በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ምንድን ነው?

ለሁሉም ሰው የሚሆን ምሥራች

ለሁሉም ሰው የሚሆን ምሥራች

ኢየሱስ ከሞት መነሳቱ ደቀ መዛሙርቱ ጽኑ እምነትና ቅንዓት እንዲኖራቸው አድርጓል። በተለይም ሐዋርያው ጳውሎስ በትንሹ እስያና በሜድትራንያን አካባቢ በሙሉ የተጓዘ ሲሆን ጉባኤዎችን አደራጅቷል፤ እንዲሁም ክርስቲያኖች የሚደርስባቸውን ጫና እና ኃይለኛ ተቃውሞ በጽናት እንዲቋቋሙ አጠናክሯቸዋል። ክርስቲያኖች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሟቸውም ቁጥራቸው እየበዛ ሄደ።

ጳውሎስ ራሱ ወህኒ ወርዶ ነበር። ሆኖም እስር ቤት እያለም ለክርስቲያን ጉባኤዎች ማበረታቻና ምክር የያዙ ደብዳቤዎችን ይጽፍ ነበር። ጳውሎስ፣ በወቅቱ ከነበረው ችግር የከፋ አደጋ እንደሚመጣ ይኸውም ክህደት እንደሚነሳ አስጠንቅቋቸዋል። “ጠማማ ነገር” የሚናገሩ “ጨካኝ ተኩላዎች” በክርስቲያኖች መካከል እንደሚገቡና “ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ” እንደሚሞክሩ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ትንቢት ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30

በአንደኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ ይህ ክህደት ጀምሮ ነበር። በዚያው ጊዜ አካባቢ፣ ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በምሳሌያዊ መንገድ የሚገልጽ ራእይ አሳየው። ዮሐንስ በዚያን ጊዜ እንደጻፈው፣ ተቃዋሚዎችም ሆኑ ሐሰተኛ አስተማሪዎች አምላክ ለምድርና ለሰው ዘር ያለውን ዓላማ ሙሉ በሙሉ እንዳይፈጽም ሊያግዱት አይችሉም። ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸው ምሥራች “ለብሔር፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለሕዝብ ሁሉ” ይሰበካል። (ራእይ 14:6) ምድር እንደገና ገነት ትሆናለች፤ የአምላክን ፈቃድ መፈጸም የሚፈልግ ሁሉ በገነት ላይ መኖር ይችላል!

ይህ ሐሳብ “ምሥራች” እንደሆነ ይሰማሃል? ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን አምላክ ለሰው ዘር የሰጠውን መልእክት እንዲሁም ይህ መልእክት ዛሬም ሆነ ወደፊት የሚጠቅምህ እንዴት እንደሆነ መርምር።

መጽሐፍ ቅዱስን www.mt711.com በተሰኘው ድረ ገጽ ላይ 50 በሚያህሉ ቋንቋዎች ማንበብ ትችላለህ። በዚሁ ድረ ገጽ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ—የያዘው መልእክት ምንድን ነው? እና ከአምላክ የተላከ ምሥራች! የተሰኙትን ብሮሹሮች እንዲሁም ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ማንበብ ትችላለህ፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል የምንችልበትን ምክንያት እንዲሁም ይህ መጽሐፍ የያዛቸውን ጠቃሚ ምክሮች በቤተሰብና በግል ሕይወታችን በሥራ ላይ ማዋል የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ ሌሎች ጽሑፎችም በዚህ ድረ ገጽ ላይ ይገኛሉ። አሊያም ደግሞ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱን በማነጋገር ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ትችላለህ።

በሐዋርያት ሥራ፣ በኤፌሶን፣ በፊልጵስዩስ፣ በቆላስይስ፣ በፊልሞና፣ በ1 ዮሐንስ እና በራእይ መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ