በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ክርስቲያኖች የሕክምና እርዳታ ይቀበላሉ?

ክርስቲያኖች የሕክምና እርዳታ ይቀበላሉ?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 እንዴታ! ኢየሱስ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም” በማለት የተናገረው ሐሳብ ተከታዮቹ የሕክምና እርዳታ መቀበል እንደሚችሉ ይጠቁማል። (ማቴዎስ 9:12) መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና መጽሐፍ ባይሆንም አምላክን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች ሊከተሏቸው የሚገቡ መመሪያዎችን ይዟል።

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ

 1. ይህ ሕክምና ምን ነገሮችን እንደሚያካትት አውቃለሁ? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሁሉን ከማመን’ ይልቅ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ጥረት እንድናደርግ ይመክረናል።​—ምሳሌ 14:15

 2. ሌሎች ሐኪሞችን ማማከር ያስፈልገኝ ይሆን? በተለይ ሕመሙ ከባድ ከሆነ “ብዙ አማካሪዎች” መኖራቸው ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።​—ምሳሌ 15:22

 3. ሕክምናው ‘ከደም ራቁ’ የሚለውን የመጽሐፍ የቅዱስ ምክር እንድጥስ ያደርገኛል?​—የሐዋርያት ሥራ 15:20

 4. ምርመራው ወይም ሕክምናው ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ አለው? መጽሐፍ ቅዱስ ‘መናፍስታዊ ድርጊትን’ ያወግዛል። (ገላትያ 5:19-21) ሕክምናው ከመናፍስታዊ ድርጊቶች ጋር ንክኪ ይኖረው እንደሆነ ለማወቅ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦

  •   ሕክምናውን የሚሰጠው ሰው መናፍስታዊ ድርጊቶችን ይፈጽማል?

  •   ሕክምናውን የሚሰጠው ሰው፣ ግለሰቡ በበሽታ የተያዘው አማልክት ስለተቆጡ ወይም ጠላቶቹ መተት ስላደረጉበት እንደሆነ ይናገራል?

  •   መድኃኒቱ ሲዘጋጅ ወይም ሲወሰድ መሥዋዕት፣ ድግምት አሊያም ሌላ ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት ወይም ዕቃ ጥቅም ላይ ይውላል?

 5. የጤናዬ ጉዳይ ከልክ በላይ ያሳስበኛል? መጽሐፍ ቅዱስ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” የሚል ምክር ይሰጣል። (ፊልጵስዩስ 4:5) ምክንያታዊ መሆን እንደ መንፈሳዊ ነገሮች ባሉ “ይበልጥ አስፈላጊ [በሆኑ] ነገሮች” ላይ እንድታተኩር ይረዳሃል።​—ፊልጵስዩስ 1:10፤ ማቴዎስ 5:3