የዮሐንስ ወንጌል 9:1-41

  • ኢየሱስ ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ፈወሰ (1-12)

  • ፈሪሳውያን ዓይኑ የበራለትን ሰው በጥያቄ አፋጠጡት (13-34)

  • የፈሪሳውያን መታወር (35-41)

9  በመንገድ እያለፈ ሳለም ሲወለድ ጀምሮ ዓይነ ስውር የሆነ አንድ ሰው አየ።  ደቀ መዛሙርቱም “ረቢ፣+ ይህ ሰው ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደው ማን በሠራው ኃጢአት ነው? በራሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ?” ሲሉ ጠየቁት።  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እሱም ሆነ ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም፤ ሆኖም ይህ የሆነው የአምላክ ሥራ በእሱ እንዲገለጥ ነው።+  ቀን ሳለ፣ የላከኝን የእሱን ሥራ መሥራት አለብን፤+ ማንም ሊሠራ የማይችልበት ሌሊት ይመጣል።  በዓለም እስካለሁ ድረስ የዓለም ብርሃን ነኝ።”+  ይህን ካለ በኋላ መሬት ላይ እንትፍ በማለት በምራቁ ጭቃ ለወሰ፤ ጭቃውንም በሰውየው ዓይኖች ላይ ቀባ፤+  ሰውየውንም “ሄደህ በሰሊሆም ገንዳ ታጠብ” አለው (ሰሊሆም ማለት “ተላከ” ማለት ነው)። ሰውየውም ሄዶ ታጠበ፤ ዓይኑም በርቶለት መጣ።+  ከዚያም ጎረቤቶቹና ቀደም ሲል ሲለምን ያዩት የነበሩ ሰዎች “ይህ ሰው ተቀምጦ ይለምን የነበረው አይደለም እንዴ?” አሉ።  አንዳንዶች “አዎ፣ እሱ ነው” ሲሉ ሌሎች ደግሞ “አይ፣ እሱን ይመስላል እንጂ እሱ አይደለም” ይሉ ነበር። ሰውየው ግን “እኔው ነኝ” ይል ነበር። 10  በመሆኑም “ታዲያ ዓይኖችህ እንዴት ተከፈቱ?” ሲሉ ጠየቁት። 11  እሱም “ኢየሱስ የተባለው ሰው ጭቃ ለውሶ ዓይኖቼን ቀባና ‘ወደ ሰሊሆም ሄደህ ታጠብ’ አለኝ።+ እኔም ሄጄ ታጠብኩ፤ ዓይኔም በራልኝ” ሲል መለሰ። 12  በዚህ ጊዜ “ሰውየው የት አለ?” አሉት። እሱም “እኔ አላውቅም” አለ። 13  እነሱም ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ወደ ፈሪሳውያን ወሰዱት። 14  እንደ አጋጣሚ ሆኖ ኢየሱስ ጭቃውን የለወሰበትና የሰውየውን ዓይኖች ያበራበት ቀን+ ሰንበት ነበር።+ 15  በዚህ ጊዜ ፈሪሳውያኑም እንዴት ማየት እንደቻለ ጠየቁት። እሱም “ሰውየው ዓይኖቼን ጭቃ ቀባ፤ እኔም ታጠብኩ፤ ከዚያም ማየት ቻልኩ” አላቸው። 16  ከፈሪሳውያንም መካከል አንዳንዶቹ “ይህ ሰው ሰንበትን ስለማያከብር ከአምላክ የመጣ አይደለም” አሉ።+ ሌሎቹ ደግሞ “ኃጢአተኛ የሆነ ሰው እንዲህ ያሉ ተአምራዊ ምልክቶችን እንዴት ሊፈጽም ይችላል?” አሉ።+ በመሆኑም በመካከላቸው ክፍፍል ተፈጠረ።+ 17  በድጋሚም ዓይነ ስውሩን “ይህ ሰው ዓይኖችህን ስላበራልህ ስለ እሱ ምን ትላለህ?” አሉት። ሰውየውም “እሱ ነቢይ ነው” አለ። 18  ይሁን እንጂ አይሁዳውያኑ ማየት የቻለውን ሰው ወላጆች እስከጠሩበት ጊዜ ድረስ ሰውየው ዓይነ ስውር እንደነበረና በኋላ ዓይኑ እንደበራለት አላመኑም ነበር። 19  ወላጆቹንም “ዓይነ ስውር ሆኖ ተወልዷል የምትሉት ልጃችሁ ይህ ነው? ታዲያ አሁን እንዴት ሊያይ ቻለ?” ሲሉ ጠየቋቸው። 20  ወላጆቹም እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ይህ ልጃችን እንደሆነና ዓይነ ስውር ሆኖ እንደተወለደ እናውቃለን። 21  አሁን ግን እንዴት ሊያይ እንደቻለ የምናውቀው ነገር የለም፤ ዓይኖቹን ማን እንዳበራለትም አናውቅም። እሱን ጠይቁት፤ ሙሉ ሰው ነው። ስለ ራሱ መናገር ያለበት እሱ ነው።” 22  ወላጆቹ ይህን ያሉት አይሁዳውያኑን* ስለፈሩ ነው፤+ ምክንያቱም አይሁዳውያን ኢየሱስን፣ ‘ክርስቶስ ነው’ ብሎ የተቀበለ ማንኛውም ሰው ከምኩራብ እንዲባረር አስቀድመው ወስነው ነበር።+ 23  ወላጆቹ “ሙሉ ሰው ነው። እሱን ጠይቁት” ያሉት ለዚህ ነበር። 24  ስለዚህ ዓይነ ስውር የነበረውን ሰው ለሁለተኛ ጊዜ ጠርተው “እውነቱን በመናገር ለአምላክ ክብር ስጥ፤ እኛ ይህ ሰው ኃጢአተኛ መሆኑን እናውቃለን” አሉት። 25  እሱም መልሶ “ኃጢአተኛ ይሁን አይሁን የማውቀው ነገር የለም። እኔ የማውቀው ዓይነ ስውር እንደነበርኩና አሁን ግን ማየት እንደቻልኩ ነው” አለ። 26  በዚህ ጊዜ “ምንድን ነው ያደረገልህ? ዓይንህን ያበራልህስ እንዴት ነው?” አሉት። 27  እሱም “ነገርኳችሁ እኮ፤ እናንተ ግን አትሰሙም። እንደገና መስማት የፈለጋችሁት ለምንድን ነው? እናንተም የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን ፈለጋችሁ እንዴ?” ሲል መለሰላቸው። 28  እነሱም ሰውየውን በንቀት እንዲህ አሉት፦ “የዚያ ሰው ደቀ መዝሙር አንተ ነህ፤ እኛ ግን የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን። 29  አምላክ ሙሴን እንዳነጋገረው እናውቃለን፤ ይህ ሰው ግን ከየት እንደመጣ አናውቅም።” 30  ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ከየት እንደመጣ አለማወቃችሁ በጣም የሚያስገርም ነገር ነው፤ ያም ሆነ ይህ ዓይኖቼን አብርቶልኛል። 31  አምላክ ኃጢአተኞችን እንደማይሰማ እናውቃለን፤+ ፈሪሃ አምላክ ያለውንና ፈቃዱን የሚያደርገውን ሁሉ ግን ይሰማዋል።+ 32  ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዓይኖች የከፈተ አለ ሲባል ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተሰምቶ አይታወቅም። 33  ይህ ሰው ከአምላክ ባይሆን ኖሮ ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልም ነበር።”+ 34  እነሱም መልሰው “አንተ ሁለመናህ በኃጢአት ተበክሎ የተወለድክ! እኛን ልታስተምር ትፈልጋለህ?” አሉት። ከዚያም አባረሩት!+ 35  ኢየሱስም ሰውየውን እንዳባረሩት ሰማ፤ ባገኘውም ጊዜ “በሰው ልጅ ላይ እምነት አለህ?” አለው። 36  ሰውየውም “ጌታዬ፣ አምንበት ዘንድ እሱ ማን ነው?” ሲል መለሰ። 37  ኢየሱስም “አይተኸዋል፤ ደግሞም እያነጋገረህ ያለው እሱ ነው” አለው። 38  እሱም “ጌታ ሆይ፣ በእሱ አምናለሁ” አለ። ከዚያም ሰገደለት።* 39  ኢየሱስም “የማያዩ ማየት እንዲችሉ፣+ የሚያዩም እንዲታወሩ፣+ ለዚህ ፍርድ ወደዚህ ዓለም መጥቻለሁ” አለ። 40  በዚያ የነበሩ ፈሪሳውያንም ይህን ሰምተው “እናንተም ዕውሮች ናችሁ እያልከን ነው?” አሉት። 41  ኢየሱስም “ዕውሮች ብትሆኑማ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባችሁ ነበር። አሁን ግን ‘እናያለን’ ትላላችሁ። ስለዚህ ኃጢአታችሁ እንዳለ ይኖራል” አላቸው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ዮሐ 7:13 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ወይም “እጅ ነሳው።”