በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ጭንቀት ውስጥ ስገባ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳኝ ይችላል?

ጭንቀት ውስጥ ስገባ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳኝ ይችላል?

 መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አዎ፣ ምክንያቱም ከሁሉ የላቀ እርዳታ ማግኘት የሚቻለው ‘ያዘኑትን ከሚያጽናናው አምላክ’ ነው።—2 ቆሮንቶስ 7:6

አምላክ የተጨነቁ ሰዎችን የሚረዳው እንዴት ነው?

  •   ኃይል በመስጠት። አምላክ ‘የሚያጽናናህ’ ያሉብህን ችግሮች በሙሉ በማስወገድ ሳይሆን ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል እንዲሰጥህ ለምታቀርበው ጸሎት መልስ በመስጠት ነው። (ፊልጵስዩስ 4:13) ይሖዋ ሊያዳምጥህ ዝግጁ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ትችላለህ፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል” ይላል። (መዝሙር 34:18) እንዲያውም ስሜትህን በቃላት መግለጽ በምትቸገርበት ጊዜም እንኳ አምላክ በልብህ የምታሰማውን ጩኸት ሊሰማ ይችላል።—ሮም 8:26, 27

  •   ከሌሎች እንዲማሩ በማድረግ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ “ከጥልቅ ወደ አንተ እጮኻለሁ” በማለት ለአምላክ ጸልዮአል። ይህ መዝሙራዊ አምላክ በጥፋተኝነት ስሜት እንድንደቆስ የማይፈልግ መሆኑን ማስታወሱ ከጭንቀቱ እንዲገላገል ረድቶታል። እንዲያውም አምላክን እንዲህ ብሎታል፦ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአትን ብትቈጣጠር፣ ጌታ ሆይ፤ ማን ሊቆም ይችላል? ነገር ግን በአንተ ዘንድ ይቅርታ አለ፤ ስለዚህም ልትፈራ ይገባሃል።”​—መዝሙር 130:1, 3, 4

  •   ተስፋ በመስጠት። አምላክ ማጽናኛ ከመስጠት ባሻገር ለጭንቀት የሚዳርጉንን ነገሮች በሙሉ ለማስወገድ ቃል ገብቷል። አምላክ የገባው ይህ ቃል ሲፈጸም ጭንቀትን ጨምሮ “ያለፉት ነገሮች አይታሰቡም፤ አይታወሱም።”​—ኢሳይያስ 65:17

 ማሳሰቢያ፦ የይሖዋ ምሥክሮች አምላክ ለሰዎች እርዳታ እንደሚሰጥ ቢያምኑም ከባድ የመንፈስ ጭንቀትን ጨምሮ ሌሎች በሽታዎች ሲያጋጥማቸው የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ። (ማርቆስ 2:17) ያም ቢሆን አንድን የሕክምና ዓይነት ለይተን በመጥቀስ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ አናቀርብም፤ በዚህ ረገድ እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ውሳኔ ማድረግ እንደሚኖርበት እናምናለን።