ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 18:1-24

  • “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች!” (1-8)

    • ‘ሕዝቤ ሆይ፣ ከእሷ ውጡ’ (4)

  • በባቢሎን ውድቀት ያለቅሳሉ (9-19)

  • ባቢሎን በመውደቋ በሰማይ ደስታ ሆነ (20)

  • ባቢሎን እንደ ድንጋይ ባሕር ውስጥ ትጣላለች (21-24)

18  ከዚህ በኋላ ከፍተኛ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም የተነሳ ምድር በብርሃን ደመቀች።  እሱም በኃይለኛ ድምፅ እንዲህ ሲል ጮኸ፦ “ወደቀች! ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች!+ የአጋንንት መኖሪያ፣ የርኩስ መንፈስ ሁሉ* እንዲሁም የርኩሳንና የተጠሉ ወፎች ሁሉ መሰወሪያ ሆነች!+  ብሔራት ሁሉ የዝሙቷ* የፍትወት* ወይን ጠጅ ሰለባ ሆነዋል፤+ የምድር ነገሥታትም ከእሷ ጋር አመንዝረዋል፤+ የምድር ነጋዴዎችም * ያላንዳች ኀፍረት ባከማቸቻቸው ውድ ነገሮች በልጽገዋል።”  ከሰማይም ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “ሕዝቤ ሆይ፣ የኃጢአቷ ተባባሪ መሆን የማትፈልጉና የሚደርስባት መቅሰፍት ተካፋይ መሆን የማትፈልጉ ከሆነ ከእሷ ውጡ።+  ኃጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ተቆልሏልና፤+ አምላክም የፈጸመቻቸውን ኢፍትሐዊ ድርጊቶች* አስቧል።+  በሌሎች ላይ በፈጸመችው በዚያው መንገድ ብድራቷን መልሱላት፤+ አዎ፣ ለሠራቻቸው ነገሮች እጥፍ ክፈሏት፤+ በቀላቀለችበት ጽዋ+ እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት።+  ለራሷ ክብር የሰጠችውንና ያላንዳች ኀፍረት ውድ ነገሮች በማከማቸት የተቀማጠለችውን ያህል፣ በዚያው ልክ ሥቃይና ሐዘን ስጧት። ሁልጊዜ በልቧ ‘ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ፤ መበለትም አይደለሁም፤ ሐዘንም ፈጽሞ አይደርስብኝም’ ትላለችና።+  መቅሰፍቶቿ ይኸውም ሞትና ሐዘን እንዲሁም ረሃብ በአንድ ቀን የሚመጡባት ለዚህ ነው፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ትቃጠላለች፤+ ምክንያቱም የፈረደባት ይሖዋ* አምላክ ብርቱ ነው።+  “ከእሷ ጋር ያመነዘሩና* ያላንዳች ኀፍረት ከእሷ ጋር በቅንጦት የኖሩ የምድር ነገሥታትም እሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጭስ በሚያዩበት ጊዜ ስለ እሷ ያለቅሳሉ እንዲሁም በሐዘን ደረታቸውን ይደቃሉ። 10  ደግሞም ሥቃይዋን በመፍራት በሩቅ ቆመው ‘አንቺ ታላቂቱ ከተማ፣+ አንቺ ብርቱ የሆንሽው ከተማ ባቢሎን፣ እንዴት ያሳዝናል! እንዴት ያሳዝናል! ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ተፈጽሟልና’ ይላሉ። 11  “የምድር ነጋዴዎችም ከዚህ በኋላ ብዛት ያለውን ሸቀጣቸውን የሚገዛቸው ስለማይኖር ስለ እሷ ያለቅሳሉ እንዲሁም ያዝናሉ፤ 12  ብዛት ያለው ሸቀጣቸውም ወርቅን፣ ብርን፣ የከበሩ ድንጋዮችን፣ ዕንቁን፣ ጥሩ በፍታን፣ ሐምራዊ ጨርቅን፣ ሐርንና ደማቅ ቀይ ጨርቅን ያካተተ ነው፤ በተጨማሪም ጥሩ መዓዛ ካለው እንጨት የተሠራ ነገር ሁሉ፣ ከዝሆን ጥርስ፣ ውድ ከሆነ እንጨት፣ ከመዳብ፣ ከብረትና ከእብነ በረድ የተሠራ ማንኛውም ዓይነት ዕቃ ሁሉ ይገኝበታል፤ 13  ደግሞም ቀረፋ፣ የሕንድ ቅመም፣ ዕጣን፣ ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት፣ ነጭ ዕጣን፣ የወይን ጠጅ፣ የወይራ ዘይት፣ የላመ ዱቄት፣ ስንዴ፣ ከብቶች፣ በጎች፣ ፈረሶች፣ ሠረገላዎች፣ ባሪያዎችና ሰዎች* ይገኙበታል። 14  አዎ፣ የተመኘሽው* ጥሩ ፍሬ ከአንቺ ርቋል፤ ምርጥና ማራኪ የሆኑ ነገሮችም ሁሉ ከአንቺ ጠፍተዋል፤ ዳግመኛም አይገኙም። 15  “እነዚህን ነገሮች በመሸጥ በእሷ የበለጸጉ ነጋዴዎች ሥቃይዋን በመፍራት በሩቅ ቆመው እያለቀሱና እያዘኑ 16  እንዲህ ይላሉ፦ ‘ጥሩ በፍታ፣ ሐምራዊና ደማቅ ቀይ ልብስ የለበሰችው እንዲሁም በወርቅ ጌጣጌጥ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቁዎች የተንቆጠቆጠችው+ ታላቂቱ ከተማ፣ እንዴት ያሳዝናል! እንዴት ያሳዝናል! 17  ምክንያቱም ያ ሁሉ ታላቅ ሀብት በአንድ ሰዓት ውስጥ እንዳልነበረ ሆኗል።’ “የመርከብ አዛዦች ሁሉ፣ በባሕር ላይ የሚጓዙ ሁሉ፣ መርከበኞችና መተዳደሪያቸው በባሕር ላይ የተመሠረተ ሁሉ በሩቅ ቆመው 18  እሷ ስትቃጠል የሚወጣውን ጭስ እያዩ ‘እንደ ታላቂቱ ከተማ ያለ ከተማ የት ይገኛል?’ በማለት ጮኹ። 19  በራሳቸው ላይ አቧራ በትነው እያለቀሱና እያዘኑ እንዲህ ሲሉ ጮኹ፦ ‘በባሕር ላይ መርከቦች ያሏቸውን ሁሉ በሀብቷ ያበለጸገችው ታላቂቱ ከተማ በአንድ ሰዓት ውስጥ መጥፋቷ እንዴት ያሳዝናል! እንዴት ያሳዝናል!’+ 20  “ሰማይ ሆይ፣ በእሷ ላይ በደረሰው ነገር ደስ ይበልህ፤+ ደግሞም እናንተ ቅዱሳን፣+ ሐዋርያትና ነቢያት ደስ ይበላችሁ፤ ምክንያቱም አምላክ ለእናንተ ሲል ፈርዶባታል!”+ 21  አንድ ብርቱ መልአክም ትልቅ የወፍጮ ድንጋይ የሚመስል ድንጋይ አንስቶ ወደ ባሕር በመወርወር እንዲህ አለ፦ “ታላቂቱ ከተማ ባቢሎን እንዲህ በፍጥነት ቁልቁል ትወረወራለች፤ ዳግመኛም አትገኝም።+ 22  በተጨማሪም ራሳቸውን በበገና የሚያጅቡ ዘማሪዎች፣ የሙዚቀኞች፣ የዋሽንት ነፊዎችና የመለከት ነፊዎች ድምፅ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ፈጽሞ አይሰማም። ደግሞም የማንኛውም ዓይነት የእጅ ጥበብ ባለሙያ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይገኝም፤ እንዲሁም የወፍጮ ድምፅ ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም። 23  የመብራት ብርሃን ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይበራም፤ የሙሽራና የሙሽሪት ድምፅም ዳግመኛ በአንቺ ውስጥ ከቶ አይሰማም፤ ይህም የሚሆነው ነጋዴዎችሽ የምድር ታላላቅ ሰዎች ስለነበሩና በመናፍስታዊ ድርጊቶችሽ+ ብሔራት ሁሉ ስለተሳሳቱ ነው። 24  በእሷም ውስጥ የነቢያት፣ የቅዱሳንና+ በምድር ላይ የታረዱ ሰዎች ሁሉ ደም ተገኝቷል።”+

የግርጌ ማስታወሻዎች

“የርኩስ እስትንፋስ ሁሉ፤ ርኩስ የሆነ በመንፈስ የተነገረ ቃል ሁሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ግሪክኛ፣ ፖርኒያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “የቁጣ።”
ወይም “ተጓዥ ነጋዴዎችም።”
ወይም “ወንጀሎች።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
የቃላት መፍቻው ላይ “የፆታ ብልግና” የሚለውን ተመልከት።
ወይም “የሰዎች ነፍስ።”
ወይም “ነፍስሽ የተመኘችው።”