በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በከባድ የአየር ሁኔታዎች የተነሳ ለችግር ስትዳረግ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳህ ይችላል?

በከባድ የአየር ሁኔታዎች የተነሳ ለችግር ስትዳረግ መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳህ ይችላል?

 በዓለማችን ላይ እየተከሰተ ያለው ከባድ የአየር ሁኔታ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለችግር ዳርጓል። አንተስ እንዲህ ያለ ችግር አጋጥሞሃል? እንዲህ ዓይነቱ የአየር ሁኔታ የተለያዩ ዓይነት የተፈጥሮ አደጋዎችን ሊያስከትል ይችላል። እንደ ሃሪኬን፣ ታይፉን፣ ሳይክሎን እና ቶርኔዶ ያሉ አውሎ ነፋሶች አብዛኛውን ጊዜ የጎርፍ መጥለቅለቅ እንዲከሰት ወይም በባሕር ዳርቻ ያሉ አካባቢዎች በማዕበል እንዲመቱ ሊያደርጉ ይችላሉ። ከባድ ዝናብ የመሬት መንሸራተት ያስከትላል፤ በዚህ ወቅት የሚከሰተው መብረቅ ደግሞ አውዳሚ የሆነ ሰደድ እሳት የሚያስነሳበት ጊዜ አለ። የአየር ጠባይ ለውጥን ተከትሎ የሚመጣው ድርቅ እንዲሁም ከባድ ሙቀት ወይም ቅዝቃዜ የሚያስከትለው ጉዳትም ቀላል አይደለም።

 በብዙ የዓለማችን ክፍሎች አውዳሚ የሆነ የአየር ሁኔታ የሚከሰትበት ፍጥነትም ሆነ የሚያስከትለው ጉዳት እየጨመረ ነው። የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ማኅበራት ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን ሪፖርት እንዳደረገው “በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ለችግር የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው።” አክሎም ሪፖርቱ እንዲህ ብሏል፦ “እንደ ከባድ ዝናብ፣ ጎርፍና ድርቅ ያሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸው ለሰዎች ሕይወት መቀጠፍና ለብዙዎች ኑሮ መመሰቃቀል ምክንያት ሆኗል፤ በእነዚህ አደጋዎች የተነሳ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው ይፈናቀላሉ።”

 የተፈጥሮ አደጋዎች በሰዎች ላይ አካላዊ ብቻ ሳይሆን ስሜታዊ ጉዳትም ያስከትላሉ። ብዙዎች ቤት ንብረታቸውን ማጣታቸው አልፎ ተርፎም የሚወዱትን ሰው በሞት መነጠቃቸው ካስከተለባቸው የስሜት ቀውስ ጋር መታገል ያስፈልጋቸዋል።

 አንተም ከባድ በሆነ የአየር ሁኔታ ምክንያት ለችግር ተዳርገህ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ያጋጠመህን ችግር እንድትወጣ ሊረዳህ ይችላል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ማጽናኛ፣ ተስፋና ጠቃሚ ምክር እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያጋጠማቸውን በርካታ ሰዎች ረድቷል። (ሮም 15:4) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በብዙዎች አእምሮ ውስጥ ለሚጉላላ ወሳኝ ጥያቄ መልስ ይሰጣል፦ አምላክ እንዲህ ያለ ነገር እንዲከሰት የፈቀደው ለምንድን ነው? ለኃጢአታችን እየቀጣን ነው?

በዛሬው ጊዜ እየተከሰተ ያለው ከባድ የአየር ሁኔታ የአምላክ ቅጣት አይደለም

 መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራ ተጠያቂው አምላክ እንዳልሆነ ያስተምራል። ‘አምላክ በክፉ ነገር ሊፈተን አይችልም፤ እሱ ራሱም ማንንም በክፉ ነገር አይፈትንም’ የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ያዕቆብ 1:13) በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ሰዎች በከባድ የአየር ሁኔታ እንዲሠቃዩ እያደረገ ያለው አምላክ አይደለም።

 እርግጥ አምላክ ክፉ ሰዎችን ለመቅጣት የተፈጥሮ ኃይሎችን እንደተጠቀመ የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች አሉ። ሆኖም እነዚህ ክስተቶች በዛሬው ጊዜ ከምናያቸው አውዳሚ የሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች ፈጽሞ የተለዩ ናቸው፤ በዛሬው ጊዜ የሚከሰቱት የተፈጥሮ አደጋዎች ድንገተኛ ከመሆናቸውም ሌላ በጥሩም ሆነ በመጥፎ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደርሳሉ። አምላክ የተፈጥሮ ኃይሎችን ተጠቅሞ ክፉዎችን በሚቀጣበት ጊዜ ግን ጥሩ ለሆኑ ሰዎች ጥበቃ እንደሚያደርግ፣ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጥና እንዲህ ያለ እርምጃ የሚወስድበትን ምክንያት እንደሚገልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ በኖኅ ዘመን በመላዋ ምድር ላይ የጥፋት ውኃ አምጥቶ ነበር። በዚህ ወቅት እንዲህ ያለ እርምጃ የሚወስድበትን ምክንያት ገልጿል፤ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፤ እንዲሁም ለኖኅና ለቤተሰቡ ጥበቃ አድርጓል።—ዘፍጥረት 6:13፤ 2 ጴጥሮስ 2:5

 በዛሬው ጊዜ እየተከሰቱ ያሉት የተፈጥሮ አደጋዎች የአምላክ ቅጣት እንዳልሆኑ የሚያሳይ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ተፈጥሮ አደጋዎች ምን ይላል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

አምላክ በከባድ የአየር ሁኔታ ምክንያት ችግር ለደረሰባቸው ሰዎች ያስባል

 መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ a አምላክ ለሰዎች እንደሚያስብና ስሜታቸውን እንደሚረዳ ይናገራል። እስቲ የሚከተሉትን የሚያጽናኑ ጥቅሶች ተመልከት፦

  •   ኢሳይያስ 63:9 “በጭንቃቸው ሁሉ [አምላክ] ተጨነቀ።”

     ትርጉሙ፦ ይሖዋ ችግር የደረሰባቸውን ሰዎች ጭንቀት ሲያይ በጣም ያዝናል።

  •   1 ጴጥሮስ 5:7 “እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”

     ትርጉሙ፦ ይሖዋ አንተ ያለህበት ሁኔታ ከልብ ያሳስበዋል።

 ይሖዋ ለሰዎች ያለው አሳቢነትና ርኅራኄ እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው ጠቃሚ ምክር አማካኝነት ያጽናናናል፤ እንዲሁም ወደፊት የተፈጥሮ አደጋ የሌለበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚገልጽ አስተማማኝ ተስፋ ሰጥቶናል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

በከባድ የአየር ሁኔታ የተነሳ ለችግር የማንዳረግበት ጊዜ

 ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን” እንደሚሰጠን ቃል ገብቷል። (ኤርምያስ 29:11) የአምላክ ዓላማ ሰዎች በአየር ሁኔታ የተነሳ ስጋት ሳያድርባቸው ገነት በሆነች ምድር ላይ በደስታ እንዲኖሩ ነው።—ዘፍጥረት 1:28፤ 2:15፤ ኢሳይያስ 32:18

 አምላክ፣ ኢየሱስ በሚገዛው ሰማያዊ መንግሥቱ አማካኝነት ይህ ዓላማው እንዲፈጸም ያደርጋል። (ማቴዎስ 6:10) ኢየሱስ የተፈጥሮ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ለመከላከል ጥበቡም ሆነ ኃይሉ አለው። ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ የአየሩን ጠባይ ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይል እንዳለው አሳይቷል። (ማቴዎስ 6:10) ኢየሱስ በጥበብና በማስተዋል ይገዛል፤ የሰው ልጆች አካባቢያቸውን እንዲንከባከቡና ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው እንዲኖሩ ያስተምራል። (ኢሳይያስ 11:2) በኢየሱስ አገዛዝ ሥር ሰዎች በከባድ የአየር ሁኔታ የተነሳ ለችግር አይዳረጉም።

 ይሁንና “ኢየሱስ ኃይሉን ተጠቅሞ የአየሩን ሁኔታ የሚቆጣጠረው መቼ ነው?” ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። የዚህን ጥያቄ መልስ ለማወቅ “የአምላክ መንግሥት ምድርን የሚገዛው መቼ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

አሁን ማድረግ የምትችለው ነገር

 የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር የተፈጥሮ አደጋ ከመከሰቱ በፊት፣ በሚከሰትበት ወቅትና ከዚያ በኋላ ምን ማድረግ እንደምትችል ይጠቁምሃል።

  •   ከመከሰቱ በፊት፦ አፋጣኝ እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅ።

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።”—ምሳሌ 22:3

     ትርጉሙ፦ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድና ቤተሰብህን ከአደጋ መጠበቅ እንድትችል አንተ ባለህበት አካባቢ ምን ዓይነት አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል አስቀድመህ አስብ።

     እውነተኛ ታሪክ፦ “ሰደድ እሳቱ በተከሰተበት ዕለት እኛ አስቀድመን ተዘጋጅተን ነበር። አደጋ ሲከሰት ይዘን የምንወጣውን ቦርሳ አዘጋጅተን ነበር። መድኃኒታችንንም ሆነ ልብሳችንን ቀደም ብለን አስገብተናል። በዙሪያችን ያሉት ሰዎች በጣም ከመደናገጣቸው የተነሳ ምን እንደሚያደርጉ ግራ ገብቷቸው ነበር። እኛ ግን የሚያስፈልገንን ሁሉ አስቀድመን ማዘጋጀታችን በጣም ጠቅሞናል!”—ታማራ፣ ካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

  •   በሚከሰትበት ወቅት፦ ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ ትኩረት አድርግ።

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ንብረቱ ሕይወት ሊያስገኝለት አይችልም።”—ሉቃስ 12:15

     ትርጉሙ፦ ሕይወት ከንብረት ይበልጣል።

     እውነተኛ ታሪክ፦ “ላዊን b የተባለው አውሎ ነፋስ ቤታችንን ባወደመበት ጊዜ ምን እንደማደርግ ግራ ገብቶኝ ነበር። ግን ወደ ይሖዋ አምላክ አጥብቄ ጸለይኩ። ያጣነው ሕይወታችንን ሳይሆን ቁሳዊ ነገሮች እንደሆነ ማስተዋል ችያለሁ።”—ሌስሊ፣ ፊሊፒንስ

  •   ከተከሰተ በኋላ፦ የዛሬን ብቻ አስብ፤ ስለ ነገ አትጨነቅ።

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት።”—ማቴዎስ 6:34

     ትርጉሙ፦ ወደፊት ሊያጋጥሙህ ስለሚችሉ ነገሮች ከልክ በላይ አትጨነቅ።

     እውነተኛ ታሪክ፦ “ኧርማ በተባለው ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ የተነሳ ቤቴ በጎርፍ ከተጥለቀለቀ በኋላ በጣም ብዙ ውሳኔዎችን ማድረግ ነበረብኝ፤ ይህም በጣም አስጨንቆኝ ነበር። ‘ስለ ነገ አትጨነቁ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አደረግኩ። በይሖዋ እርዳታ ከማስበው በላይ ብዙ ነገሮችን መወጣት እንደምችል አስተውያለሁ።”—ሳሊ፣ ፍሎሪዳ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

 ተጨማሪ ምክሮችን ለማግኘት “አደጋ ሲደርስ ሕይወት ለማዳን የሚያስችሉ እርምጃዎች” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

a ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው።—መዝሙር 83:18

b ይህ አውሎ ነፋስ ሃይማ ተብሎም ይጠራል።