በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

መንፈሳዊነት ምንድን ነው? መንፈሳዊ ለመሆን የግድ የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን ያስፈልገኛል?

መንፈሳዊነት ምንድን ነው? መንፈሳዊ ለመሆን የግድ የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን ያስፈልገኛል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተሠራበት መንገድ መረዳት እንደምንችለው፣ መንፈሳዊነት ማለት አምላክን ለማስደሰት ከልብ መፈለግና መነሳሳት እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ ማዳበር ማለት ነው። መንፈሳዊ ሰው በአምላክ መሥፈርቶች መሠረት ለመኖር እና የቅዱስ መንፈሱን አመራር ለመከተል ጥረት ያደርጋል። aሮም 8:5፤ ኤፌሶን 5:1

 ብዙውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊነትን ለማብራራት በንጽጽር ይጠቀማል። ለምሳሌ ከመንፈሳዊ ሰው በተቃራኒ “ዓለማዊ ሰው . . . ከአምላክ መንፈስ የሆኑትን ነገሮች [ወይም የአምላክን ትምህርቶች] አይቀበልም።” (1 ቆሮንቶስ 2:14-16) ከመንፈሳዊ ሰዎች በተቃራኒ ሥጋዊ ሰዎች ከልግስና እና ከሰላም ይልቅ “ቅናትና ጠብ” ይቀናቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 3:1-3) ስም አጥፊ የሆኑና በንግግራቸው የልብ ጓደኛሞችን የሚለያዩ ሰዎች “የእንስሳ ባሕርይ ያላቸውና መንፈሳዊ ያልሆኑ” ተብለዋል።—ይሁዳ 19፤ ምሳሌ 16:28 b

በዚህ ርዕስ ውስጥ፦

 መንፈሳዊ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

 መንፈሳዊነት በአምላክ መልክ በመፈጠራችን ያገኘነው ችሎታ ነው። (ዘፍጥረት 1:27) አብዛኞቹ ሰዎች በዓይን ለማይታዩና ለማይዳሰሱ ነገሮች ከፍ ያለ ግምት የሚሰጡት ወይም ስለ እነዚህ ነገሮች ለማወቅ የሚፈልጉት ለዚህ ነው።

 በተፈጥሯችን ይሖዋ c አምላክ ያሉትን እንደ ሰላም፣ ምሕረትና ፍትሐዊነት የመሳሰሉ ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ አለን። (ያዕቆብ 3:17) በተጨማሪም አምላክ እሱን የሚታዘዙ ሰዎችን መንፈሳዊነታቸውን እንዲያሳድጉ ይረዳቸዋል።—የሐዋርያት ሥራ 5:32

 መንፈሳዊነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

 መንፈሳዊነት “ሕይወትና ሰላም” ያስገኛል። (ሮም 8:6) ከአምላክ የሚገኙት እነዚህ ስጦታዎች ከምንም ነገር በላይ ውድ ናቸው።

  •   ሕይወት፦ አምላክ መንፈሳዊ ለሆኑ ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል።—ዮሐንስ 17:3፤ ገላትያ 6:8

  •   ሰላም፦ ይህ ከአምላክ ጋር የሚኖረን ሰላም ነው። በሥጋዊ ፍላጎታቸው ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ሰዎች የአምላክ ጠላቶች ናቸው። (ሮም 8:7) አምላክ መንፈሳዊነታቸውን ለማሳደግ የሚጥሩ ሰዎችን “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ [የሆነውን] የአምላክ ሰላም” በመስጠት ይባርካቸዋል። (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) እንዲህ ያለው ውስጣዊ ሰላም ደግሞ በሕይወታቸው ደስተኛ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።—ማቴዎስ 5:3

 መንፈሳዊነቴን ማሳደግ የምችለው እንዴት ነው?

  •   የአምላክን ትእዛዛት ተማር እንዲሁም አክብር። መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብህ ይህን ለማድረግ ይረዳሃል። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት “በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው” ስለሆነ የአምላክን ሐሳብ የያዘ መጽሐፍ ነው። (2 ጴጥሮስ 1:21) ከመጽሐፍ ቅዱስ የምትማረው ነገር አምላክን “በመንፈስና በእውነት” ለማምለክ ይረዳሃል፤ ይኸውም የመንፈስ ቅዱስን አመራር ለማግኘትና ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ያስችልሃል።—ዮሐንስ 4:24

  •   የአምላክን እርዳታ ለማግኘት ጸልይ። (ሉቃስ 11:13) አምላክ አንድ መንፈሳዊ ሰው የሚታወቅባቸውን ባሕርያት እንድታዳብር ይረዳሃል። (ገላትያ 5:22, 23) በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ችግሮች ለመወጣት የሚያስችል ጥበብም ይሰጥሃል።—ያዕቆብ 1:5

  •   መንፈሳዊ ከሆኑ ሰዎች ጋር ጊዜ አሳልፍ። እንዲህ ያሉት ሰዎች መንፈሳዊነትህን እንድታሳድግ ያበረታቱሃል። (ሮም 1:11, 12) ከአምላክ ጋር የሚጋጭ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ግን መንፈሳዊነትህን ያዳክምብሃል።—ያዕቆብ 4:4

 መንፈሳዊ ለመሆን የግድ የአንድ ሃይማኖት አባል መሆን ያስፈልገኛል?

 አንድ ሰው ሃይማኖት ስላለው ብቻ መንፈሳዊ ነው ማለት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ሃይማኖተኛ እንደሆነ ቢያስብም እንኳ አንደበቱን የማይገታ ከሆነ ይህ ሰው የገዛ ልቡን ያታልላል፤ አምልኮውም ከንቱ ነው።”—ያዕቆብ 1:26 የግርጌ ማስታወሻ

 ያም ቢሆን መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች አምላክን እሱ በሚቀበለው መንገድ እንደሚያመልኩት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። መንፈሳዊ የሆኑ ሰዎች “አንድ መንፈስ” ብቻ እንዳለ እሱም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንደሆነ አምነው ይቀበላሉ። ይህ መንፈስ አምላክን እንደ “አንድ አካል” ሆነው እንዲያመልኩት ያነሳሳቸዋል፤ ይህም “አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት [በመጠበቅ]” አምላክን እንደ አንድ ቡድን ሆነው እንደሚያመልኩት የሚያሳይ ነው።—ኤፌሶን 4:1-4

 ስለ መንፈሳዊነት የሚነገሩ የተሳሳቱ ሐሳቦች

 የተሳሳተ ሐሳብ፦ ራስን ለማብቃት ወይም እምቅ ችሎታን ለማውጣት የሚደረግ ማንኛውም ጥረት መንፈሳዊነት ነው።

 እውነታው፦ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት መንፈሳዊነት፣ በአምላክ አስተሳሰብ ሕይወትን መምራት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ያለአምላክ እገዛ የተሻለ ሰው ለመሆን የሚደረግ ጥረትን አያበረታታም። መንፈሳዊ ሰዎች እርካታ የሚያገኙት ይሖዋን ፈጣሪያቸው አድርገው በመቀበልና ከእሱ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር ነው።—መዝሙር 100:3

 የተሳሳተ ሐሳብ፦ መንፈሳዊ ሰው መሆን የሚቻለው የምናኔ ሕይወት በመኖር ወይም ራስን በማሠቃየት ነው።

 እውነታው፦ የራስን ሰውነት ማሠቃየት ‘በገዛ ፈቃድ የሚቀርብ አምልኮ’ ተብሏል፤ ይህ አንድ ሰው ሥጋዊ አስተሳሰብ እንዳለው የሚያሳይ ነው። (ቆላስይስ 2:18, 23) መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ሕይወትን የሚያያይዘው ከደስታ ጋር እንጂ ከሥቃይ ጋር አይደለም።—ምሳሌ 10:22

 የተሳሳተ ሐሳብ፦ መናፍስታዊ ድርጊቶችን ጨምሮ ከመንፈሳዊ ዓለም ጋር ለመገናኘት የሚደረግ ማንኛውም ጥረት መንፈሳዊነትን ያሳድጋል።

 እውነታው፦ ከመናፍስታዊ ድርጊቶች አንዱ ከሞቱ ሰዎች መንፈስ ጋር ለመነጋገር የሚደረግ ጥረት ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የሞቱ ሰዎች ምንም ነገር እንደማያውቁ ያስተምራል። (መክብብ 9:5) እንደ እውነቱ ከሆነ መናፍስታዊ ድርጊት የሚያገናኘው አምላክን ከሚቃወሙ መንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር ነው። መናፍስታዊ ድርጊት አምላክን የሚያስቆጣ ከመሆኑም ሌላ አንድ ሰው መንፈሳዊ እንዳይሆን እንቅፋት ይፈጥራል።—ዘሌዋውያን 20:6፤ ዘዳግም 18:11, 12

 የተሳሳተ ሐሳብ፦ ሁሉም ፍጥረታት በውስጣቸው መንፈሳዊነት አለ።

 እውነታው፦ አምላክ የፈጠራቸው ነገሮች በሙሉ ለእሱ ክብር ያመጣሉ። (መዝሙር 145:10፤ ሮም 1:20) መንፈሳዊነት ሊኖራቸው የሚችሉት ግን ማሰብ የሚችሉ ፍጥረታት ብቻ ናቸው። በአንጻሩ እንስሳት የሚመሩት በደመ ነፍስ ስለሆነ ከአምላክ ጋር ወዳጅነት መመሥረት አይችሉም። በአብዛኛው ድርጊታቸውን የሚመራው ለሰውነታቸው የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት የሚያደርጉት ጥረት ነው። (2 ጴጥሮስ 2:12) መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊነት፣ ከእንስሳዊ አስተሳሰብና ባሕርይ ጋር እንደሚቃረን የሚገልጸው ለዚህ ነው።—ያዕቆብ 3:15፤ ይሁዳ 19

a መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “መንፈስ” ተብለው የተተረጎሙት ቃላት መሠረታዊ ትርጉም “ትንፋሽ” ነው። እነዚህ ቃላት፣ በዓይን ባይታይም ኃይሉና እንቅስቃሴው በማስረጃ የተደገፈ ነገርንም ሊያመለክቱ ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ መንፈስ እንደሆነ ይናገራል፤ ከሁሉ የላቀና የራሱ ማንነት ያለው መንፈስ ነው። መንፈሳዊ ሰው የሚባለው የአምላክን ፈቃድ ለማድረግና በአምላክ ቅዱስ መንፈስ ለመመራት የሚመርጥ ሰው ነው።

b መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ሥጋዊ” እና “ዓለማዊ” ሰዎች የተባሉት ሥጋዊ ፍላጎታቸውን ስለማርካት ብቻ የሚያስቡ እንዲሁም ለዚህ ብቻ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፤ እነዚህ ሰዎች ለአምላክ መሥፈርቶች ግድ የላቸውም።

c መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክ ስም ይሖዋ ነው።—መዝሙር 83:18