በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሕይወት ታሪክ

በመንግሥቱ አገልግሎት ያሳለፍኩት ሕይወት

በመንግሥቱ አገልግሎት ያሳለፍኩት ሕይወት

በ1947 በሳንታ አና፣ ኤል ሳልቫዶር የነበሩ የካቶሊክ ቀሳውስት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ዓመፅ ለማነሳሳት ሞክረው ነበር። ወንድሞች ሳምንታዊውን የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እያደረጉ ሳለ አንዳንድ ልጆች በሚስዮናውያኑ ቤት በር በኩል ትላልቅ ድንጋዮችን ወረወሩ። ከዚያም ቀሳውስቱ በርካታ ሰዎችን እየመሩ መጡ። ከሕዝቡ መካከል አንዳንዶቹ ችቦ የያዙ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ምስሎች ይዘው ነበር። ለሁለት ሰዓት ያህል ሕንፃው ላይ ድንጋይ እየወረወሩ “ድንግል ለዘላለም ትኑር!” እና “ይሖዋ ይሙት!” የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ቆዩ። እንዲህ ያደረጉት ሚስዮናውያኑን አስፈራርተው ከከተማዋ ለማስወጣት አስበው ነበር። ይህን ያወቅሁት ከሚስዮናውያኑ አንዷ ስለነበርኩና ከ67 ዓመታት በፊት በተደረገው በዚያ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ስለነበረ ነው። *

ይህ ክስተት ከመፈጸሙ ከሁለት ዓመት በፊት፣ እኔና በሚስዮናዊነት አገልግሎት ጓደኛዬ የሆነችው ኤቭለን ትራበርት በዚያን ጊዜ በኢተካ፣ ኒው ዮርክ ይገኝ ከነበረው ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት አራተኛው ክፍል ተመርቀን ነበር። ከዚያም በሳንታ አና እንድናገለግል ተመድበን ነበር። በሚስዮናዊነት ስላሳለፍኳቸው ወደ 29 የሚጠጉ ዓመታት ከመተረኬ በፊት ግን ሚስዮናዊ ለመሆን ምን እንዳነሳሳኝ ልንገራችሁ።

መንፈሳዊ ውርሻዬ

ወላጆቼ ጆንና ኢቫ ኦልሰን በ1923 እኔን ሲወልዱ የሚኖሩት በስፖካን፣ ዋሽንግተን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነበር። የሉተራን ሃይማኖት ተከታዮች የነበሩ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያኗ ስለ ገሃነመ እሳት የምታስተምረው ነገር አምላክ ፍቅር እንደሆነ ካላቸው እምነት ጋር ስለሚጋጭ አልተቀበሉትም። (1 ዮሐ. 4:8) አባቴ የሚሠራው ዳቦ መጋገሪያ ቤት ውስጥ ነበር፤ አንድ ቀን ምሽት ላይ አንድ የሥራ ባልደረባው መጽሐፍ ቅዱስ ሲኦል መሠቃያ ሥፍራ መሆኑን እንደማያስተምር አረጋገጠለት። ብዙም ሳይቆይ ወላጆቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት የጀመሩ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት ምን እንደሚል ትክክለኛውን ነገር ተማሩ።

በዚያን ጊዜ ገና የዘጠኝ ዓመት ልጅ ብሆንም ወላጆቼ አዲስ ስላገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በስሜት ይናገሩ እንደነበር አስታውሳለሁ። እውነተኛው አምላክ ስሙ ይሖዋ እንደሆነ ሲማሩና አደናጋሪ የሆነው የሥላሴ መሠረት ትምህርት ውሸት  መሆኑን ሲገነዘቡ ደስታቸው ይበልጥ ጨመረ። እኔም ‘ነፃ የሚያወጣውን እውነት’ በመማር እነዚህን ድንቅ ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች ልክ እንደ ስፖንጅ መጠጥኩ። (ዮሐ. 8:32) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት አሰልቺ እንደሆነ ፈጽሞ ተሰምቶኝ አያውቅም፤ ይልቁንም የአምላክን ቃል መመርመር ምንጊዜም ያስደስተኛል። ዓይናፋር የነበርኩ ቢሆንም ከወላጆቼ ጋር በስብከቱ ሥራ እካፈል ነበር። ወላጆቼ በ1934 ተጠመቁ። እኔ ደግሞ በ1939 በ16 ዓመቴ ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።

በ1941 በሴንት ሉዊስ፣ ሚዙሪ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ከእናቴና ከአባቴ ጋር

ሐምሌ 1940 ወላጆቼ ቤታቸውን ሸጡ፤ ከዚያም ሦስታችንም አቅኚዎች በመሆን በኮር ደ ሌን፣ አይዳሆ ውስጥ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርን። እዚያም በአንድ ጋራዥ ፎቅ ላይ የሚገኝ አፓርተማ ተከራይተን እንኖር ነበር። ቤታችን ውስጥ የጉባኤ ስብሰባም ይደረግ ነበር። በዚያን ጊዜ የመንግሥት አዳራሽ ያላቸው ጉባኤዎች ጥቂት በመሆናቸው ወንድሞች የሚሰበሰቡት በግል ቤቶች ወይም በተከራዩአቸው ቤቶች ነበር።

በ1941 እኔና ወላጆቼ በሴንት ሉዊስ፣ ሚዙሪ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘን። እሁድ “የልጆች ቀን” ሲሆን ከ5 እስከ 18 ዓመት ባለው ዕድሜ ውስጥ የምንገኝ ልጆች ከመድረኩ ፊት ለፊት ተቀምጠን ነበር። ወንድም ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ በንግግሩ መደምደሚያ ላይ በዚያ ለነበርነው ልጆች ‘አምላክንና የእሱን ንጉሥ ለመታዘዝ የተስማማችሁ ልጆች በሙሉ እባካችሁ አንድ ጊዜ ተነስታችሁ ቁሙ!’ አለን፤ ከዚያም ሁላችንም ተነስተን ቆምን። ከዚያም ወንድም ራዘርፎርድ “እነሆ! ከ15,000 የሚበልጡ የመንግሥቱ አዳዲስ ምሥክሮች!” በማለት በደስታ ተናገረ። ያ አጋጣሚ አቅኚነት የዕድሜ ልክ ሥራዬ እንዲሆን ያደረግሁትን ውሳኔ ይበልጥ ለማጠናከር ረድቶኛል።

የቤተሰባችን የአገልግሎት ምድቦች

በሴንት ሉዊስ ከተሰበሰብን ከጥቂት ወራት በኋላ ቤተሰባችን ወደ ደቡባዊ ካሊፎርኒያ ተዛወረ። እዚያም በኦክስናርድ ከተማ አዲስ ጉባኤ የማቋቋም ኃላፊነት ተሰጠን። የምንኖረው አንድ አልጋ ብቻ ባላት አነስተኛ ተንቀሳቃሽ ቤት ውስጥ ነበር። ማታ ማታ በምግብ ጠረጴዛችን ላይ “አልጋዬን” አንጥፌ እተኛለሁ፤ ከዚያ በፊት የራሴ መኝታ ክፍል የነበረኝ ከመሆኑ አንጻር ይህ ትልቅ ለውጥ ማድረግ ጠይቆብኛል!

ካሊፎርኒያ ከመድረሳችን ጥቂት ቀደም ብሎ ጃፓን ታኅሣሥ 7, 1941 በሃዋይ በሚገኘው ፐርል ሃርበር ላይ ጥቃት ሰነዘረች። በቀጣዩ ቀን ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ገባች። ባለሥልጣናቱ በሰጡት ትእዛዝ መሠረት ማታ ማታ የከተማዋ ነዋሪዎች በሙሉ መብራት ማጥፋት ነበረባቸው። መብራት እንዲጠፋ የተፈለገው የጃፓን ባሕር ሰርጓጅ መርከቦች በካሊፎርኒያ የባሕር ዳርቻ ይዘዋወሩ ስለነበር ከተማዋ ላይ ጥቃት እንዳይሰነዝሩ ለመከላከል ነው።

ከተወሰኑ ወራት በኋላ ይኸውም መስከረም 1942 በክሌቭላንድ፣ ኦሃዮ በተካሄደው አዲሱ ዓለም በተባለው ቲኦክራሲያዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተን ነበር። እዚያም ወንድም ናታን ሆመር ኖር “ሰላም—ዘላቂ ሊሆን ይችላል?” በሚል ርዕስ የሰጠውን ንግግር አዳመጥን። ወንድም ኖር ራእይ ምዕራፍ 17 ላይ “ከዚህ በፊት ነበር፤ አሁን ግን የለም፤ ይሁንና ከጥልቁ ሊወጣ ነው፤ ወደ ጥፋትም ይሄዳል” ስለተባለለት “አውሬ” አብራራ። (ራእይ 17:8, 11) ወንድም ኖር “አውሬው” በ1939 ሥራውን ማከናወን ያቆመውን የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር እንደሚያመለክት ገለጸ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር በሌላ እንደሚተካና ከዚያ በኋላ በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል። በ1945 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት አበቃ። ከዚያም “አውሬው” የተባበሩት መንግሥታት በሚል ስያሜ በድጋሚ ብቅ አለ። በዚህ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራቸውን በማስፋፋታቸው ከዚያ ወዲህ ታላቅ ጭማሪ ተገኝቷል!

የጊልያድ ዲፕሎማዬ

ይህ ትንቢት ወደፊት ምን እንደሚፈጸም እንዳስተውል ረዳኝ። በቀጣዩ ዓመት የጊልያድ ትምህርት ቤት እንደሚጀምር ማስታወቂያ በተነገረ ጊዜ ሚስዮናዊ የመሆን ፍላጎት አደረብኝ። በ1943 በፖርትላንድ፣ ኦሪገን በአቅኚነት እንዳገለግል  ተመደብኩ። በዚያ ወቅት ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል በሸክላ ማጫወቻ ተጠቅመን ለሰዎች ንግግሮችን እናስደምጣቸው ነበር፤ ከዚያም ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ እንሰጣቸዋለን። በ1943 ዓመቱን ሙሉ፣ ሳስብ የነበረው ስለ ሚስዮናዊነት አገልግሎት ነበር።

በ1944 ከውዷ ጓደኛዬ ከኤቭለን ትራበርት ጋር ወደ ጊልያድ ስንጋበዝ ደስታዬ ወደር አልነበረውም። አምስት ወራት በወሰደው በዚህ ሥልጠና ላይ አስተማሪዎቻችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ደስታ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ አስተማሩን። ትሕትናቸው ያስደንቀን ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሌሎቻችን ምግብ ስንበላ የሚያስተናግዱን አስተማሪዎቻችን ነበሩ። ጥር 22, 1945 ተመረቅን።

የሚስዮናዊነት ምድቤ

እኔና ኤቭለን፣ ከሊዎ እና ኤስተር መሃን ጋር ወደተመደብንባት ወደ ኤል ሳልቫዶር ሰኔ 1946 ሄድን። በዚያም “አዝመራው እንደነጣ” ማለትም ለመሰብሰብ እንደደረሰ ተመለከትን። (ዮሐ. 4:35) በመግቢያው ላይ የጠቀስኩት ክስተት እንደሚያሳየው ቀሳውስቱ በጣም ተቆጥተው ነበር። ይህ ከመሆኑ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በሳንታ አና የመጀመሪያውን ወረዳ ስብሰባ አድርገን ነበር። የሕዝብ ንግግሩን በስፋት ያስተዋወቅን ሲሆን በስብሰባው ላይ 500 የሚያህሉ ሰዎች ሲገኙ በጣም ተደሰትን። ተቃውሞውን በመፍራት ከተማውን ለቅቀን በመውጣት ፈንታ እዚያው ቆይተን ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ለመርዳት ቆረጥን። ቀሳውስቱ፣ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያነቡ ከማስጠንቀቃቸውም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ ለመግዛት አቅሙ የነበራቸው ጥቂቶች ነበሩ፤ ያም ቢሆን ብዙዎች እውነትን ተጠምተው ነበር። ሰዎች፣ ስለ እውነተኛው አምላክ ስለ ይሖዋና ምድርን እንደገና ገነት ለማድረግ ስለሰጠው አስደናቂ ተስፋ እነሱን ለማስተማር ስንል ስፓንኛ ለመማር የምናደርገውን ጥረት ያደንቁ ነበር።

ከጊልያድ ተመርቀን ወደ ኤል ሳልቫዶር የተላክነው አምስት ሚስዮናውያን። ከግራ ወደ ቀኝ፦ ኤቭለን ትራበርት፣ ሚሊ ብራሺየር፣ ኤስተር መሃን፣ እኔ እና ሊዎ መሃን

መጀመሪያ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናኋቸው ሰዎች አንዷ ሮሳ አሴንስዮ ነበረች። ሮሳ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመረች በኋላ፣ አብራው ትኖር ከነበረው ሰው ጋር ተለያየች። ከዚያ እሱም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። በኋላም ተጋቡና ተጠምቀው ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ። ሮሳ በሳንታ አና አቅኚ ከሆኑት የአካባቢው ነዋሪዎች የመጀመሪያዋ ናት። *

ሮሳ አነስተኛ የምግብ መደብር ነበራት። ይሖዋ የሚያስፈልጋትን እንደማያሳጣት በመተማመን አገልግሎት ስትወጣ መደብሯን ትዘጋለች። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ተመልሳ መደብሩን ስትከፍት ደንበኞች በብዛት መጥተው ይገዙ ነበር። የማቴዎስ 6:33ን እውነተኝነት ከራሷ ተሞክሮ ያየች ሲሆን እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ታማኝ ነበረች።

ስድስት ሚስዮናውያን የአንድን ሰው ቤት ተከራይተን እንኖር ነበር፤ በአንድ ወቅት የአካባቢው ቄስ፣ ከቤቱ ካላስወጣን እሱና ሚስቱ በቤተ ክርስቲያን እንደሚወገዙ አከራያችንን አስጠነቀቀው። የቤቱ ባለቤት በንግድ ሥራ የተሰማራ ታዋቂ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው ቀድሞውንም ቢሆን የቀሳውስቱ ምግባር ያናድደው ስለነበረ ለቄሱ ተጽዕኖ እጅ አልሰጠም። እንዲያውም ከቤተ ክርስቲያን ቢባረር ግድ እንደማይሰጠው ለቄሱ ነገረው። ለእኛም እስከፈለግን ጊዜ ድረስ በቤቱ መኖር እንደምንችል ገለጸልን።

አንድ ታዋቂ ሰው የይሖዋ ምሥክር ሆነ

በ1955 የተሠራው ቅርንጫፍ ቢሮ

በዋና ከተማዋ በሳን ሳልቫዶር የሚኖር ባልታሳር ፔርላ የተባለ መሐንዲስ ነበር፤ አንዲት ሚስዮናዊት፣ ባለቤቱን መጽሐፍ  ቅዱስ ታስጠናት ነበር። ጥሩ ልብ ያለው ይህ ሰው የሃይማኖት መሪዎችን ግብዝነት በመመልከቱ በአምላክ ላይ የነበረው እምነት ተሸርሽሮ ነበር። ቅርንጫፍ ቢሮ ለመሥራት ሲታሰብ ባልታሳር ገና ወደ እውነት ባይመጣም እንኳ የሕንፃውን ንድፍና ግንባታውን ያለ ክፍያ ለመሥራት ራሱን በፈቃደኝነት አቀረበ።

ባልታሳር በግንባታ ፕሮጀክቱ ላይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር አብሮ መሥራቱ እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኘ እርግጠኛ እንዲሆን አደረገው። ይህ ሰው ሐምሌ 22, 1955 የተጠመቀ ሲሆን ባለቤቱ ፓውሊና ደግሞ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ተጠመቀች። ሁለቱም ልጆቻቸው ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ነው። ባልታሳር ጁኒየር የሚባለው ልጁ በብሩክሊን ቤቴል ለ49 ዓመታት አገልግሏል፤ በዚያም ሁልጊዜ እየሰፋ ለሚሄደው ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ ድጋፍ በመስጠት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ሲሆን አሁን በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ኮሚቴ ውስጥ ያገለግላል። *

በሳን ሳልቫዶር ትላልቅ ስብሰባዎች ማድረግ በጀመርንበት ጊዜ ወንድም ባልታሳር ፔርላ በአንድ ትልቅ የስፖርት ማዕከል መጠቀም እንድንችል ረድቶናል። መጀመሪያ ላይ በማዕከሉ ውስጥ የተወሰኑ መደዳዎችን ብቻ እንጠቀም ነበር፤ ይሁን እንጂ በይሖዋ በረከት ቁጥራችን በየዓመቱ እየጨመረ በመሄዱ የስፖርት ማዕከሉን መሙላት አልፎ ተርፎም አዳራሹ የማይበቃን ደረጃ ላይ መድረስ ችለናል! በእነዚያ አስደሳች ወቅቶች፣ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናኋቸውን ሰዎች የማየት አጋጣሚ አገኝ ነበር። የቀድሞ ጥናቶቼ “ከልጅ ልጆቼ” ጋር ማለትም እነሱ ካስጠኗቸው አዳዲስ ተጠማቂዎች ጋር ሲያስተዋውቁኝ ምን ያህል እንደምደሰት አስቡት!

ወንድም ፍሬድሪክ ዊልያም ፍራንዝ በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ለተገኘን ሚስዮናውያን ንግግር ሲያቀርብ

በአንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ አንድ ወንድም ወደ እኔ መጣና መናዘዝ የሚፈልገው ነገር እንዳለ ነገረኝ። እኔም ማንነቱን ስላላወቅሁ ምን ሊነግረኝ እንደፈለገ ለማወቅ ጓጓሁ። እሱም “በሳንታ አና እያላችሁ ድንጋይ ከወረወሩባችሁ ልጆች አንዱ እኔ ነኝ” አለኝ። አሁን ግን ይሖዋን አብሮኝ እያገለገለ ነው! ይህን ስሰማ ልቤ በደስታ ተሞላ። ከእሱ ጋር ያደረግሁት ጭውውት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት አንድ ሰው ሊመርጠው ከሚችለው ማንኛውም ሥራ የበለጠ የሚክስ እንደሆነ አረጋግጦልኛል።

በኤል ሳልቫዶር የተካፈልነው የመጀመሪያው የወረዳ ስብሰባ

እርካታ የሚያስገኝ ምርጫ

ወደ 29 ለሚጠጉ ዓመታት በኤል ሳልቫዶር በሚስዮናዊነት አገልግያለሁ፤ መጀመሪያ የተመደብኩት በሳንታ አና ከተማ ሲሆን ከዚያም በሶንሶናቴ ቀጥሎም በሳንታ ቴክላ በመጨረሻም በሳን ሳልቫዶር ሠርቻለሁ። ከዚያ በኋላ ግን ደጋግሜ በመጸለይ ጉዳዩን ብዙ ካሰብኩበት በኋላ በ1975 የሚስዮናዊነት  ምድቤን ትቼ ወደ ስፖካን ለመመለስ ወሰንኩ። ምክንያቱም ታማኝ የሆኑት በዕድሜ የገፉ ወላጆቼ የእኔ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር።

አባቴ በ1979 አረፈ፤ ከዚያም እያደር እየደከመችና ራሷን መርዳት እያቃታት የሄደችውን እናቴን ስንከባከብ ቆየሁ። አባቴ ከሞተ ከስምንት ዓመት በኋላ እናቴ በ94 ዓመት ዕድሜዋ አረፈች። በዚያ አስቸጋሪ ጊዜ እኔም በአካላዊም ሆነ በስሜታዊ ሁኔታ ኃይሌ እየተሟጠጠ ሄደ። ውጥረቱ፣ ሺንግልዝ የተባለ የሚያሠቃይ በሽታ አስከተለብኝ። ይሁን እንጂ ጸሎት እንዲሁም ደግፈው የያዙኝ የይሖዋ አፍቃሪ ክንዶች ያጋጠመኝን ፈተና በጽናት ለመወጣት አስችለውኛል። ይሖዋ “እስከ ሽምግልናችሁ፣ እስከ ሽበትም . . . እሸከማችኋለሁ፤ እደግፋችኋለሁ፤ አድናችኋለሁ” በማለት የገባው ቃል ተፈጽሞልኛል።—ኢሳ. 46:4

በ1990 ወደ ኦማክ፣ ዋሽንግተን ተዛወርኩ። እዚያም በስፓንኛ ቋንቋ ሳገለግል እንደገና ጠቃሚ እንደሆንኩ ተሰማኝ፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ ውስጥ ብዙዎቹ ተጠምቀዋል። ኅዳር 2007 በኦማክ ያለውን ቤቴን መንከባከብ ስላቃተኝ ዋሽንግተን ውስጥ ኦማክ አቅራቢያ በምትገኝ ሸላያን በተባለች ከተማ በአፓርታማ ውስጥ መኖር ጀመርኩ። እዚህ ያለው የስፓንኛ ጉባኤ ከመጣሁበት ጊዜ ጀምሮ በጥሩ ሁኔታ እየተንከባከበኝ ሲሆን ለዚህም እጅግ አመስጋኝ ነኝ። ጉባኤው ውስጥ ያለሁት አረጋዊት እኔ ብቻ ስለሆንኩ ወንድሞችና እህቶች እንደ “አያታቸው” አድርገው በደግነት ይንከባከቡኛል።

‘ልቤ ሳይከፈል’ ትኩረቴን ሙሉ በሙሉ በአገልግሎቱ ላይ ማድረግ እንድችል ስል ላለማግባትና ቤተሰብ ላለመመሥረት የመረጥኩ ቢሆንም ብዙ መንፈሳዊ ልጆች አሉኝ። (1 ቆሮ. 7:34, 35) በአሁኑ ሥርዓት ውስጥ ሊሟላልኝ የሚችለው ሁሉ ነገር እንዳልሆነ አውቃለሁ። በመሆኑም መቅደም ያለባቸውን ነገሮች ለማስቀደም በመወሰን ሕይወቴን ይሖዋን በሙሉ ልብ ለማገልገል አውዬዋለሁ። በአዲሱ ዓለም ውስጥ በሁሉም ዓይነት አስደሳች እንቅስቃሴዎች ለመካፈል በቂ ጊዜ ይኖራል። የምወደው ጥቅስ ይሖዋ ‘የሕያዋን ፍጥረታትን ሁሉ ፍላጎት እንደሚያረካ’ የሚያረጋግጠው መዝሙር 145:16 ነው።

የአቅኚነት አገልግሎት ወጣት እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርገኛል

አሁን 91 ዓመቴ ነው፤ ያም ቢሆን በአንጻራዊ ሁኔታ ጥሩ ጤንነት ስላለኝ በአቅኚነት ማገልገሌን ቀጥያለሁ። የአቅኚነት አገልግሎት ወጣት እንደሆንኩ እንዲሰማኝ የሚያደርገኝ ከመሆኑም ሌላ ዓላማ ያለው ሕይወት እንድመራም ይረዳኛል። መጀመሪያ ወደ ኤል ሳልቫዶር ስመጣ የስብከቱ ሥራ ገና መጀመሩ ነበር። በዚህች አገር የሰይጣን ተቃውሞ አሁንም ባያባራም በአሁኑ ወቅት ከ39,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች አሉ። ይህም እምነቴን አጠናክሮታል። ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት፣ ሕዝቦቹ የሚያደርጉትን ጥረት እየደገፈው እንደሆነ ጥርጥር የለውም!

^ አን.4 የ1981 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 45-46 ተመልከት።

^ አን.19 የ1981 የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 41-42

^ አን.24 የ1981 የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 66-67, 74-75