መዝሙር 30:1-12

  • ሐዘን ወደ ደስታ ተለወጠ

    • ‘አምላክ ሞገስ የሚያሳየው ለዕድሜ ልክ ነው’ (5)

ማህሌት። ለቤቱ ምረቃ የተዘመረ የዳዊት መዝሙር። 30  ይሖዋ ሆይ፣ ወደ ላይ ስላነሳኸኝ* ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ጠላቶቼ በእኔ ሥቃይ እንዲደሰቱ አልፈቀድክም።+   ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ እርዳታ ለማግኘት ወደ አንተ ጮኽኩ፤ አንተም ፈወስከኝ።+   ይሖዋ ሆይ፣ ከመቃብር* አውጥተኸኛል።*+ በሕይወት አቆይተኸኛል፤ ወደ ጉድጓድ* ከመውረድ አድነኸኛል።+   እናንተ የእሱ ታማኝ አገልጋዮች፣ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ፤+ለቅዱስ ስሙ*+ ምስጋና አቅርቡ፤   ምክንያቱም የሚቆጣው ለአጭር ጊዜ ነው፤+ሞገስ የሚያሳየው* ግን ለዕድሜ ልክ ነው።+ ማታ ለቅሶ ቢሆንም ጠዋት ግን እልልታ ይሆናል።+   በተረጋጋሁ ጊዜ “ፈጽሞ አልናወጥም”* አልኩ።   ይሖዋ ሆይ፣ ሞገስ ባሳየኸኝ ጊዜ እንደ ተራራ አጠነከርከኝ።+ ፊትህን በሰወርክ ጊዜ ግን ተሸበርኩ።+   ይሖዋ ሆይ፣ ወደ አንተ ደጋግሜ ተጣራሁ፤+ሞገስ ለማግኘትም ይሖዋን አብዝቼ ተማጸንኩ።   መሞቴና* ወደ ጉድጓድ* መውረዴ+ ምን የሚያስገኘው ጥቅም አለ? አፈር ያወድስሃል?+ የአንተንስ ታማኝነት ይናገራል?+ 10  ይሖዋ ሆይ፣ ስማኝ፤ ሞገስም አሳየኝ።+ ይሖዋ ሆይ፣ ረዳቴ ሁን።+ 11  ሐዘኔን ወደ ጭፈራ ለወጥክ፤ማቄን አውልቀህ ደስታን አለበስከኝ፤ 12  ይህም እኔ* ዝም ከማለት ይልቅ ለአንተ የውዳሴ መዝሙር እዘምር ዘንድ ነው። ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ ለዘላለም አወድስሃለሁ።

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “ስላወጣኸኝ።”
ወይም “ከሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ነፍሴን ከመቃብር አውጥተሃታል።”
ወይም “መቃብር።”
ቃል በቃል “ለቅዱስ መታሰቢያው።”
ወይም “በጎ ፈቃድ የሚያሳየው።”
ወይም “ፈጽሞ አልንገዳገድም (አልውተረተርም)።”
ቃል በቃል “ደሜና።”
ወይም “መቃብር።”
ወይም “ክብሬ።”