ ልታስቡበት ይገባል።”

  •   ‘ይህን ኃላፊነት ለመቀበል ዝግጁ ነኝ?’

     መጽሐፍ ቅዱስ “ልጅን ሊሄድበት በሚገባው መንገድ አሠልጥነው” ይላል። (ምሳሌ 22:6) ይህን በአእምሯችሁ በመያዝ እንደሚከተለው እያላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ፦

     ‘ልጄ ምን ዓይነት አደጋዎች እንዳሉ እንዲያውቅና ራሱን ከአደጋ እንዲጠብቅ ለመርዳት በሚያስችለኝ መጠን ስለ ስልኩ አውቃለሁ? በስልኩ ላይ ያለውን ለወላጆች የተዘጋጀ መቆጣጠሪያ እንዴት መጠቀም እንደምችል አውቃለሁ? ልጄ በስልክ አጠቃቀሙ ረገድ አስተዋይ እንዲሆን ልረዳው የምችለው እንዴት ነው?’ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ወላጆች ለልጆቻቸው ዘመናዊ ስልክ ከሰጡ በኋላ ዞር ብለውም አያዩአቸውም።”

 ዋናው ነጥብ፦ ልጆች ኃላፊነት እንደሚሰማቸው በሚያሳይ መንገድ ዘመናዊ ስልክ መጠቀም እንዲችሉ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል። ኢንዲስትራክተብል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ራስን ገዝቶ እነዚህን መሣሪያዎች መጠቀም ማቆም በጣም ከባድ ነው፤ ስለዚህ በተለይ ያለወላጅ እርዳታ ልጆቻችን እንዲህ እንዲያደርጉ ልንጠብቅባቸው አንችልም።”

a በዚህ ርዕስ ውስጥ “ዘመናዊ ስልክ” የሚለው አገላለጽ የተሠራበት ኢንተርኔት መጠቀም የሚያስችሉ ስልኮችን ለማመልከት ነው።

b በቶማስ ከርስቲንግ ከተዘጋጀው ዲስኮኔክትድ የተባለ መጽሐፍ የተወሰደ።