በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ምን ብለን እንጸልይ?—ጸሎት የሚባለው አቡነ ዘበሰማያት ብቻ ነው?

ምን ብለን እንጸልይ?—ጸሎት የሚባለው አቡነ ዘበሰማያት ብቻ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አቡነ ዘበሰማያት ወይም የጌታ ጸሎት፣ እንዴትና ስለ ምን ጉዳይ መጸለይ እንዳለብን ያስተምረናል። ኢየሱስ ይህን ጸሎት ያስተማረው ደቀ መዛሙርቱ “ጌታ ሆይ፣ . . . እንዴት እንደምንጸልይ አስተምረን” ብለው ላቀረቡት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ነው። (ሉቃስ 11:1) ሆኖም በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አቡነ ዘበሰማያት የሚለው ወይም የጌታ ጸሎት ብቻ አይደለም። a ኢየሱስ ይህን ጸሎት ያስተማረው አምላክ ምን ዓይነት ጸሎቶችን እንደሚሰማ ናሙና እንዲሆን ነው።

በዚህ ርዕስ ውስጥ፦

 የጌታ ጸሎት ምን ይላል?

 የጌታ ጸሎት የሚገኘው ማቴዎስ 6:9-13 ላይ ነው፤ ይህን ጸሎት በተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ብንመለከተው ቃላቱ በተወሰነ መጠን ሊለያዩ ይችላሉ። ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።

 አዲስ ዓለም ትርጉም፦ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም። የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን፤ የበደሉንን ይቅር እንዳልን በደላችንን ይቅር በለን። ከክፉው አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።”

 የ1954 ትርጉም፦ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን።” b

 የጌታ ጸሎት ትርጉሙ ምንድን ነው?

 ኢየሱስ ያስተማራቸው ነገሮች ሁሉ ከቀሪዎቹ ቅዱሳን መጻሕፍት ጋር ይስማማሉ፤ በመሆኑም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የጌታን ጸሎት ትርጉም ለመረዳት ያግዙናል ብለን ማሰባችን ምክንያታዊ ነው።

“በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ”

 አምላክን “አባታችን” ብለን መጥራታችን ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም የፈጠረንና ሕይወት የሰጠን እሱ ነው።—ኢሳይያስ 64:8

“ስምህ ይቀደስ”

 ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም ሊከበርና ሊቀደስ ይገባዋል። የሰው ልጆች ስለ አምላክ ማንነትና ስለ ዓላማዎቹ ለሌሎች ሲናገሩ የአምላክ ስም እንዲቀደስ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።—መዝሙር 83:18፤ ኢሳይያስ 6:3

“መንግሥትህ ይምጣ”

 የአምላክ መንግሥት ሰማይ ላይ ያለ መስተዳድር ሲሆን ንጉሡ ኢየሱስ ነው። ይህ መንግሥት መጥቶ መላዋን ምድር እንዲያስተዳድር እንድንጸልይ ኢየሱስ አስተምሮናል።—ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 11:15

“ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም”

 ሰማይ ላይ ክፋትም ሆነ ሞት የለም፤ አምላክ ለምድር ያለው ፈቃድም ቢሆን የሰው ልጆች በሰላምና በደስታ ለዘላለም እንዲኖሩባት ነው።—መዝሙር 37:11, 29

“የዕለቱን ምግባችንን ዛሬ ስጠን”

 ለሕይወት የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮች ለማግኘት የፈጣሪያችን እርዳታ እንደሚያስፈልገን መርሳት የለብንም።—የሐዋርያት ሥራ 17:24, 25

“የበደሉንን ይቅር እንዳልን በደላችንን ይቅር በለን”

 ሰው ሆኖ ኃጢአተኛ ስለሌለ ሁላችንም ይቅርታ ያስፈልገናል። ሆኖም አምላክ ይቅር እንዲለን ከፈለግን እኛም ሌሎች ሲበድሉን ይቅር ልንላቸው ይገባል።—ማቴዎስ 6:14, 15

“ከክፉው አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን”

 ይሖዋ አምላክ መቼም ቢሆን ክፉ ነገር እንድናደርግ አይፈትነንም። (ያዕቆብ 1:13) ሆኖም “ክፉው” የተባለው ሰይጣን ዲያብሎስ ይፈትነናል፤ ሰይጣን “ፈታኙ” ተብሎም ተጠርቷል። (1 ዮሐንስ 5:19፤ ማቴዎስ 4:1-4) ይሖዋን የሚያሳዝን ነገር ለማድረግ ስንፈተን እጅ እንዳንሰጥ አምላክን ልንለምነው ይገባል።

 መጸለይ ያለብን አቡነ ዘበሰማያትን በመድገም ነው?

 ኢየሱስ የጌታን ጸሎት ያስተማረው የጸሎት ናሙና እንዲሆነን እንጂ ቃል በቃል እንድንደግመው አይደለም። ኢየሱስ ይህን ጸሎት ከማስተማሩ በፊት እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል፦ “በምትጸልዩበት ጊዜ . . . አንድ ዓይነት ነገር ደጋግማችሁ አታነብንቡ።” (ማቴዎስ 6:7) በሌላ ወቅት ላይ እንዴት እንደምንጸልይ ሲያስተምር እነዚያኑ ቃላት መልሶ አልደገመም፤ የተጠቀመባቸው ቃላት ትንሽ ይለያሉ።—ሉቃስ 11:2-4

 ከሁሉ የተሻለው ጸሎት፣ የልባችንን አውጥተን ለአምላክ በመናገር የምናቀርበው ጸሎት ነው።—መዝሙር 62:8

 እንዴት እንጸልይ?

 የጌታ ጸሎት፣ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ጸሎት ለማቅረብ ምን ማድረግ እንደምንችል ያስተምረናል። ስለ ጸሎት ከሚናገሩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋርም ይስማማል። እንዴት?

  •   ልንጸልይ የሚገባው ወደ አምላክ ብቻ ነው

     ጥቅስ፦ “ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።”—ፊልጵስዩስ 4:6

     ትርጉሙ፦ መጸለይ ያለብን ወደ አምላክ ብቻ እንጂ ወደ ኢየሱስ፣ ወደ ማርያም ወይም ወደ ቅዱሳን አይደለም። በጌታ ጸሎት መጀመሪያ ላይ ያሉት “አባታችን ሆይ” የሚሉት ቃላት መጸለይ ያለብን ወደ ይሖዋ አምላክ ብቻ እንደሆነ ያስተምሩናል።

  •   በጸሎት መጠየቅ ያለብን ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ነገሮችን ነው

     ጥቅስ፦ “የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።”—1 ዮሐንስ 5:14

     ትርጉሙ፦ ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ እስከሆነ ድረስ ስለ ማንኛውም ነገር መጸለይ እንችላለን። ኢየሱስ በጌታ ጸሎት ላይ ‘ፈቃድህ ይፈጸም’ የሚለውን ልመና ማካተቱ የአምላክ ፈቃድ ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው ያስተምረናል። መጽሐፍ ቅዱስን በመማር አምላክ ለምድርም ሆነ ለሰው ልጆች ያለው ፈቃድ ምን እንደሆነ ማወቅ እንችላለን።

  •   ስለ ግል ጉዳዮቻችን መጸለይ እንችላለን

     ጥቅስ፦ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል።”—መዝሙር 55:22

     ትርጉሙ፦ አምላክ በግል ለሚያሳስቡን ነገሮች ትኩረት ይሰጣል። ኢየሱስ ባስተማረው የጌታ ጸሎት ላይ የግል ልመናዎችን አካትቷል፤ እኛም አምላክ ለዕለት የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንዲሰጠን፣ ከባድ ውሳኔዎችን ስናደርግ እንዲመራን፣ በችግር ጊዜ እንዲደግፈንና ኃጢአታችንን ይቅር እንዲለን c መለመን እንችላለን።

a ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ በሌሎች ወቅቶች ሲጸልዩ በጸሎት ናሙናው ላይ ያለውን ሐሳብ ቃል በቃል አልደገሙም።—ሉቃስ 23:34፤ ፊልጵስዩስ 1:9

b የ1954 ትርጉም የጌታን ጸሎት የሚደመድመው “መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን” በሚለው ሐረግ ነው። ይህ የውዳሴ ሐረግ በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይም ይገኛል። ሆኖም ዘ ጀሮም ቢብሊካል ኮሜንታሪ የተባለው ማመሣከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው ይህ ሐረግ “ተዓማኒነት ባላቸው አብዛኞቹ [ጥንታዊ ቅጂዎች] ላይ አይገኝም።”

c የአምላክ ይቅርታ እንደሚያስፈልጋቸው የሚሰማቸው አንዳንድ ሰዎች ከበደላቸው የተነሳ መጸለይ ይከብዳቸው ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ እንዲህ ላሉት ሰዎች “በመካከላችን የተፈጠረውን ችግር ተወያይተን እንፍታ” የሚል ጥሪ አቅርቦላቸዋል። (ኢሳይያስ 1:18) ይሖዋ ከልብ ተጸጽተው ይቅርታውን የሚፈልጉ ሰዎችን ይቅር ይላቸዋል።