አንደኛ ሳሙኤል 1:1-28

  • ሕልቃና እና ሁለቱ ሚስቶቹ (1-8)

  • ልጅ ያልነበራት ሐና፣ ይሖዋ ልጅ እንዲሰጣት ጸለየች (9-18)

  • ሳሙኤል ተወለደ እንዲሁም ለይሖዋ ተሰጠ (19-28)

1  በኤፍሬም+ ተራራማ አካባቢ በምትገኘው በራማታይምጾፊም+ የሚኖር ሕልቃና+ የተባለ አንድ ሰው ነበር፤ ይህ ሰው ኤፍሬማዊ ሲሆን የጹፍ ልጅ፣ የቶሁ ልጅ፣ የኤሊሁ ልጅ፣ የየሮሃም ልጅ ነበር።  እሱም ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ የአንደኛዋ ስም ሐና ሲሆን የሌላኛዋ ደግሞ ፍናና ነበር። ፍናና ልጆች ነበሯት፤ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም።  ያም ሰው አምልኮ ለማቅረብና* ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ መሥዋዕት ለመሠዋት በየዓመቱ ከከተማው ወደ ሴሎ ይወጣ ነበር።+ በዚያም ሁለቱ የኤሊ ልጆች ሆፍኒ እና ፊንሃስ+ ለይሖዋ ካህናት ሆነው ያገለግሉ ነበር።+  አንድ ቀን ሕልቃና መሥዋዕት ሲያቀርብ ለሚስቱ ለፍናና እንዲሁም ለወንዶች ልጆቿና ለሴቶች ልጆቿ በሙሉ ድርሻቸውን ሰጣቸው፤+  ሆኖም ሐናን ይወዳት ስለነበር ልዩ የሆነ ድርሻ ሰጣት፤ ይሁንና ይሖዋ ለሐና ልጅ አልሰጣትም ነበር።*  በተጨማሪም ይሖዋ ልጅ ስላልሰጣት ጣውንቷ እሷን ለማበሳጨት ዘወትር ትሳለቅባት ነበር።  እሷም በየዓመቱ እንዲህ ታደርግባት ነበር፤ ሐና ወደ ይሖዋ ቤት+ በወጣች ቁጥር፣ እስክታለቅስና መብላት እስኪያቅታት ድረስ ጣውንቷ ትሳለቅባት ነበር።  ባሏ ሕልቃና ግን “ሐና፣ ለምን ታለቅሻለሽ? ለምንስ አትበይም? ልብሽስ ለምን ያዝናል? ከአሥር ወንዶች ልጆች እኔ አልበልጥብሽም?” አላት።  ከዚያም ሐና በሴሎ ከበሉና ከጠጡ በኋላ ተነሳች። በዚህ ጊዜ ካህኑ ኤሊ በይሖዋ ቤተ መቅደስ*+ መቃን አጠገብ ወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር። 10  እሷም በጣም ተማርራ* ነበር፤ ስቅስቅ ብላም እያለቀሰች ወደ ይሖዋ ትጸልይ ጀመር።+ 11  እንዲህም ስትል ተሳለች፦ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣ አገልጋይህ እየደረሰባት ያለውን መከራ ተመልክተህ ብታስበኝና አገልጋይህን ሳትረሳት ወንድ ልጅ ብትሰጣት+ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለይሖዋ እሰጠዋለሁ፤ ራሱንም ምላጭ አይነካውም።”+ 12  ሐና በይሖዋ ፊት ለረጅም ሰዓት ስትጸልይ ኤሊ አፏን ይመለከት ነበር። 13  ሐና የምትናገረው በልቧ ነበር፤ በመሆኑም ከንፈሯ ሲንቀጠቀጥ ቢታይም ድምፅዋ አይሰማም ነበር። በመሆኑም ኤሊ የሰከረች መሰለው። 14  ስለዚህ “ስካሩ የማይለቅሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅሽን መጠጣት ተዪ” አላት። 15  ሐናም መልሳ እንዲህ አለች፦ “አልሰከርኩም ጌታዬ! እኔ ብዙ ጭንቀት ያለብኝ ሴት* ነኝ፤ የወይን ጠጅም ሆነ ሌላ የሚያሰክር መጠጥ አልጠጣሁም፤ ይልቅስ ነፍሴን* በይሖዋ ፊት እያፈሰስኩ ነው።+ 16  እኔ እስካሁን ድረስ እየተናገርኩ ያለሁት በውስጤ ካለው ብሶትና ጭንቀት የተነሳ ስለሆነ አገልጋይህን እንደማትረባ ሴት አትቁጠራት።” 17  ከዚያም ኤሊ “በሰላም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ የለመንሽውን ነገር ይስጥሽ” አላት።+ 18  እሷም “አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ታግኝ” አለችው። ከዚያም ተነስታ ሄደች፤ ምግብም በላች፤ ዳግመኛም በፊቷ ላይ ሐዘን አልታየም። 19  እነሱም በማለዳ ተነስተው በይሖዋ ፊት ሰገዱ፤ ከዚያም በራማ+ ወደሚገኘው ቤታቸው ተመለሱ። ሕልቃናም ከሚስቱ ከሐና ጋር የፆታ ግንኙነት ፈጸመ፤ ይሖዋም አሰባት።+ 20  ከዚያም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ* ሐና ፀንሳ ወንድ ልጅ ወለደች፤ እሷም “ከይሖዋ የለመንኩት ነው” በማለት ስሙን+ ሳሙኤል* አለችው። 21  ከጊዜ በኋላም ሕልቃና ለይሖዋ ዓመታዊውን መሥዋዕት ለመሠዋትና+ የስእለት መባውን ለማቅረብ ቤተሰቡን ሁሉ ይዞ ወጣ። 22  ሐና ግን አልወጣችም፤+ ምክንያቱም ለባሏ “ሕፃኑ ጡት እንደጣለ አመጣዋለሁ፤ እሱም ይሖዋ ፊት ይቀርባል፤ ዕድሜውንም ሙሉ በዚያ ይኖራል” በማለት ነግራው ነበር።+ 23  ባሏ ሕልቃናም “መልካም መስሎ የታየሽን አድርጊ። ልጁን ጡት እስክታስጥዪው ድረስ ቤት ሁኚ። ይሖዋም ያልሽውን ይፈጽም” ብሏት ነበር። በመሆኑም ሐና ቤት ተቀመጠች፤ ልጇንም ጡት እስክታስጥለው ድረስ ተንከባከበችው። 24  እሷም ልክ ልጁን ጡት እንዳስጣለችው ከልጁ ጋር የሦስት ዓመት ወይፈን፣ አንድ የኢፍ መስፈሪያ* ዱቄትና አንድ እንስራ የወይን ጠጅ ይዛ ወጣች፤+ ልጁንም በሴሎ+ ወደሚገኘው ወደ ይሖዋ ቤት ይዛው መጣች። 25  እነሱም ወይፈኑን ካረዱ በኋላ ልጁን ወደ ኤሊ አመጡት። 26  እሷም እንዲህ አለች፦ “ጌታዬ ሆይ፣ በሕያውነትህ* እምላለሁ፤ ጌታዬ ሆይ፣ እኔ ወደ ይሖዋ ለመጸለይ ከአንተ ጋር እዚህ ቦታ ቆሜ የነበርኩት ሴት ነኝ።+ 27  ይህን ልጅ እንዲሰጠኝ ጸልዬ ነበር፤ ይሖዋም የለመንኩትን ሰጠኝ።+ 28  እኔ ደግሞ በበኩሌ ልጁን ለይሖዋ እሰጠዋለሁ።* በሕይወት ዘመኑም ሁሉ ለይሖዋ የተሰጠ ይሆናል።” እሱም* በዚያ ለይሖዋ ሰገደ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ለመስገድና።”
ቃል በቃል “ማህፀኗን ዘግቶት ነበር።”
የመገናኛ ድንኳኑን ያመለክታል።
ወይም “በነፍሷ ተመርራ።”
ወይም “መንፈሷ ክፉኛ የተደቆሰባት ሴት።”
“ጊዜው ሲደርስ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“የአምላክ ስም” የሚል ትርጉም አለው።
አንድ ኢፍ 22 ሊትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “በሕያው ነፍስህ።”
በዕብራይስጥ “አውሰዋለሁ።”
ሕልቃናን እንደሚያመለክት ከሁኔታው መረዳት ይቻላል።