በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው?

ሰዎች የሚሞቱት ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 በተለይ የቅርብ ወዳጆቻችንን በሞት ስናጣ ሰዎች ለምን እንደሚሞቱ መጠየቃችን የተለመደ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሞት የሚያስከትለው መንደፊያ ኃጢአት ነው” ይላል።​—1 ቆሮንቶስ 15:56

ሁሉም ሰዎች ኃጢአተኛ የሆኑትና የሚሞቱት ለምንድን ነው?

 የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የሆኑት አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ኃጢአት በመሥራታቸው ምክንያት ሞተዋል። (ዘፍጥረት 3:17-19) አምላክ “የሕይወት ምንጭ” በመሆኑ በእሱ ላይ ማመፅ ሞት ማስከተሉ ሳይታለም የተፈታ ነው።​—መዝሙር 36:9፤ ዘፍጥረት 2:17

 አዳም የነበረበትን ኃጢአት ለዘሮቹ በሙሉ አስተላልፏል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ።” (ሮም 5:12) ሁሉም ሰዎች የሚሞቱት ኃጢአተኞች በመሆናቸው ነው።​—ሮም 3:23

ሞት የሚወገደው እንዴት ነው?

 አምላክ ‘ሞትን ለዘላለም የሚውጥበት’ ጊዜ እንደሚመጣ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 25:8) ሞትን ለማስወገድ ግን መጀመሪያ ምንጩን ማለትም ኃጢአትን ማጥፋት ያስፈልገዋል። አምላክ ይህን የሚያደርገው ‘የዓለምን ኃጢአት በሚያስወግደው’ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ነው።​—ዮሐንስ 1:29፤ 1 ዮሐንስ 1:7