በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአቋሟ ጸንታለች

በአቋሟ ጸንታለች

ሶንግ ሂ የ11 ዓመት ልጅ እያለች እናቷ በልጇ ጀርባ ላይ ያበጠ ነገር እንዳለ አስተዋለች። አንድ ሐኪም፣ ባደረገላት ምርመራ ስኮሊዎሲስ የሚባል በሽታ እንደያዛት አረጋገጠ፤ ይህ በሽታ የአከርካሪ አጥንት ከጎን በኩል ጎብጦ “C” ወይም “S” ቅርጽ እንዲኖረው ያደርጋል። የሶንግ ሂ ሁኔታ በጣም አስጊ ስለነበረ ቀዶ ሕክምና ማድረጓ ግድ ሆነ። ይሁን እንጂ ሶንግ ሂ ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ አይደለችም። “ንቁ!” ያጋጠማትን ነገር በተመለከተ አነጋግሯታል።

መጀመሪያ ላይ በሽታሽ እንደታወቀ ሐኪሞች ሊረዱሽ ችለው ነበር?

ለሦስት ዓመታት ያህል ሁለት ሐኪሞች ክትትል ሲያደርጉልኝ ቆዩ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን አከርካሪዬ ይበልጥ እየጎበጠ ሄደ። እንዲያውም ጉብጠቱ በጣም አስከፊ ደረጃ ላይ በመድረሱ አከርካሪዬ ልቤንና ሳንባዬን መጫን ጀመረ፤ ከዚህም የተነሳ መተንፈስ እየከበደኝ መጣ። በመሆኑም ቀዶ ሕክምና ማድረጌ አይቀሬ ሆነ።

ቀዶ ሕክምናው እንዲደረግልሽ ተስማምተሽ ነበር?

አዎን። ሆኖም ቀዶ ሕክምናው ከባድ እንደሚሆን ተነገረኝ። በዚህ ወቅት የአከርካሪዬ ጉብጠት 116 ዲግሪ ደርሶ ነበር፤ ይህ በጣም መጥፎ የሚባለው ደረጃ ነው። ከእኔ ጋር በተያያዘ ደግሞ ቀዶ ሕክምናውን ይበልጥ ከባድ የሚያደርገው ጉዳይ አለ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተው ሃይማኖታዊ አቋሜ የተነሳ ደም ለመውሰድ ፈቃደኛ አይደለሁም። *

ታዲያ ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ ፈቃደኛ የሆነ ሐኪም አገኘሽ?

እኔና እናቴ በምንኖርበት በፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ አንድ ስፔሻሊስት ጋር ሄድን። ይሁን እንጂ ደም እንደማልወስድ ስነግረው ያለደም እንዲህ ዓይነት ውስብስብ ቀዶ ሕክምና ሊያደርግልኝ የሚችል ሐኪም እንደሌለ ነገረኝ። ከዚህም በላይ ቀዶ ሕክምና ካላደረግኩ 20 ዓመት ሳይሞላኝ ልሞት እንደምችል አስጠነቀቀኝ። በወቅቱ ገና 14 ዓመቴ ነበር።

ይህ አቋምሽ በምን ላይ እንደተመሠረተ አስረድተሽው ነበር?

አዎን። አቋሜ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነና አምላክ የሰውም ሆነ የእንስሳ ደም ቅዱስ ነው ብሎ እንደተናገረ አስረዳሁት። * እንዲያውም አንድ እስራኤላዊ ደም ቢበላ በሞት ይቀጣ እንደነበረ ነገርኩት! * በተጨማሪም የሐዋርያት ሥራ 15:19, 20ን አሳየሁት። ለክርስቲያኖች የተሰጠው ይህ ትእዛዝ “ከደም እንዲርቁ” የሚገልጽ ሐሳብ ይዟል። ይህም ደም በምንም መንገድ ይኸውም በአፍም ሆነ በደም ሥር ወደ ሰው አካል መግባት የለበትም ማለት ነው።

ቀዶ ሐኪሙ ምን ምላሽ ሰጠ?

ሁኔታውን ካስረዳሁት በኋላም ያለደም ቀዶ ሕክምናውን እንደማያደርግ ነገረኝ። በጣም የሚገርመው ሆስፒታሉ ደም የምወስድ ከሆነ ለቀዶ ሕክምናው ምንም ክፍያ እንደማልጠየቅ አሳወቀኝ።

ይህ በጣም ጥሩ አጋጣሚ ነው! ታዲያ አንቺና እናትሽ ምን ወሰናችሁ?

ያለደም ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ ፈቃደኛ የሚሆን ሐኪም የሚገኝ ባይመስልም እንኳ በአቋማችን ለመጽናት ቆርጠን ነበር። ይሁንና ነገሮች ይባስ እየተወሳሰቡ ሄዱ። ከሕግ አንፃር ሲታይ ገና ለአካለ መጠን ያልደረስኩ ልጅ ነበርኩ። በመሆኑም ሁኔታዬ ይባስ አስጊ እየሆነ ስለሄደ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ቀረበ። ደግነቱ የፍሎሪዳ ግዛት አቃቤ ሕግ፣ ያለደም ቀዶ ሕክምና ሊያደርግልኝ የሚችል ሐኪም እንድንፈልግ 30 ቀን ሰጠን።

ታዲያ ሐኪም አገኛችሁ?

አዎን! የአካባቢው የይሖዋ ምሥክሮች የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ባደረገልን ትብብር፣ ኒው ዮርክ ውስጥ ያለደም ቀዶ ሕክምናውን ማድረግ የሚችልና እኔን ለማከም ፈቃደኛ የሆነ አንድ የአከርካሪ አጥንት ስፔሻሊስት አገኘን። ስለዚህ ፍርድ ቤቱ የሰጠን ቀነ ገደብ ከማለፉ በፊት ተሳካልን። *

ቀዶ ሕክምናው እንዴት ነበር?

መቶ በመቶ የተሳካ ነበር! ቀዶ ሕክምና ያደረጉልኝ ዶክተር ሮበርት በርንስታይን የጎበጠውን አከርካሪዬን ለማቃናት እንደ አስፈላጊነቱ መስተካከል የሚችሉ ዘንጎች ጀርባዬ ውስጥ አስገቡልኝ። ቀዶ ሕክምናውን ያከናወኑት በሁለት ደረጃ ከመሆኑም ሌላ በሁለት ሳምንታት ልዩነት ነበር።

በሁለት ደረጃዎች ማከናወን ለምን አስፈለገ?

በመጀመሪያው ቀዶ ሕክምና ላይ ብዙ ደም ከፈሰሰኝ ሁለተኛውን ቀዶ ሕክምና ከማድረጌ በፊት የተወሰነ ጊዜ ማለፉ ሰውነቴ ተጨማሪ ቀይ የደም ሴሎችን እንዲያመርት ጊዜ ስለሚሰጠው ነው። በኋላ እንደታየው በሁለቱም የቀዶ ሕክምና ወቅቶች የፈሰሰኝ ደም በጣም ጥቂት ነበር፤ ይህም ሊሆን የቻለው የቀዶ ሕክምና ቡድኑ ጥሩ ዝግጅት በማድረጉ፣ የላቀ ችሎታ ያለው በመሆኑና ሥራውን በጥንቃቄ በማከናወኑ ነው። በተጨማሪም ደም በመውሰድ ከሚመጡት መዘዞች ነፃ በመሆኔ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ በፍጥነት ማገገም ችያለሁ። *

ቀዶ ሐኪሙ በውጤቱ ምን ተሰማቸው?

ሐኪሞች የሕመምተኛውን ማንነት ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው

በጣም ነው የተደሰቱት! እንዲያውም “የሕክምና እርዳታ መስጠት ማለት ቀዶ ሕክምና የማድረግ ጉዳይ ብቻ አይደለም” ብለዋል። ሐኪሞች የሕመምተኛውን እምነቶችና እሴቶች ጨምሮ የግለሰቡን ማንነት ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው የሚል አመለካከት አላቸው። የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ብዙ ሰዎችም ይህን አመለካከት ሙሉ በሙሉ ይደግፋሉ።

^ አን.7 የሶንግ ሂ እናት የይሖዋ ምሥክር ናት። ሶንግ ሂ የእናቷን እምነት የምትከተል ከመሆኑም ሌላ በ2012 በ16 ዓመቷ ተጠምቃለች።

^ አን.17 የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች፣ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሕመምተኞች ያለደም ጥሩ ሕክምና የሚሰጡ ሐኪሞችን እንዲያገኙ በማፈላለግ እርዳታ ያበረክታሉ።

^ አን.21 የኒው ሳውዝ ዌልስ ሄልዝ (አውስትራሊያ)፣ ክሊኒካል ኤክሰለንስ ኮሚሽን ደም መውሰድ ያለውን አደጋ አስመልክቶ ባወጣው ጽሑፍ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “ደም መስጠት ማለት አንድን የውስጥ አካል በሌላ ሰው ውስጥ መትከል ማለት ነው። ምንጊዜም ቢሆን የሰው አካል ባዕድ የሆነ ነገር ሲገባበት አይቀበልም። ይህ የተፈጥሮ ችሎታ ለጤንነት በጣም አስፈላጊ ነው።”