በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የጤና እክል ቢኖርባትም ለሌሎች አሳቢነት ታሳያለች

የጤና እክል ቢኖርባትም ለሌሎች አሳቢነት ታሳያለች

 በብራዚል የምትኖረው ማሪያ ሉሲያ አሸርስ ሲንድሮም የተባለ በሽታ አለባት። ይህ በዘር የሚተላለፍ በሽታ ያለባቸው ብዙ ሰዎች መስማት የተሳናቸው ናቸው ወይም የመስማት ችግር ያጋጥማቸዋል፤ በተጨማሪም የማየት ችሎታቸው ቀስ በቀስ እየተዳከመ ይሄዳል። ማሪያ ሉሲያ ስትወለድ ጀምሮ መስማት የተሳናት ነበረች። በልጅነቷ የምልክት ቋንቋ ተምራለች። ዕድሜዋ 30 ዓመት ገደማ ሲሆን ደግሞ የማየት ችሎታዋ እያሽቆለቆለ መጣ። ማሪያ ሉሲያ ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩባትም ራሷን አላገለለችም። አሁን ዕድሜዋ ከ70 ዓመት በላይ ሆኗል፤ ሆኖም ሕይወቷ ትርጉም ያለውና አስደሳች ነው።

 ማሪያ ሉሲያ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የተገናኘችው የማየት ችሎታዋ ማሽቆልቆል ከመጀመሩ በፊት በ1977 ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “አድሪያኖ ከተባለ አብሮኝ የተማረ ልጅ ጋር ተገናኘሁ፤ በወቅቱ አድሪያኖ የይሖዋ ምሥክር ሆኖ ነበር። አምላክ ምድርን ገነት ለማድረግ ቃል እንደገባና በዚያም ሁሉም ሰው ፍጹም ጤንነት እንደሚኖረው ነገረኝ። የነገረኝ ነገር በጣም ስላስደሰተኝ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማሁ። ብዙም ሳይቆይ ሪዮ ዴ ጄኔሮ ውስጥ በሚገኝ አንድ ጉባኤ መሰብሰብ ጀመርኩ። የስብሰባው የተወሰኑ ክፍሎች ወደ ምልክት ቋንቋ ይተረጎሙ ነበር። በይሖዋ እርዳታ መንፈሳዊ እድገት አድርጌ ሐምሌ 1978 ተጠመቅኩ።”

 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ማሪያ ሉሲያ ጉባኤ ቀየረች፤ በአዲሱ ጉባኤዋ ውስጥ ምልክት ቋንቋ የሚችል አንድም ሰው አልነበረም። ስብሰባውን መረዳት ስለማትችል መጀመሪያ ላይ ሁኔታው ተፈታታኝ ሆኖባት ነበር። ሆኖም ሁለት እህቶች ረዷት። በስብሰባ ላይ አጠገቧ ተቀምጠው የሚባለውን ነገር ወረቀት ላይ ይጽፉላት ነበር። ማሪያ ሉሲያ እንዲህ ብላለች፦ “ቤት ስገባ የጻፉልኝን ማስታወሻ ደጋግሜ በማንበብ ሐሳቡን ለመረዳት እሞክራለሁ። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ሁለት እህቶች የምልክት ቋንቋ ተምረው አስተርጓሚዎቼ ሆኑ።”

 የማሪያ ሉሲያ የማየት ችሎታ እያሽቆለቆለ ሲሄድ አስተርጓሚዎቿ የሚጠቀሙበትን ምልክት ማየት ከባድ እየሆነባት ሄደ። በመሆኑም ከሌሎች ጋር ለመግባባት የእጅ ለእጅ ምልክት ቋንቋ መጠቀም ጀመረች። እሱ ደግሞ ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “የሚያስተረጉምልኝን ሰው እጅ እይዛለሁ። በዚህ መንገድ አስተርጓሚዬ የሚጠቀምበትን ምልክት መረዳት እችላለሁ።”

 ማሪያ ሉሲያ አስተርጓሚዎቿ ለሚያደርጉላት እርዳታ አመስጋኝ ነች። እንዲህ ብላለች፦ “ከይሖዋ ያገኘኋቸው ውድ ስጦታዎች ናቸው። በእነሱ እርዳታ ከጉባኤ፣ ከወረዳና ከክልል ስብሰባዎች ጥቅም ማግኘት ችያለሁ።”

 ማሪያ ሉሲያ በአገልግሎት አዘውትራ ትካፈላለች። የእጅ ለእጅ ምልክት ቋንቋን በመጠቀም መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ትሰብካለች፤ እነሱም ምሥራቹን ለእነሱ ለመስበክ በምታደርገው ጥረት በእጅጉ ይደነቃሉ። በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ማሪያ ሉሲያ በወንድሟ እርዳታ፣ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች በርካታ ደብዳቤዎችን ጽፋለች፤ ዦዜ አንቶኒዮ የተባለው ወንድሟ ማየትና መስማት የተሳነው ነው። a

 ይሁንና ደብዳቤ የምትጽፈው እንዴት ነው? እንዲህ ብላለች፦ “የL ቅርጽ ያለው ጠፍጣፋ ፕላስቲክ እጠቀማለሁ። ይህ መሣሪያ ቀጥ ባለ መስመር ለመጻፍና አንቀጽ በአንቀጽ ለመጻፍ ይረዳኛል። ዦዜ አንቶኒዮ አስደናቂ የማስታወስ ችሎታ አለው። በደብዳቤዎቹ ውስጥ የማካትታቸውን ርዕሰ ጉዳዮችና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይመርጣል። መስማት የተሳናቸው ሰዎች መረዳት በሚችሉት መንገድ ለመጻፍ ጥረት አደርጋለሁ። ብዙዎቹ መስማት የተሳናቸው ሰዎች የጽሑፍ ቋንቋን መረዳት ይከብዳቸዋል።”

 ማሪያ ሉሲያ አሁን የማየት ችሎታዋን ሙሉ በሙሉ ብታጣም በጣም ታታሪ ሴት ነች። ካሮላይን የተባለች አስተርጓሚዋ እንዲህ ብላለች፦ “ማሪያ ሉሲያ የቤት ውስጥ ሥራዋን በሙሉ የምታከናውነው ራሷ ነች፤ ቤቷ በጣም ንጹሕ ነው። ምግብ አብስላ ጓደኞቿን መጋበዝ ትወዳለች።”

 በማሪያ ሉሲያ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ጄፈርሰን እንዲህ ብሏል፦ “ማሪያ ሉሲያ ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር አላት። ሰዎችንም ትወዳለች። ሁልጊዜ ሌሎችን ለመርዳት ጥረት ታደርጋለች። የራሷን ጥቅም መሥዋዕት የምታደርግ እህት ነች።”—ፊልጵስዩስ 2:4

a ዦዜ አንቶኒዮ የይሖዋ ምሥክር የሆነው ከማሪያ ሉሲያ በኋላ ነው፤ በ2003 ተጠመቀ። ልክ እንደ ማሪያ ሉሲያ እሱም ሲወለድ ጀምሮ መስማት የተሳነው ነበር፤ ውሎ አድሮም የማየት ችሎታውን አጣ።