በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ

ሴሎችህ—ሕያው ቤተ መጻሕፍት!

ሴሎችህ—ሕያው ቤተ መጻሕፍት!

በ1953፣ የሞለኪውል ባዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ጄምስ ዋትሰንና ፍራንሲስ ክሪክ ስለ ሕይወት ባለን ሳይንሳዊ ግንዛቤ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣ አንድ ግኝት ይፋ አደረጉ። ዲ ኤን ኤ ጥንድ የሆነ ጥምዝ ቅርጽ እንዳለው በምርምር ደረሱበት። * በአብዛኛው በሴሎች እንብርት ውስጥ የሚገኘው ይህ ክር መሰል ንጥረ ነገር፣ ኮድ ወይም “የተጻፈ” መረጃ የያዘ ነው፤ ከዚህም የተነሳ ሴሎችን ሕያው ቤተ መጻሕፍት ናቸው ብለን በምሳሌያዊ መንገድ መግለጽ እንችላለን። ይህ አስገራሚ ግኝት በሥነ ሕይወት መስክ አዲስ ዘመን እንዲጠባ አድርጓል! ይሁንና በሴሎች ውስጥ ያለው “ጽሑፍ” ምን አገልግሎት አለው? ከሁሉም በላይ ደግሞ አመራማሪ የሆነው ጥያቄ ‘ጽሑፉ በሴሎቹ ላይ እንዴት ሊሰፍር ቻለ?’ የሚለው ነው።

ሴሎች መረጃ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

አንድ ዘር፣ ዛፍ የሚሆነው ወይም አንድ የዳበረ እንቁላል ሰው የሚሆነው እንዴት እንደሆነ አስበህ ታውቃለህ? ባሕሪህን የወረስከው እንዴት እንደሆነስ ጥያቄ ተፈጥሮብህ ያውቃል? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ዲ ኤን ኤ ውስጥ ከሚገኝ መረጃ ጋር የተያያዘ ነው።

አብዛኞቹ ሴሎች ማለት ይቻላል ዴ ኤን ኤ ይኸውም የተጠማዘዘ ረጅም መሰላል የሚመስሉ ውስብስብ የሆኑ ሞለኪውሎች አላቸው። በሰው ጂኖም (በአካላችን ውስጥ ያለው የተሟላ ዲ ኤን ኤ) ውስጥ የሚገኙት መሰላሎች ወደ ሦስት ቢሊዮን ገደማ የሚሆኑ የኬሚካል “መወጣጫዎች” አሏቸው። እያንዳንዱ መወጣጫ ከሁለት ኬሚካላዊ ንጥረ ነገሮች የተሠራ ስለሆነ የሳይንስ ሊቃውንት እነዚህን መወጣጫዎች ጥንድ ኬሚካሎች ብለው ይጠሯቸዋል፤ የኬሚካሎቹ አጠቃላይ ቁጥር ደግሞ አራት ነው። እነዚህ ንጥረ ነገሮች ኤ፣ ሲ፣ ጂ እና ቲ ተብለው የሚጠሩ ሲሆን ይህን ስም ያገኙት እያንዳንዱ ቃል በእንግሊዝኛ ከሚጠራበት የመጀመሪያ ፊደል ነው። * በ1957 ፍራንሲስ ክሪክ በመስመር የተደረደሩት ኬሚካላዊ መወጣጫዎች በኮድ መልክ የተጻፉ መመሪያዎችን እንደሚያስገኙ ሐሳብ አቅርበው ነበር። በ1960ዎቹ ደግሞ ኮዱ የያዘው ትርጉም በግልጽ መታወቅ ጀመረ።

አንድ መረጃ የተላለፈው በሥዕል፣ በድምፅ ወይም በቃል መልክ ቢሆንም በብዙ መንገዶች ሊቀመጥና ሊተነተን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ኮምፒውተሮች ይህን የሚያደርጉት ሙሉ በሙሉ በዲጂታል መልክ ነው። ሕይወት ያላቸው ሴሎች ግን መረጃን የሚያስቀምጡትና የሚተነትኑት ኬሚካላዊ በሆነ መንገድ ሲሆን ከዚህ ጋር በተያያዘ ዲ ኤን ኤ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። ዲ ኤን ኤ ከአንዱ ሴል ወደ ሌላው የሚተላለፈው ሴሎች ሲከፈሉ እንዲሁም ሕይወት ያላቸው ነገሮች መሰላቸውን ሲያስገኙ ነው። ይህ፣ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ብቻ ያላቸው ችሎታ እንደሆነ ይታመናል።

ታዲያ ሴሎች መረጃውን የሚጠቀሙት እንዴት ነው? ዲ ኤን ኤ የምግብ አሠራር መመሪያዎችን የያዘ መጽሐፍ እንደሆነ አድርገህ አስብ፤ እያንዳንዱ መመሪያ ደረጃ በደረጃ መከናወን ያለበትን ነገር አንድ በአንድ የሚገልጽ ሲሆን እያንዳንዱ ሂደት ደግሞ በጥንቃቄ ተጽፎ ተቀምጧል። ይሁን እንጂ ዲ ኤን ኤ ውስጥ ያለው መመሪያ የሚያስገኘው ኬክ ወይም ብስኩት ሳይሆን ጎመን ወይም ላም ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ሕይወት ባላቸው ሴሎች ውስጥ ሂደቶቹ የሚከናወኑት ሙሉ በሙሉ በራሳቸው ነው፤ ይህም ሂደቱን ውስብስብና የረቀቀ ያደርገዋል።

በባክቴሪያ ሴል ላይ የሚገኘው መረጃ ባለ 1,000 ገጽ መጽሐፍ ይወጣዋል

የጄኔቲክ መረጃ እስከሚፈለግበት ጊዜ ድረስ ተቀምጦ ይቆያል፤ ከዚያም ያረጁ ወይም የተጎዱ ሴሎችን ጤናማ በሆኑ ለመተካት ወይም ለቀጣዩ ዘር መልክና ቁመና ለማስተላለፍ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። ለመሆኑ ዲ ኤን ኤ ምን ያህል መረጃ ይይዛል? በጣም አነስተኛ ፍጥረት የሆነውን አንድ ሴል ያለውን ባክቴሪያ እንውሰድ። ጀርመናዊው የሳይንስ ሊቅ በርንት ኦላፍ ኩፐርስ እንዲህ ብለዋል፦ “በሰው ቋንቋ ሲገለጽ፣ የባክቴሪያ ሴል የሚሠራበትን መንገድ የሚገልጸው ሞለኪውሉ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ ባለ አንድ ሺህ ገጽ መጽሐፍ ሊወጣው ይችላል።” የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዴቪድ ዲመር “አንድ ሰው፣ ሕይወት ካላቸው ነገሮች መካከል እጅግ አነስተኛ የሆነው እንኳ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ ሲገነዘብ በጣም ይገረማል” ሲሉ ጽፈዋል። ታዲያ ስለ ሰው ጂኖም ምን ሊባል ነው? ኩፐርስ “[የሰው ጂኖም] አንድ ቤተ መጻሕፍት ሊሞሉ የሚችሉ በሺህ የሚቆጠሩ ጥራዞችን የመያዝ አቅም አለው” በማለት ተናግረዋል።

“እኛ በሚገባን መንገድ የተጻፈ”

በዲ ኤን ኤ ውስጥ የሰፈረው ጽሑፍ “የሞለኪውል የጄኔቲክ ቋንቋ” ነው የሚለው ስያሜ “እንዲሁ ተምሳሌታዊ ከሆነ አገላለጽ” ያለፈ ትርጉም አለው በማለት ኩፐርስ ተናግረዋል። “ሰዎች በቋንቋቸው ዓረፍተ ነገር እንደሚያዋቅሩ ሁሉ የሞለኪውል የጄኔቲክ ቋንቋም የሚዋቀርበት መንገድ አለ” ሲሉ ገልጸዋል። በአጭር አነጋገር ዲ ኤን ኤ “ሰዋስው” ወይም ደንብ አለው፤ በዚህ አማካኝነት በውስጡ የያዛቸው መመሪያዎች እንዴት እንደሚቀናበሩና ተግባራዊ እንደሚሆኑ በጥብቅ ይቆጣጠራል።

በዲ ኤን ኤ ውስጥ ያሉት “ቃላት” እና “ዓረፍተ ነገሮች” የተለያዩ “የአሠራር መመሪያዎችን” የያዙ ናቸው፤ እነዚህ መመሪያዎች አንድ አካል የሚገነባበትን የተለያዩ ሴሎች ለመሥራት የሚያስፈልጉት ፕሮቲኖችና ሌሎች ንጥረ ነገሮች እንዲዘጋጁ ትእዛዝ ያስተላልፋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ “የአሠራር መመሪያው” የአጥንት ሴሎች፣ የጡንቻ ሴሎች፣ የነርቭ ሴሎች ወይም የቆዳ ሴሎች እንዲዘጋጁ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል። የዝግመተ ለውጥ የሥነ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ሪቻርድ ዶከንዝ “የዲ ኤን ኤ ፈትል መረጃ የያዘ ነው፤ ይህም ማለት በኬሚካል ኮዶች የተጻፈ መልእክት ሲሆን እያንዳንዱ ፊደል በአንድ ኬሚካል ይወከላል” በማለት ጽፈዋል። “ጉዳዩ ለማመን የሚያዳግት ቢሆንም ኮዱ እኛ በሚገባን መንገድ የተጻፈ እንደሆነ ማወቅ ችለናል” ሲሉ ገልጸዋል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ዳዊት ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ፅንስ እያለሁ እንኳ ዓይኖችህ አዩኝ፤ የአካሌ ክፍሎች በሙሉ በመጽሐፍህ ተጻፉ” ብሎ ነበር። (መዝሙር 139:16) እርግጥ ነው፣ ዳዊት የተጠቀመው ቅኔያዊ አነጋገር ቢሆንም የተናገረው ሐሳብ ፍጹም እውነት ነው። ይህ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ዓይነተኛ መለያ ነው። ቀልብ የሚስቡ ተረቶች ወይም ጥንት ይነገሩ የነበሩ አፈ ታሪኮች በትንሹም እንኳ ቢሆን በአንዳቸውም ላይ ተጽዕኖ አላሳደሩም።—2 ሳሙኤል 23:1, 2፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16

አንድ ሕፃን ከወላጆቹ የተለያዩ ባሕርያትን የሚወርሰው እንዴት ነው?

ጽሑፉ እዚያ ላይ እንዴት ሊሰፍር ቻለ?

ብዙውን ጊዜ እንደሚያጋጥመው የሳይንስ ሊቃውንት አንድ ሚስጥር ግልጽ ሲሆንላቸው ሌላ ሚስጥር የሚገለጥበት አጋጣሚ ይከፈታል። ከዲ ኤን ኤ ጋር በተያያዘም ተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጥሯል። ዲ ኤን ኤ በኮድ መልክ የተጻፈ መረጃ እንደያዘ ሲታወቅ አስተዋይ የሆኑ ሰዎች ‘መረጃው እዚያ ላይ እንዴት ሊሰፍር ቻለ?’ የሚል ጥያቄ ተፈጠረባቸው። እርግጥ ነው፣ የመጀመሪያው የዲ ኤን ኤ ሞለኪውል ሲሠራ ያየ ሰው የለም። በመሆኑም የሆነ ድምዳሜ ላይ መድረስ ያለብን እኛ ራሳችን ነን። እንደዚያም ሆኖ በግምት አንድ ድምዳሜ ላይ እንድንደርስ አይጠበቅብንም። ከዚህ በታች በንጽጽር መልክ የቀረቡትን ሐሳቦች ተመልከት።

  • በ1999 ፓኪስታን ውስጥ የማይታወቅ ጽሑፍ ወይም ምልክት የሰፈረባቸው እጅግ ጥንታዊ የሆኑ የሸክላ ስብርባሪዎች ተገኝተው ነበር። ምልክቶቹ ምን ትርጉም እንዳላቸው እስካሁን ድረስ አልታወቀም። ያም ቢሆን ግን አንድ ሰው እንደጻፋቸው ይታመናል።

  • ዋትሰንና ክሪክ፣ ዲ ኤን ኤ እንዴት እንደተዋቀረ ካወቁ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሁለት የፊዚክስ ሊቃውንት ከሕዋ በኮድ መልክ የሚመጡ የሬዲዮ ምልክቶች መኖር አለመኖራቸውን ለማጣራት ሐሳብ አቀረቡ። በመሆኑም ሌሎች ፕላኔቶች ላይ የማስተዋል ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ይኖሩ እንደሆነ የሚደረገው ፍለጋ ተጀመረ።

መልእክቱ ምንድን ነው? አንድ መረጃ በምልክት መልክ በሸክላ ላይ የተጻፈም ይሁን በኮድ መልክ ከሕዋ የተላከ፣ ሰዎች መረጃን የሚያያይዙት ከማስተዋል ችሎታ ጋር ነው። ሰዎች እዚህ መደምደሚያ ላይ ለመድረስ የግድ መረጃው ሲዘጋጅ ማየት አያስፈልጋቸውም። ሆኖም የሰው ልጅ ከደረሰበት መረጃ ሁሉ እጅግ የረቀቀው ማለትም የኬሚካል ውጤት የሆነው የሕይወት ኮድ በታወቀ ጊዜ ብዙዎች፣ መረጃ ካለ ማስተዋል ያለው አካል አለ የሚለውን ሐቅ ገሸሽ አድርገው ዲ ኤን ኤ በድንገት እንደተገኘ መናገር ጀመሩ። ታዲያ ይህ ምክንያታዊ ነው? ደግሞስ ወጥነት ያለው አቋም ነው? ሳይንሳዊስ ነው? አንጋፋ የሆኑ በርካታ የሳይንስ ሊቃውንት ለእነዚህ ጥያቄዎች “አይደለም” የሚል መልስ ይሰጣሉ። ከእነዚህ መካከል ዶክተር ጂን ህዋንግ እና ፕሮፌሰር ያንደ ሱ ይገኙበታል። እስቲ የሰጡትን ሐሳብ እንመልከት።

ዶክተር ጂን ህዋንግ ለጄኔቲክ መሠረት በሆነው የሒሳብ ቀመር ላይ ጥናት ያካሂዳሉ። በአንድ ወቅት በዝግመተ ለውጥ ያምኑ የነበሩ ቢሆንም በምርምር የደረሱባቸው ግኝቶች የአመለካከት ለውጥ እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል። ለንቁ! እንዲህ ብለዋል፦ “የጄኔቲክ ጥናት ስለ ሕይወት አሠራር ጥልቅ ማስተዋል ይሰጣል፤ ይህ ደግሞ ፈጣሪ ባለው ጥበብ በአድናቆት እንድሞላ አድርጎኛል።”

ፕሮፌሰር ያንደ ሱ፣ በታይዋን የሚገኘው ብሔራዊ የፒንግቱንግ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ክፍል ውስጥ የፅንስ ጥናት ዳይሬክተር ናቸው። በአንድ ወቅት እሳቸውም በዝግመተ ለውጥ ያምኑ ነበር፤ ያደረጉት ምርምር ግን ሐሳባቸውን እንዲቀይሩ አነሳስቷቸዋል። ሴል የሚከፋፈልበትንና ለተፈለገው ዓላማ የሚውልበትን መንገድ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦ “ትክክለኛዎቹ የሴል ዓይነቶች በትክክለኛው ቅደም ተከተልና በትክክለኛዎቹ ቦታዎች ላይ መዘጋጀት አለባቸው። በመጀመሪያ ሴሎቹ ተሰባስበው ሕብረ ሕዋሳት ያስገኛሉ፤ ሕብረ ሕዋሳቱ ደግሞ የውስጥ አካል ክፍሎችን እንዲሁም እጅንና እግርን ያስገኛሉ። እንዲህ ላለው ሂደት መመሪያ ስለ መጻፍ ሐሳቡ እንኳ የሚመጣለት የትኛው መሐንዲስ ነው? ሆኖም ለፅንስ አስተዳደግ የሚያስፈልጉት መመሪያዎች እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ዲ ኤን ኤ ውስጥ ተጽፈዋል። ይህ ሁሉ እጅግ በሚገርም ሁኔታ እንደተሠራ ሳስብ ሕይወት የተገኘው ከአምላክ እንደሆነ በእርግጠኝነት እንዳምን አድርጎኛል።”

ጂን ህዋንግ (በስተግራ) እና ያንደ ሱ

ንድፍ አውጪ መኖሩን ማመን ልዩነት ያመጣል?

ጉዳዩን ከፍትሕ አንጻር ካየነው የዚህ ጥያቄ መልስ “እንዴታ!” የሚል ነው። ሕይወት የተገኘው ከአምላክ ከሆነ ምስጋና የሚገባው እሱ እንጂ ዝግመተ ለውጥ አይደለም። (ራእይ 4:11) በተጨማሪም ለጥበቡ ወሰን የሌለው ፈጣሪ የእጅ ሥራዎች ከሆንን የተፈጠርነው በዓላማ ነው ማለት ነው። በአንጻሩ ግን፣ ሕይወት የተገኘው ድንገት በተከሰቱ ሂደቶች ከሆነ ዓላማ ሊኖረው አይችልም። *

በእርግጥም አስተዋይ የሆኑ ሰዎች ለጥያቄዎቻቸው አጥጋቢ መልስ ለማግኘት ይጓጓሉ። የነርቭና የአእምሮ ፕሮፌሰር የሆኑት ቪክቶር ፍራንከል “ሰው የሕይወትን ትርጉም ለመረዳት የሚያደርገው ጥረት በሕይወት ለመኖር የሚያነሳሳው ዋና ምክንያት ነው” በማለት ተናግረዋል። በሌላ አነጋገር መንፈሳዊ ረሃብ ያለን ከመሆኑም ሌላ ይህ ፍላጎታችን እንዲረካ እንፈልጋለን፤ ይህ ረሃብ ትርጉም የሚኖረው በአምላክ የተፈጠርን ከሆነ ብቻ ነው። የአምላክ የእጅ ሥራ ከሆን ታዲያ እሱ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማርካት የምንችልበት ዝግጅት አድርጎልናል?

የዚህን ጥያቄ መልስ ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው ከይሖዋ [ወይም ከአምላክ] አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም” በማለት ከተናገረው ሐሳብ ማግኘት እንችላለን። (ማቴዎስ 4:4) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የይሖዋ ቃል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን መንፈሳዊ ረሃብ በማርካት ሕይወታቸው ትርጉም ያለው እንዲሆን ከማስቻሉም ሌላ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓል። (1 ተሰሎንቄ 2:13) አንተም ከመጽሐፍ ቅዱስ ተመሳሳይ ጥቅም እንድታገኝ ምኞታችን ነው። ሌላው ቢቀር ይህን ልዩ መጽሐፍ ልትመረምረው ይገባል።

^ አን.3 ዋትሰንና ክሪክ ከእነሱ በፊት የነበሩ ተመራማሪዎች ስለ ዲ ኤን ኤ በጻፉት ነገር ላይ ተመሥርተው ተጨማሪ ግኝቶችን ይፋ አድርገዋል፤ ዲኦክሲራይቦኑክሊክ አሲድ በአጭሩ ሲጠራ ዴ ኤን ኤ ይባላል።—“ ዲ ኤን ኤ—ወሳኝ የሆኑ ዓመታት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

^ አን.6 አራቱ ፊደላት የሚወክሉት አደኒን፣ ሳይተሲን፣ ጉዋኒን እና ታይሚን የሚሉትን ስሞች ነው።

^ አን.22 ስለ ፍጥረትና ዝግመተ ለውጥ ለሚነሱ ጥያቄዎች የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች እና ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? በተሰኙት ብሮሹሮች ላይ በሰፊው መልስ ተሰጥቶባቸዋል። ብሮሹሮቹ www.mt711.com/am ላይ ይገኛሉ።