በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለውሾቼ የሚበላ ነገር ሰጧቸው

ለውሾቼ የሚበላ ነገር ሰጧቸው

በኦሪገን፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ኒክ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ጊዜው በ2014 መጀመሪያ አካባቢ ነው፤ ሁለት ትናንሽ ውሾቼን በከተማው መሃል አንሸራሽር ነበር። መሃል ከተማ ላይ ብዙውን ጊዜ የጽሑፍ ጋሪ ይዘው የሚቆሙ የይሖዋ ምሥክሮች አገኝ ነበር። ደስ የሚል አለባበስ ያላቸው ሲሆን አላፊ አግዳሚውን በፈገግታ ሰላም ይሉ ነበር።

“እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ለሰዎች ብቻ ሳይሆን ለውሾቼም ደጎች ነበሩ። አንድ ቀን፣ ጋሪው አጠገብ የቆመችው ኢሌን ለውሾቼ የሚበላ ነገር ሰጠቻቸው። ከዚያ በኋላ በዚያ ባለፍን ቁጥር ውሾቹ ምግቧን ፍለጋ ወደ ጋሪው ይጎትቱኝ ጀመር።

“በዚህ ሁኔታ ወራት አለፉ። ውሾቹ የለመዱትን ምግብ ፍለጋ ወደ ጋሪው ይሄዳሉ። እኔ ደግሞ ከእነዚያ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር አጭር ውይይት አደርጋለሁ። ከእነሱ ጋር ብዙ ማውራት ግን አልፈልግም ነበር። ዕድሜዬ ከ70 በላይ ነበር፤ የይሖዋ ምሥክሮች ምን ብለው እንደሚያምኑም ብዙ የማውቀው ነገር አልነበረም። ከዚያ በፊት በሄድኩባቸው ቤተ ክርስቲያኖች ውስጥ ባየሁት ነገር ተስፋ ስለቆረጥኩ መጽሐፍ ቅዱስን በራሴ ለማጥናት ወስኜ ነበር።

“በዚያው ጊዜ አካባቢ በከተማው ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የጽሑፍ ጋሪ ይዘው የሚቆሙ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችም አየሁ። እነሱም ቢሆኑ ባሕርያቸው ደስ ይላል። ለማነሳቸው ጥያቄዎች ሁሉ መልስ የሚሰጡኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ነበር፤ በመሆኑም ይበልጥ እያመንኳቸው መጣሁ።

“አንድ ቀን ኢሌን ‘እንስሳት የአምላክ ስጦታ ናቸው ብለህ ታምናለህ?’ ብላ ጠየቀችኝ። ‘እንዴ፣ በሚገባ!’ ብዬ መለስኩላት። ከዚያም በኢሳይያስ 11:6-9 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ አሳየችኝ። ሐሳቤን እንድቀይር ያደረገኝ አጋጣሚ ይህ ነበር። እንደዚያም ሆኖ ጽሑፋቸውን መቀበል አልፈለግኩም።

“በቀጣዮቹ ቀናት ከኢሌንና ከባለቤቷ ከብሬንት ጋር አጭር ሆኖም ትርጉም ያለው ውይይት አደረግን። እውነተኛ ክርስቲያን መሆን ምን እንደሚጠይቅ መረዳት እንድችል ከማቴዎስ እስከ ሐዋርያት ሥራ እንዳነብ ሐሳብ ሰጡኝ። እኔም እንዳሉኝ አደረግኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ከብሬንትና ከኢሌን ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመርኩ። ይህ የሆነው በ2016 አጋማሽ ላይ ነው።

“በየሳምንቱ የምናደርገውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና በስብሰባ አዳራሹ የሚካሄደውን የጉባኤ ስብሰባ የምጠባበቀው በጉጉት ነበር። እየተማርኩ ያለሁት ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንደሆነ ስለገባኝ በጣም ተደሰትኩ። ከአንድ ዓመት በኋላ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። አሁን 79 ዓመቴ ነው፤ እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘሁ እርግጠኛ ነኝ። ይሖዋ ራሳቸውን የወሰኑ አገልጋዮቹን ባቀፈው ቤተሰብ ውስጥ እንድገባ ስለፈቀደልኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ።”