በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች የጌታ ራትን የሚያከብሩበት መንገድ ከሌሎች ሃይማኖቶች የተለየ የሆነው ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች የጌታ ራትን የሚያከብሩበት መንገድ ከሌሎች ሃይማኖቶች የተለየ የሆነው ለምንድን ነው?

 የጌታ ራትን የምናከብርበት መንገድ ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ይህ በዓል “የጌታ ራት፣” የመጨረሻው ራት እንዲሁም የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በመባልም ይታወቃል። (1 ቆሮንቶስ 11:20) ሌሎች ሃይማኖቶች ከዚህ በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ የሚያምኑባቸውም ሆነ የሚያደርጓቸው በርካታ ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ አይደሉም።

ዓላማ

 የጌታ ራትን የምናከብርበት ዓላማ፣ የኢየሱስን ሞት በማስታወስ እሱ ለእኛ ሲል ለከፈለው መሥዋዕት አመስጋኝነታችንን ለመግለጽ ነው። (ማቴዎስ 20:28፤ 1 ቆሮንቶስ 11:24) ይህ በዓል የቁርባን ሥርዓት አሊያም የአምላክን ጸጋ ወይም የኃጢአት ይቅርታ የሚያስገኝ ሃይማኖታዊ ልማድ አይደለም። a መጽሐፍ ቅዱስ፣ የኃጢአት ይቅርታ የምናገኘው አንድ ዓይነት ሃይማኖታዊ ሥርዓት በመፈጸም ሳይሆን በኢየሱስ በማመን ብቻ እንደሆነ ያስተምራል።—ሮም 3:25፤ 1 ዮሐንስ 2:1, 2

በየስንት ጊዜው?

 ኢየሱስ፣ የጌታ ራትን እንዲያከብሩ ደቀ መዛሙርቱን ያዘዛቸው ቢሆንም በየስንት ጊዜው ማክበር እንዳለባቸው ግን አልነገራቸውም። (ሉቃስ 22:19) አንዳንዶች በየወሩ መከበር እንዳለበት የሚሰማቸው ሲሆን ሌሎች ደግሞ በየሳምንቱ፣ በየቀኑ፣ ወይም በቀን ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት አሊያም ደግሞ ግለሰቡ አስፈላጊ ሆኖ የተሰማውን ያህል ማክበር እንደሚችል ይሰማቸዋል። b ሆኖም ግምት ውስጥ ልናስገባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮችን እስቲ ተመልከት።

 ኢየሱስ የጌታ ራትን ያቋቋመው አይሁዳውያን ፋሲካን በሚያከብሩበት ዕለት ሲሆን የሞተውም በዚያኑ ቀን ነበር። (ማቴዎስ 26:1, 2) ይህ የሆነው በአጋጣሚ አይደለም። ቅዱሳን መጻሕፍት የኢየሱስን መሥዋዕት ከፋሲካ በግ ጋር ያመሳስሉታል። (1 ቆሮንቶስ 5:7, 8) የፋሲካ በዓል የሚከበረው ደግሞ በዓመት አንድ ጊዜ ነበር። (ዘፀአት 12:1-6፤ ዘሌዋውያን 23:5) በተመሳሳይ ሁኔታ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች c የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ የሚያከብሩት በዓመት አንድ ጊዜ ነበር። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች የሚከተሉት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ይህን ልማድ ነው።

ቀንና ሰዓት

 ኢየሱስ የተወው ምሳሌ ይህ በዓል በየስንት ጊዜው መከበር እንዳለበት ብቻ ሳይሆን በዓሉ የሚከበርበትን ቀንና ሰዓትም ለማወቅ ይረዳናል። ኢየሱስ ይህን በዓል ለመጀመሪያ ጊዜ ያከበረው በመጽሐፍ ቅዱስ የጨረቃ አቆጣጠር መሠረት ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ነበር። (ማቴዎስ 26:18-20, 26) እኛም፣ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የተዉትን ምሳሌ በመከተል የመታሰቢያውን በዓል በየዓመቱ ኒሳን 14 ላይ እናከብራለን። d

 ኒሳን 14, 33 ዓ.ም. የዋለው ዓርብ ቀን ላይ ቢሆንም በዓሉ የሚከበርበት ቀን በየዓመቱ የተለያየ ዕለት ላይ ሊውል ይችላል። ኒሳን 14 የሚውልበትን ዕለት ለማወቅ በዘመናዊው የአይሁዳውያን የቀን መቁጠሪያ የሚሠራበትን ዘዴ ከመጠቀም ይልቅ በኢየሱስ ዘመን የነበረውን የቀን አቆጣጠር እንከተላለን። e

ቂጣና የወይን ጠጅ

 ኢየሱስ ይህን አዲስ በዓል ሲያቋቁም የተጠቀመው ያልቦካ ቂጣና ቀይ የወይን ጠጅ ከፋሲካ በዓል የተረፈ ነበር። (ማቴዎስ 26:26-28) እኛም ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በመከተል ለበዓሉ እርሾም ሆነ ማንኛውም ዓይነት ማጣፈጫ ያልገባበት ቂጣ እንጠቀማለን፤ የወይን ጠጁም ቢሆን ምንም ነገር ያልተቀላቀለበት ቀይ የወይን ጠጅ እንጂ የወይን ጭማቂ አሊያም ማጣፈጫ ወይም ቅመም የገባበት ወይን አይደለም።

 አንዳንድ ሃይማኖቶች እርሾ የገባበት ቂጣ ይጠቀማሉ፤ ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እርሾ አብዛኛውን ጊዜ የተሠራበት ኃጢአትንና ብክለትን ለማመልከት ነው። (ሉቃስ 12:1፤ 1 ቆሮንቶስ 5:6-8፤ ገላትያ 5:7-9) በመሆኑም ኃጢአት የሌለበትን የክርስቶስን አካል ሊወክል የሚችለው እርሾም ሆነ ማንኛውም ዓይነት ማጣፈጫ ያልገባበት ቂጣ ብቻ ነው። (1 ጴጥሮስ 2:22) በወይን ጠጅ ፋንታ ያልፈላ የወይን ጭማቂ መጠቀም ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ የሌለው ልማድ ነው። አንዳንድ ሃይማኖቶች እንዲህ የሚያደርጉት የአልኮል መጠጥ መጠጣትን ስለሚከለክሉ ነው፤ እርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት መመሪያ አልያዘም።—1 ጢሞቴዎስ 5:23

ምሳሌያዊ እንጂ ቃል በቃል ሥጋና ደም አይደለም

 በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚቀርቡት ቂጣና የወይን ጠጅ፣ የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚወክሉ ምሳሌያዊ ነገሮች ናቸው። አንዳንዶች እንደሚያስቡት ተአምራዊ በሆነ መንገድ ተቀይረው ትክክለኛ ሥጋና ደም አይሆኑም ወይም ከኢየሱስ ሥጋና ደም ጋር አይቀላቀሉም። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሐሳብ የሚደግፈው እንዴት እንደሆነ ተመልከት።

  •   ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን ያዘዛቸው ቃል በቃል ደሙን እንዲጠጡ ቢሆን ኖሮ ደም እንዳይበሉ የሚከለክለውን የአምላክን ሕግ እንዲጥሱ መናገር ይሆንበት ነበር። (ዘፍጥረት 9:4፤ የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29) ኢየሱስ ደግሞ አምላክ ከደም ቅድስና ጋር በተያያዘ የሰጠውን ሕግ እንዲጥሱ ለሰዎች መመሪያ ሊሰጥ አይችልም።—ዮሐንስ 8:28, 29

  •   በወቅቱ ሐዋርያት የኢየሱስን ደም ቃል በቃል እየጠጡ የነበሩ ቢሆን ኖሮ፣ ደሙ “የሚፈሰው” በሌላ አባባል መሥዋዕታዊ ሞት የሚሞተው ወደፊት እንደሆነ አድርጎ አይናገርም ነበር።—ማቴዎስ 26:28

  •   ኢየሱስ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” ነው። (ዕብራውያን 9:25, 26) ይሁን እንጂ የጌታ ራት በተከበረ ቁጥር ቂጣውና የወይን ጠጁ ተቀይረው የኢየሱስን ሥጋና ደም የሚሆኑ ከሆነ መሥዋዕቱ የሚቀርበው በተደጋጋሚ ነው ማለት ይሆናል።

  •   ኢየሱስ “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አለ እንጂ “ይህን መሥዋዕቴን ሁልጊዜ አቅርቡ” አላለም።—1 ቆሮንቶስ 11:24

 በሚስጥረ ቁርባን ማለትም ቂጣውና የወይን ጠጁ ተለውጦ ቃል በቃል የኢየሱስን ሥጋና ደም ይሆናል ብለው የሚያምኑ ሰዎች፣ እንዲህ ያለ አመላካከት እንዲኖራቸው ያደረገው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተተረጎሙበት መንገድ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ኢየሱስ የወይን ጠጁን በተመለከተ “የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው” ብሎ እንደተናገረ አድርገው ተርጉመውታል። (ማቴዎስ 26:28) ነገር ግን ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ “ይህ ደሜን ያመለክታል፣” “ይህ ደሜ ማለት ነው” ወይም “ይህ ደሜን ይወክላል” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። f ስለዚህ ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ያደርግ እንደነበረው በምሳሌያዊ መንገድ እያስተማረ ነበር።—ማቴዎስ 13:34, 35

ከቂጣውና ከወይኑ የሚካፈሉት እነማን ናቸው?

 የይሖዋ ምሥክሮች የጌታ ራትን በሚያከብሩበት ወቅት፣ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈሉት ሰዎች ቁጥር በጣም ጥቂት ነው። ለምን?

 የፈሰሰው የኢየሱስ ደም አምላክ ከጥንቱ የእስራኤል ብሔር ጋር የገባውን ቃል ኪዳን የሚተካ “አዲስ ቃል ኪዳን” እንዲቋቋም አስችሏል። (ዕብራውያን 8:10-13) በዚህ አዲስ ቃል ኪዳን የታቀፉ ሰዎች ከቂጣውና ከወይኑ ይካፈላሉ። በዚህ ቃል ኪዳን የሚታቀፉት ሁሉም ክርስቲያኖች ሳይሆኑ አምላክ ልዩ በሆነ መንገድ ‘የጠራቸው’ ሰዎች ብቻ ነው። (ዕብራውያን 9:15፤ ሉቃስ 22:20) እነዚህ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ሆነው በሰማይ የመግዛት ልዩ መብት ያገኛሉ፤ ቁጥራቸው ደግሞ 144,000 ብቻ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ሉቃስ 22:28-30፤ ራእይ 5:9, 10፤ 14:1, 3

 ከክርስቶስ ጋር እንዲገዙ ከተጠሩት “ትንሽ መንጋ” በተለየ አብዛኞቻችን በምድር ላይ ለዘላለም ከሚኖሩት “እጅግ ብዙ ሕዝብ” መካከል የመሆን ተስፋ አለን። (ሉቃስ 12:32፤ ራእይ 7:9, 10) ተስፋችን ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ስለሆነ ከቂጣውና ከወይኑ ባንካፈልም እንኳ ኢየሱስ ለእኛ ሲል ለከፈለው መሥዋዕት ያለንን አመስጋኝነት እንገልጻለን።—1 ዮሐንስ 2:2

a በማክሊንቶክና በስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ ጥራዝ 9፣ ገጽ 212 እንዲህ ይላል፦ “ቅዱስ ቁርባን የሚለው ሐረግ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አይገኝም፤ በተጨማሪም μυστήριον [ሚስቴሪዮን፣ ሚስጥር ማለት ነው] የሚለው የግሪክኛ ቃል ጥምቀትን፣ የጌታ ራትን ወይም ማንኛውንም ክብረ በዓል ለማመልከት ተሠርቶበት አያውቅም።”

b አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ከጌታ ራት ጋር በተያያዘ ‘በበላችሁና በጠጣችሁ ቁጥር’ የሚለውን አገላለጽ ይጠቀማሉ፤ አንዳንዶች ይህ አባባል በዓሉ ምን ያህል ጊዜ በተደጋጋሚ መከበር እንዳለበት ይጠቁማል በሚል ይረዱታል። ይሁን እንጂ መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ እዚህ ቦታ ላይ የገባበት መንገድ “በ . . . ጊዜ” ወይም “ጊዜ ሁሉ” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል።—1 ቆሮንቶስ 11:25, 26 አዲሱ መደበኛ ትርጉም፤ የ1954 ትርጉም

c ዘ ኒው ሻፍ-ሄርትሶክ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጂየስ ኖውሌጅ የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 4፣ ገጽ 43-44 እንዲሁም በማክሊንቶክ እና ስትሮንግ የተዘጋጀውን ሳይክሎፒዲያ፣ ጥራዝ 8፣ ገጽ 836 ተመልከት።

d ዘ ኒው ካምብሪጅ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1፣ ገጽ 841 ተመልከት።

e በዘመናዊው የአይሁዳውያን የቀን መቁጠሪያ መሠረት የኒሳን ወር መጀመሩ የሚረጋገጠው በከዋክብት ጥናት አዲስ ጨረቃ ስትታይ ነው፤ ሆኖም በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሠራበት የነበረው ዘዴ ይህ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ወሩ የሚጀምረው በኢየሩሳሌም አዲስ ጨረቃ ስትታይ ነው፤ ይህም በከዋክብት ጥናት መሠረት አዲስ ጨረቃ ወጥታለች ከሚባልበት ዕለት በአንድ ወይም ከዚያ በላይ ቀን ሊዘገይ ይችላል። በዚህ ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ በዓል የሚያከብሩበት ቀንና በዘመናችን ያሉ አይሁዳውያን የፋሲካን በዓል የሚያከብሩበት ቀን ሊለያይ የሚችልበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።

f በጄምስ ሞፋት የተዘጋጀውን ኤ ኒው ትራንስሌሽን ኦቭ ዘ ባይብል፣ በቻርልስ ቢ ዊልያምስ የተዘጋጀውን ዘ ኒው ቴስታመንት—ኤ ትራንስሌሽን ኢን ዘ ላንግዌጅ ኦቭ ዘ ፒፕል እንዲሁም በሂዩ ጄ ሾንፊልድ የተዘጋጀውን ዚ ኦሪጅናል ኒው ቴስታመንት ተመልከት።