በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የዓለም መጨረሻ የሚመጣው መቼ ነው?

የዓለም መጨረሻ የሚመጣው መቼ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 የዓለም መጨረሻ የሚመጣው መቼ እንደሆነ ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለም” የሚለውን ቃል የሚጠቀምበት እንዴት እንደሆነ መረዳት አስፈላጊ ነው። አብዛኛውን ጊዜ “ዓለም” ተብሎ የሚተረጎመው ኮስሞስ የተባለው የግሪክኛ ቃል የሰው ልጆችን በተለይም ከአምላክና ከፈቃዱ ጋር ተስማምቶ የማይኖረውን የሰው ዘር ክፍል ለማመልከት ይሠራበታል። (ዮሐንስ 15:18, 19፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ኮስሞስ የሚለው ቃል ማኅበረሰቡ ያለበትን ሥርዓት ያመለክታል።—1 ቆሮንቶስ 7:31፤ 1 ዮሐንስ 2:15, 16 a

“የዓለም መጨረሻ” ምንድን ነው?

 “የዓለም መጨረሻ” የሚለው አገላለጽ በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። (ማቴዎስ 24:3) ይህ አገላለጽ የሚያመለክተው ምድር ወይም የሰው ልጆች በሙሉ እንደሚጠፉ ሳይሆን በምድር ላይ ያለው ሥርዓት እንደሚጠፋ ነው።—1 ዮሐንስ 2:17

 መጽሐፍ ቅዱስ ‘ክፉ አድራጊዎች እንደሚጠፉና’ ጥሩ ሰዎች በምድር ላይ ተደስተው እንደሚኖሩ ይናገራል። (መዝሙር 37:9-11) ይህ ጥፋት የሚመጣው በአርማጌዶን ጦርነት በሚደመደመው ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ነው።—ማቴዎስ 24:21, 22፤ ራእይ 16:14, 16

የዓለም መጨረሻ የሚመጣው መቼ ነው?

 ኢየሱስ “ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:36, 42) አክሎም ‘ባላሰባችሁት ሰዓት ይመጣል’ በማለት መጨረሻው የሚመጣው በድንገት እንደሆነ ጠቁሟል።—ማቴዎስ 24:44

 መጨረሻው የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት ማወቅ እንደማንችል የታወቀ ነው፤ ሆኖም ኢየሱስ የዓለም መጨረሻ መድረሱን እንድናውቅ የሚያስችሉንን ክንውኖች አጠቃሎ የያዘ “ምልክት” ሰጥቶናል። (ማቴዎስ 24:3, 7-14) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጊዜ ‘የፍጻሜው ዘመን፣’ እንዲሁም ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ በማለት ይጠራዋል።—ዳንኤል 12:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

ከዓለም መጨረሻ በኋላ የሚተርፍ ነገር ይኖራል?

 አዎ። መጽሐፍ ቅዱስ “ምድር . . . ለዘላለም ከቦታዋ አትናወጥም” ስለሚል ምድር አትጠፋም። (መዝሙር 104:5) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” ስለሚል በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ይኖራሉ። (መዝሙር 37:29) አምላክ ከመጀመሪያም የነበረውን ዓላማ ዳር ያደርሳል፦

a አዮን የሚለው የግሪክኛ ቃልም በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ “ዓለም” ተብሎ ተተርጉሟል። በዚህ መንገድ ሲተረጎም አዮን የሚለው ቃል ማኅበረሰቡ ያለበትን ሥርዓት ስለሚያመለክት ከኮስሞስ ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ይኖረዋል።