በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ሠርግ ምን ይመስላል?

የይሖዋ ምሥክሮች ሠርግ ምን ይመስላል?

 ብዙውን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ቀለል ያለና ክብር ያለው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ይኖራቸዋል፤ በፕሮግራሙ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አጠር ያለ ንግግር ይቀርባል። ከሥነ ሥርዓቱ በኋላ ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ሊሰባሰቡ ወይም ድግስ ሊያዘጋጁ ይችላሉ። a ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረበት ወቅት በቃና ከተማ በተደረገ እንዲህ ያለ ድግስ ላይ ተገኝቶ ነበር።—ዮሐንስ 2:1-11

 በጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ምን ይከናወናል?

 የሥነ ሥርዓቱ ዋነኛ ክፍል የጋብቻ ንግግር ነው፤ ንግግሩ 30 ደቂቃ ገደማ የሚፈጅ ሲሆን ንግግሩን የሚያቀርበው አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ አገልጋይ ነው። ሞቅ ባለና በሚያበረታታ መንገድ የሚቀርበው ይህ ንግግር መጽሐፍ ቅዱስ ሙሽሮቹ ዘላቂ፣ ፍቅር የሰፈነበትና የሰመረ ትዳር እንዲመሠርቱ የሚረዳቸው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።—ኤፌሶን 5:33

 በብዙ አገሮች ውስጥ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ አገልጋዮች ሕጋዊ ጋብቻ እንዲያስፈጽሙ ይፈቅዳል። ሁኔታው እንዲህ ከሆነ በንግግሩ መደምደሚያ ላይ ሙሽሮቹ ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ። ቀለበት ሊለዋወጡም ይችላሉ። ከዚያም ሃይማኖታዊ አገልጋዩ ሁለቱ ሰዎች ሕጋዊ ባልና ሚስት እንደሆኑ ያሳውቃል።

 በሌሎች አገሮች ውስጥ ደግሞ ሕጉ ሙሽሮች በአንድ የመንግሥት ተቋም ውስጥ ጋብቻቸውን እንዲፈጽሙ ያስገድዳል። ሙሽሮቹ የጋብቻ ንግግሩ ከመቅረቡ ከጥቂት ጊዜ በፊት እንዲህ ያለውን ሕጋዊ ጋብቻ ይፈጽማሉ። ሙሽሮቹ በመንግሥት ተቋሙ ውስጥ ቃለ መሐላ ካልፈጸሙ በንግግሩ መደምደሚያ ላይ ቃለ መሐላ መፈጸም ይችላሉ። በመንግሥት ተቋሙ ውስጥ ቃለ መሐላ ፈጽመው ከነበረ ደግሞ ቃለ መሐላውን አስቀድመው እንደፈጸሙ በሚጠቁም መንገድ በንግግሩ ላይ ሊደግሙት ይመርጡ ይሆናል። ከዚያም አምላክ ሙሽሮቹን እንዲባርካቸው ለመጠየቅ በሚቀርብ ጸሎት ንግግሩ ይደመደማል።

 የይሖዋ ምሥክሮች የጋብቻ ሥነ ሥርዓት የሚካሄደው የት ነው?

 የሚቻል ከሆነ፣ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ መፈጸም ይመርጣሉ። b ሙሽሮቹ ከንግግሩ በኋላ ድግስ የሚኖራቸው ከሆነ ደግሞ ለግብዣው ሌላ ቦታ ይመርጣሉ።

 በዝግጅቱ ላይ ማን ሊገኝ ይችላል?

 ሠርጉ የሚካሄደው በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ከሆነ አብዛኛውን ጊዜ ዝግጅቱ ለሁሉም ሰው ክፍት ነው፤ የይሖዋ ምሥክሮችም ሆኑ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች መገኘት ይችላሉ። ሙሽሮቹ ድግስ ካዘጋጁ ግን የሚፈልጉትን ሰው መርጠው ይጠራሉ።

 እንግዶች ምን ዓይነት ልብስ መልበስ ይኖርባቸዋል?

 በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የሚካሄድ ሠርግ የተለየ የአለባበስ ደንብ ባይኖረውም የይሖዋ ምሥክሮች ልከኛና የሚያስከብር አለባበስ እንድንለብስ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መመሪያ ለመታዘዝ ጥረት ያደርጋሉ። ሌሎችም ተመሳሳይ ነገር ቢያደርጉ ደስ ይላቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9) ሙሽሮቹ ድግስ ለማዘጋጀት ከመረጡም ይህ መመሪያ ይሠራል።

 የሠርግ ስጦታ ይኖራል?

 መጽሐፍ ቅዱስ ለጋሶች እንድንሆን ያበረታታናል። (መዝሙር 37:21) የይሖዋ ምሥክሮች የሠርግ ስጦታ መስጠትም ሆነ መቀበል ያስደስታቸዋል። (ሉቃስ 6:38) ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች ስጦታ እንዲሰጣቸው አይጠይቁም ወይም ስጦታ የሰጧቸውን ሰዎች ስም በሕዝብ ፊት አያስነግሩም። (ማቴዎስ 6:3, 4፤ 2 ቆሮንቶስ 9:7፤ 1 ጴጥሮስ 3:8) እንዲህ ያለው ልማድ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጋር የሚጋጭ ከመሆኑም ሌላ ታዳሚዎቹን ሊያሸማቅቅ ይችላል።

 ጽዋ የማንሳት ሥነ ሥርዓት ይኖራል?

 አይኖርም። የይሖዋ ምሥክሮች ጽዋ በማንሳት ሥነ ሥርዓት አይካፈሉም፤ ምክንያቱም ይህ ልማድ ከሐሰት ሃይማኖታዊ ልማዶች የመነጨ ነው። c የይሖዋ ምሥክሮች ለሙሽሮቹ መልካም ምኞታቸውን በሌሎች መንገዶች ይገልጻሉ።

 ሙሽሮቹ ላይ ሩዝ ወይም ወረቀት ይበተናል?

 አይበተንም። በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች በሙሽሮቹ ላይ ሩዝ፣ ወረቀት ወይም ሌላ ነገር ይበትናሉ። ይህም ለሙሽሮቹ መልካም ዕድል፣ ደስታና ረጅም ዕድሜ እንደሚያመጣላቸው ያምናሉ። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች ከአጉል እምነት ጋር ንክኪ ካላቸው ልማዶች ይርቃሉ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከሚጋጩት ከእነዚህ ልማዶች መካከል “መልካም ዕድል ይሁንላችሁ” ብሎ መናገር ይገኝበታል።—ኢሳይያስ 65:11

 ምግብና መጠጥ ይቀርባል?

 በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በሚከናወነው ሥነ ሥርዓት ላይ ምግብና መጠጥ አይቀርብም። አንዳንድ ሙሽሮች ከንግግሩ በኋላ ምግብ ወይም መጠጥ የሚቀርብበት ድግስ ለማዘጋጀት ሊመርጡ ይችላሉ። (መክብብ 9:7) የአልኮል መጠጥ እንዲቀርብ ከወሰኑ ተገቢ መጠን ያለው መጠጥ እንዲቀርብና አልኮል ለመጠጣት ዕድሜያቸው ለሚፈቅድላቸው ሰዎች ብቻ እንዲቀርብ ማድረግ አለባቸው።—ሉቃስ 21:34፤ ሮም 13:1, 13

 ሙዚቃ ወይም ጭፈራ ይኖራል?

 ሙሽሮቹ ድግስ የሚኖራቸው ከሆነ ሙዚቃና ጭፈራ እንዲኖር ሊመርጡ ይችላሉ። (መክብብ 3:4) ሙሽሮቹ የሚመርጡት ሙዚቃ በባሕላቸውና በግል ምርጫቸው ላይ የተመካ ነው፤ ሆኖም የሙዚቃ ምርጫቸው ተገቢ ሊሆን ይገባል። በስብሰባ አዳራሽ የሚካሄደው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጭብጥ ላይ የተመሠረተ ሙዚቃ ይኖረዋል።

 የይሖዋ ምሥክሮች የጋብቻ ክብረ በዓል ያከብራሉ?

 የጋብቻ ክብረ በዓል ማክበርን የሚደግፍም ሆነ የሚያወግዝ ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ባለትዳሮች የጋብቻ ክብረ በዓላቸውን ማክበርን በተመለከተ የራሳቸውን ውሳኔ ያደርጋሉ። የጋብቻ ክብረ በዓል ለማክበር ከወሰኑ ብቻቸውን ወይም ከወዳጅ ዘመድ ጋር ሆነው ሊያከብሩ ይችላሉ።

a ከሠርግ ጋር የተያያዙ ልማዶች፣ ባሕሎችና ሕጎች ከቦታ ቦታ ሊለያዩ ይችላሉ።

b ንግግሩን የሚያቀርበው ሃይማኖታዊ አገልጋይ የጋብቻው ሥነ ሥርዓቱን ለማስፈጸም ገንዘብ አይከፈለውም፤ የስብሰባ አዳራሹን ለመጠቀምም ክፍያ የለውም።

c ጽዋ የማንሳት ልማድ ስላለው አረማዊ ምንጭ መረጃ ለማግኘት በየካቲት 15, 2007 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።