በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ታይዋን

ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል—ታይዋን

ቹንግ ኬዮን እና ጁሊ የሚባሉ በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኙ ባልና ሚስት የዛሬ አምስት ዓመት ድረስ በሲድኒ፣ አውስትራሊያ የዘወትር አቅኚ ሆነው ያገለግሉ ነበር። ቹንግ ኬዮን “የምንሠራው የተወሰነ ሰዓት ብቻ ሲሆን የተደላደለ ሕይወት እንመራ ነበር” በማለት ይናገራል። “የምንኖርበት አካባቢ የአየር ንብረቱ ደስ የሚል፣ ሕይወት ደግሞ ዘና ያለ ነበር። ከወዳጅ ዘመዶቻችን ጋር አንድ አካባቢ መኖር መቻላችንም ያስደስተን ነበር።” ያም ሆኖ ቹንግ ኬዮንና ጁሊ ቅር የሚላቸው ነገር ነበር። ምን ይሆን? በይሖዋ አገልግሎት የበለጠ ለመሥራት ሁኔታቸው እንደሚፈቅድላቸው ቢያውቁም አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ፈራ ተባ እያሉ ነበር።

ከዚያም በ2009 በተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ የሰሙት ንግግር ልባቸውን በጥልቅ ነካው። ተናጋሪው ያተኮረው አገልግሎታቸውን ማስፋት በሚችሉ ወንድሞችና እህቶች ላይ ነበር። እንዲህ አለ፦ “ይህን ምሳሌ ተመልከቱ። አንድ አሽከርካሪ መኪናውን ወደ ግራ ወይም ወደ ቀኝ ሊጠመዝዝ የሚችለው መኪናው እየተንቀሳቀሰ ከሆነ ብቻ ነው። በተመሳሳይም ኢየሱስ አገልግሎታችንን ልናሰፋ የምንችልበትን መንገድ የሚመራን ቢሆንም ይህን የሚያደርገው ግን የምንንቀሳቀስ ይኸውም ግባችን ላይ ለመድረስ ከልብ ጥረት የምናደርግ ከሆነ ብቻ ነው።” * እነዚህ ባልና ሚስት፣ ተናጋሪው በቀጥታ ለእነሱ እየተናገረ እንደሆነ ተሰማቸው። በታይዋን የሚያገለግሉ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት በዚያው ስብሰባ ላይ ቃለ መጠይቅ ተደርጎላቸው ነበር። እነሱም በአገልግሎቱ ስላገኙት ደስታ የተናገሩ ሲሆን አሁንም በስብከቱ ሥራ ገና ብዙ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ገለጹ። ቹንግ ኬዮንና ጁሊ ይህ ሐሳብም ለእነሱ እንደተነገረ ሆኖ ተሰማቸው።

ጁሊ “ወደ ታይዋን ለመሄድ የሚያስፈልገውን እርምጃ ለመውሰድ ድፍረት እንዲሰጠን ከስብሰባው በኋላ ወደ ይሖዋ ጸለይን” ብላለች። አክላም እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ያም ቢሆን ፈርተን ነበር። ጥልቅ የመዋኛ ገንዳ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘለን ስንገባ የሚሰማን ዓይነት ስሜት ነበረን።” ያሰቡትን ለማድረግ የረዳቸው መክብብ 11:4 ሲሆን ጥቅሱ “ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም፤ ደመናትንም የሚያይ አያጭድም” ይላል። ቹንግ ኬዮን “‘ነፋስን መጠባበቁንና ማየቱን’ ትተን ‘መዝራትና  ማጨድ’ ለመጀመር ወሰንን” ብሏል። ከዚያም ደግመው ደጋግመው ጸለዩ፤ የሚስዮናውያንን የሕይወት ታሪኮች አነበቡ፤ እንዲሁም ቀደም ብለው ወደ ታይዋን ከሄዱ ወንድሞችና እህቶች ጋር ብዙ ኢ-ሜይሎችን ተለዋወጡ፤ በኋላም መኪናቸውንና የቤት ዕቃቸውን ሸጠው ከሦስት ወር በኋላ ወደ ታይዋን ሄዱ።

መስበክ የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም

ከሌሎች አገራት የመጡ ከ100 የሚበልጡ ወንድሞችና እህቶች ታይዋን ውስጥ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች እያገለገሉ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች የመጡት ከስፔን፣ ከብሪታንያ፣ ከአውስትራሊያ፣ ከካናዳ፣ ከኮሪያ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ከጃፓንና ከፈረንሳይ ሲሆን ከ21 እስከ 73 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ። ከእነሱ መካከል ከ50 የሚበልጡ ያላገቡ እህቶች አሉ። እነዚህ ቀናተኛ ወንድሞችና እህቶች አገልግሎታቸውን በሌላ አገር ለማከናወን የረዳቸው ምንድን ነው? እስቲ የሚሉትን እንስማ።

ሎራ

ከካናዳ የመጣች ሎራ የምትባል ያላገባች እህት በምዕራባዊ ታይዋን በአቅኚነት እያገለገለች ነው። ከአሥር ዓመት በፊት ግን የስብከቱን ሥራ አትወደውም ነበር። ሎራ “በአገልግሎት ላይ ብዙ ጊዜ ስለማላሳልፍ አገልግሎቱን ያን ያህል አልወደውም ነበር” በማለት ትናገራለች። በካናዳ የሚኖሩ ጓደኞቿ ለአንድ ወር ወደ ሜክሲኮ ሄደው በዚያ አብረው እንዲሰብኩ ጠየቋት። “በአገልግሎት ላይ ረጅም ጊዜ ሳሳልፍ ይህ የመጀመሪያዬ ነበር፤ አገልግሎቱ ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ ስመለከት ተገረምኩ!” ብላለች።

ሎራ እንዲህ ያለ አስደሳች ጊዜ ማሳለፏ ካናዳ ውስጥ በሌላ አገር ቋንቋ ወደሚካሄድ ጉባኤ ለመዛወር እንድታስብ አነሳሳት። ቻይንኛ መማር ጀመረች፤ ከዚያም በቻይንኛ በሚመራ ቡድን ውስጥ ታገለግል ጀመር፤ እንዲሁም ወደ ታይዋን ለመሄድ ግብ ያወጣች ሲሆን መስከረም 2008 እዚህ ግቧ ላይ መድረስ ችላለች። ሎራ “አዲሱን አካባቢ እስክለምደው ድረስ አንድ ዓመት ገደማ ፈጅቶብኛል፤ አሁን ግን ወደ ካናዳ ተመልሼ ለመሄድ ፈጽሞ አላስብም” ብላለች። ስለ ስብከቱ ሥራ ምን ይሰማታል? “በጣም ደስ ይላል” ትላለች። “መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናቸው ሰዎች ይሖዋን በማወቃቸው ሕይወታቸው እንዴት እንደሚለወጥ ከማየት የበለጠ የሚያረካ ነገር የለም። ታይዋን ውስጥ በማገልገሌ ይህን ከፍተኛ ደስታ ደጋግሜ ለማጣጣም አጋጣሚ አግኝቻለሁ።”

 ቋንቋውን መልመድ

ብራያንና ሚሼል

በ30ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ የሚገኙ ብራያን እና ሚሼል የሚባሉ ባልና ሚስት ከስምንት ዓመት በፊት ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ታይዋን ተዛወሩ። መጀመሪያ ላይ በአገልግሎት ትርጉም ያለው ድርሻ እንደሚያበረክቱ አልተሰማቸውም ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ተሞክሮ ያለው ሚስዮናዊ እንደሚከተለው አላቸው፦ “ለአንድ ሰው ትራክት ብቻ እንኳ ብትሰጡት ያ ሰው ስለ ይሖዋ ሲሰማ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ሊሆን እንደሚችል ማስታወስ ይኖርባችኋል። ስለዚህ በአገልግሎቱ ጠቃሚ ድርሻ እያበረከታችሁ ነው!” ይህ የሚያበረታታ ሐሳብ ብራያንና ሚሼል ተስፋ እንዳይቆርጡ ረድቷቸዋል። አንድ ሌላ ወንድም ደግሞ እንዲህ አላቸው፦ “ቻይንኛ በመማር ረገድ የምታደርጉትን መሻሻል የምትለኩት ትናንትናን ከዛሬ ጋር በማወዳደር ሳይሆን ከአንድ ትልቅ ስብሰባ እስከሚቀጥለው ትልቅ ስብሰባ ምን ያህል ለውጥ እንዳደረጋችሁ በማየት ከሆነ ተስፋ አትቆርጡም።” በእርግጥም ብራያንና ሚሼል ቋንቋውን መልመድ የቻሉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ውጤታማ አቅኚዎች ናቸው።

አንተስ የሌላ አገር ቋንቋ እንድትማር ምን ሊያነሳሳህ ይችላል? ሄደህ ልታገለግልበት የምትፈልገውን ቦታ ወይም አገር ለመጎብኘት ሞክር። እዚያም ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች ሂድ፤ ከአካባቢው ወንድሞችና እህቶች ጋር ጊዜ አሳልፍ፤ እንዲሁም አብረሃቸው አገልግል። ብራያን እንዲህ ይላል፦ “ብዙ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ቀና ምላሽ እንደሚሰጡ ስትመለከቱና የወንድሞችንና የእህቶችን ሞቅ ያለ ፍቅር ስትቀምሱ ተፈታታኝ ሁኔታዎቹን ተቋቁማችሁ በሌላ አገር ለማገልገል ትነሳሳላችሁ።”

መተዳደሪያስ?

ክሪስቲንና ሚሼል

የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ሲሉ ወደ ታይዋን ከሄዱት መካከል አብዛኞቹ በአቅኚነት ለማገልገል እንዲችሉ እንግሊዝኛ በማስተማር ራሳቸውን ያስተዳድራሉ። ክሪስቲን እና ሚሼል ደግሞ ዓሣ ይሸጣሉ። ክሪስቲን “ይህን ሥራ ከዚህ በፊት ሠርቼው ባላውቅም በዚህ አገር ለመቆየት እንድችል ረድቶኛል” በማለት ይናገራል። ከጊዜ በኋላ ክሪስቲን ቋሚ ደንበኞች አገኘ። ለተወሰነ ሰዓት የሚሠራው ይህ ሥራ ራሱንና ሚስቱን ለማስተዳደር ያስችለዋል፤ ከዚህም ሌላ እሱና ሚስቱ በዋነኛው ሥራቸው ይኸውም ሰዎችን ለማጥመድ በሚያስችላቸው የአቅኚነት አገልግሎት ላይ ሰፊ ጊዜ ለማሳለፍ ረድቷቸዋል።

“በጉዞውም ለመደሰት ሞክሩ”

ከዩናይትድ ስቴትስ የመጡ ዊሊያም እና ጄኒፈር የተባሉ ባልና ሚስት ታይዋን የሄዱት ከሰባት ዓመት በፊት ነው። ዊሊያም “ቋንቋውን መማር፣ በአቅኚነት ማገልገል፣ ጉባኤውን መንከባከብና ለመተዳደሪያ የሚሆን ገንዘብ ማግኘት አንዳንድ ጊዜ ጉልበትን የሚያሟጥጥ ነው” ይላል። ታዲያ እነዚህ ባልና ሚስት እንዲሳካላቸውና ደስታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ የረዳቸው ምንድን ነው? ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦችን ለማውጣት ይጥራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ቻይንኛ ሲማሩ ከራሳቸው ብዙ ስላልጠበቁ የሚያደርጉት እድገት አዝጋሚ መሆኑ ተስፋ አላስቆረጣቸውም።

ዊሊያምና ጄኒፈር

ዊሊያም በአንድ ወቅት አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች “ግባችሁ ላይ መድረስ አስደሳች ቢሆንም በጉዞውም ለመደሰት ሞክሩ” ብሎት እንደነበረ ያስታውሳል። በሌላ አባባል፣ አንድ መንፈሳዊ ግብ ካወጣን በኋላ ግባችን ላይ ለመድረስ በምንወስዳቸው እርምጃዎችም መደሰት አለብን። ዊሊያምና ሚስቱ ይህን ምክር በሥራ ላይ ማዋላቸው ግትር እንዳይሆኑ፣ በአካባቢው ያሉ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የሚሰጧቸውን ምክር እንዲያዳምጡና በአዲሱ ክልላቸው በአገልግሎት እንዲሳካላቸው የሚረዱ አንዳንድ ማስተካከያዎች እንዲያደርጉ ረድቷቸዋል። ዊሊያም ስለተሰጣቸው ምክር አክሎ ሲናገር “የተመደብንባት ደሴት ባላት ተፈጥሯዊ ውበት ለመደሰት ጊዜ መመደብ እንዳለብን እንድናስታውስም ረድቶናል” ብሏል።

ሜገን የምትባል ከዩናይትድ ስቴትስ የመጣች ያላገባች አቅኚ እህትም እንደ ዊሊያምና ጄኒፈር ሁሉ ቻይንኛ አቀላጥፋ ለመናገር ያወጣችው ግብ ላይ ለመድረስ በምትጣጣርበት ጊዜ ‘በጉዞዋ እየተደሰተች ነው።’ ሁልጊዜ ቅዳሜና እሁድ ከተወሰኑ አስፋፊዎች ጋር ሆና ማራኪ ወደሆነ የአገልግሎት ክልል ይኸውም የታይዋን ትልቅ ወደብ ወደሆነው ወደ ጋዎሺዮንግ ወደብ ሄደው ይሰብካሉ። ሜገን ከመርከብ ወደ መርከብ እየሄደች ከሕንድ፣ ከባንግላዴሽ፣ ከታይላንድ፣ ከኢንዶኔዥያ፣ ከፊሊፒንስና ከቫኑአቱ ለመጡ ዓሣ አጥማጆች ምሥራቹን መስበክ  ችላለች። እንዲህ ብላለች፦ “ዓሣ አጥማጆቹ በወደቡ የሚቆዩት ለአጭር ጊዜ በመሆኑ እዚያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እናስጀምራቸዋለን። ሁሉንም ለማዳረስ ስል ብዙውን ጊዜ አራት ወይም አምስት ሰዎችን በአንድ ላይ አስጠናለሁ።” ታዲያ ቻይንኛ በመማር ረገድስ ምን ያህል ተሳክቶላታል? እንዲህ ትላለች፦ “በፍጥነት መማር ብችል ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር፤ ይሁን እንጂ አንድ ወንድም ‘የምትችይውን ሁሉ አድርጊ፤ የቀረውን ይሖዋ ያሳካዋል’ በማለት የሰጠኝን ምክር ምንጊዜም ለማስታወስ እጥራለሁ።”

ሜገን

የማያሰጋ፣ ቀላልና አስደሳች

በብሪታኒያ ትኖር የነበረችው ካቲ ወደ ሌላ አገር ከመዛወሯ በፊት፣ ላላገባች እህት የማያሰጋ አገር ለመምረጥ ምርምር አደረገች። የሚያሳስባትን ነገር ጠቅሳ ወደ ይሖዋ የጸለየች ከመሆኑም ሌላ ለብዙ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ደብዳቤ በመጻፍ ላላገቡ እህቶች አስጊ ሁኔታ አለመኖሩን አጣራች። ለደብዳቤዎቿ የተላኩላትን መልሶች በጥንቃቄ በመመርመር ሁኔታውን ካመዛዘነች በኋላ ታይዋን ለእሷ ተስማሚ እንደሚሆን ወሰነች።

ካቲ በ2004 በ31 ዓመቷ ወደ ታይዋን ተዛወረች፤ በዚያም በተቻላት መጠን ቀላል ሕይወት መምራት ጀመረች። እንዲህ ትላለች፦ “ፍራፍሬና አትክልት በአነስተኛ ዋጋ መግዛት የምችለው የት እንደሆነ ወንድሞችንና እህቶችን ጠየቅሁ። እነሱ የሰጡኝ ጥሩ ምክር ገንዘቤን ለማብቃቃት ረድቶኛል።” ሕይወቷን ቀላል ለማድረግ የረዳት ምንድን ነው? ካቲ እንዲህ ትላለች፦ “በአነስተኛ ዋጋ በምገዛው ምግብና ልብስ ረክቼ እንድኖር እንዲረዳኝ ብዙ ጊዜ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። ይሖዋም የሚያስፈልጉኝ ነገሮች ምን እንደሆኑ ለይቼ እንዳውቅና የምመኛቸውን ነገሮች ሁሉ ባላገኝም እንዳላዝን በመርዳት ጸሎቴን እንደመለሰልኝ ይሰማኛል።” አክላም “ቀላል የሆነ ሕይወት መምራቴ በመንፈሳዊ ጉዳዮች ላይ እንዳተኩር ስለሚረዳኝ ደስተኛ ነኝ” ብላለች።

ካቲ

የካቲ ሕይወት ቀላል ብቻ ሳይሆን አስደሳችም ነው። ይህ የሆነበትን ምክንያት እንደሚከተለው በማለት ትገልጻለች፦ “ብዙ ሰዎች ለምሥራቹ ቀና ምላሽ በሚሰጡበት አካባቢ መስበክ ችያለሁ። ይህ ደግሞ በጣም የሚያስደስት ነው!” ካቲ ታይዋን መጥታ በአቅኚነት ማገልገል ስትጀምር በምታገለግልበት ከተማ ውስጥ በቻይንኛ የሚመሩት ጉባኤዎች ሁለት ነበሩ፤ በዛሬው ጊዜ ግን ሰባት ጉባኤዎች አሉ። ካቲ “እንዲህ ያለውን አስገራሚ እድገት በቅርበት ማየቴና አዝመራውን በመሰብሰቡ ሥራ መካፈሌ ሕይወቴ በየዕለቱ በደስታ እንዲሞላ ያደርጋል!” ብላለች።

‘እኔም እንኳ እፈለጋለሁ!’

በመግቢያው ላይ የተጠቀሱት ቹንግ ኬዮን እና ጁሊስ እንዴት ሆኑ? መጀመሪያ ላይ ቹንግ ኬዮን የቻይንኛ ችሎታው ውስን በመሆኑ ጉባኤውን ብዙም መርዳት እንደማይችል ተሰምቶት ነበር። ይሁን እንጂ የአካባቢው ወንድሞች ስሜት ከእሱ የተለየ ነበር። ቹንግ ኬዮን “ጉባኤያችን ተከፍሎ ሁለት ሲሆን የጉባኤ አገልጋይ ስለነበርኩ ብዙ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ተሰጡኝ” ብሏል። “በዚህ ጊዜ፣ በእርግጥ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ እያገለገልኩ እንደሆነ ተሰማኝ። እኔም እንኳ የምፈለግ መሆኑ በጣም አስደሰተኝ!” በማለት ፊቱ በፈገግታ ተሞልቶ ተናግሯል። ቹንግ ኬዮን በአሁኑ ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ እያገለገለ ነው። ጁሊም አክላ እንዲህ ብላለች፦ “ጠቃሚ አገልግሎት እያከናወንን እንደሆነ የሚሰማን ከመሆኑም በላይ እርካታና ደስታ አለን፤ ከዚህ በፊት እንዲህ ተሰምቶን አያውቅም። እዚህ የመጣነው ሌሎችን ለመርዳት ቢሆንም እኛ ራሳችን እርዳታ እንዳገኘን ይሰማናል። ይሖዋ እዚህ እንድናገለግል ስለፈቀደልን እናመሰግነዋለን!”

በብዙ አገሮች በመንፈሳዊው አዝመራ የመሰብሰብ ሥራ አሁንም ተጨማሪ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ። ትምህርትህን ልትጨርስ በመቃረብህ በሕይወትህ ምን ብታደርግ እንደሚሻል እያሰብክ ነው? በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ይበልጥ ጠቃሚ አገልግሎት ለማበርከት የምትፈልግ ያላገባህ ክርስቲያን ነህ? ለቤተሰብህ ታላቅ መንፈሳዊ ውርስ ማውረስ ትፈልጋለህ? ለሌሎች የምታካፍለው ጠቃሚ ተሞክሮ ያካበትህ ጡረታ የወጣህ ክርስቲያን ነህ? የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ በማገልገል አገልግሎትህን ለማስፋት ከወሰንክ ታላላቅ በረከቶች እንደሚጠብቁህ አትጠራጠር።