በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነት በማዳበር ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ አድርጉ!

እምነት በማዳበር ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ አድርጉ!

“ምንም ሳይጠራጠር በእምነት መለመኑን ይቀጥል።”—ያዕ. 1:6

መዝሙሮች፦ 118, 35

1. ቃየን የተሳሳተ ውሳኔ እንዲያደርግ ተጽዕኖ ያሳደረበት ምንድን ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?

ቃየን ሁለት ምርጫዎች ከፊቱ ተደቅነውበት ነበር፦ አንድም የኃጢአት ዝንባሌውን መቆጣጠር አሊያም በስሜት ተገፋፍቶ እርምጃ መውሰድ። የሚያደርገው ውሳኔ ምንም ይሁን ምን በቀሪ ሕይወቱ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። ቃየን ምን ዓይነት ውሳኔ እንዳደረገ እናውቃለን፤ ምርጫው ጥሩ አልነበረም። ያደረገው ውሳኔና በዚያ ላይ ተመሥርቶ የወሰደው እርምጃ የወንድሙ የአቤል ሕይወት እንዲቀጠፍ ምክንያት ሆኗል። የቃየን ውሳኔ ከፈጣሪው ጋር የነበረውን ዝምድና እንዲያጣም አድርጎታል።—ዘፍ. 4:3-16

2. ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

2 በተመሳሳይ ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ የተለያዩ ምርጫዎችንና ውሳኔዎችን ማድረግ ይኖርብናል። ሁሉም ውሳኔዎቻችን የሕይወትና የሞት ጉዳይ ናቸው ማለት ላይሆን ይችላል። ይሁንና የምናደርጋቸው ብዙዎቹ ምርጫዎች ወይም ውሳኔዎች በሕይወታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ጥሩ ውሳኔዎችን ካደረግን በአንጻራዊ ሁኔታ የተረጋጋና ሰላማዊ ሕይወት መኖር እንችላለን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የተሳሳቱ ውሳኔዎች ካደረግን ሕይወታችን በችግርና በብስጭት የተሞላ ሊሆን ይችላል።—ምሳሌ 14:8

3. (ሀ) ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል? በአምላክ ላይ እምነት ሊኖረን ይኸውም ጥበበኞች እንድንሆን እኛን ለመርዳት ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው እንዳለው ልንተማመን ይገባል። በተጨማሪም በይሖዋ ቃልና ነገሮችን በሚያከናውንበት መንገድ ላይ እምነት ማዳበር አለብን፤ በሌላ አባባል በመንፈሱ መሪነት ባስጻፈው ቃሉ ውስጥ በሚገኘው ምክር መተማመን ይኖርብናል። (ያዕቆብ 1:5-8ን አንብብ።) ወደ እሱ እየቀረብንና ለቃሉ ያለን ፍቅር እየጨመረ ሲሄድ እሱ በሚሰጠን ምክር ይበልጥ እንተማመናለን። በመሆኑም ውሳኔዎችን ከማድረጋችን በፊት የአምላክን ቃል የመመርመር ልማድ እናዳብራለን። ይሁን እንጂ ውሳኔ የማድረግ ችሎታችንን ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው? ደግሞስ አንድ ጊዜ ውሳኔ ካደረግን ምንም ሆነ ምን ውሳኔያችንን መቀየር የለብንም ማለት ነው?

ውሳኔ ማድረግ የማይቀር ነገር ነው

4. አዳም ምን ውሳኔ ማድረግ ነበረበት? ውሳኔውስ ምን ውጤት አስከትሏል?

4 የሰው ልጆች ከተፈጠሩበት ጊዜ አንስቶ ከባድ ውሳኔዎችን የማድረግ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። ለምሳሌ አዳም፣ ፈጣሪውን አሊያም ሔዋንን ከመስማት አንዱን መምረጥ ነበረበት። አዳም ውሳኔ አድርጓል፤ ሆኖም ያደረገው ውሳኔ ጥበብ የተንጸባረቀበት ይመስልሃል? አዳም፣ የተታለለችው ሚስቱ ባሳደረችበት ተጽዕኖ በመሸነፉ መጥፎ ውሳኔ አድርጓል፤ ይህም በገነት ውስጥ የመኖር አጋጣሚውን አልፎ ተርፎም ሕይወቱን አሳጥቶታል። አዳም ያደረገው የተሳሳተ ውሳኔ ያስከተለው መዘዝ በዚህ አላበቃም። ውሳኔው ያስከተለው ጣጣ ለእኛም ተርፏል።

5. ውሳኔ ማድረግን በተመለከተ ምን ሊሰማን ይገባል?

5 አንዳንዶች፣ ውሳኔ ማድረግ ባይኖርብን ኖሮ ሕይወት ይበልጥ አስደሳች ሊሆን እንደሚችል ያስቡ ይሆናል። አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል? ይሖዋ ሰዎችን የፈጠራቸው ማሰብና መምረጥ እንደማይችሉ ሮቦቶች አድርጎ እንዳልሆነ አስታውስ። አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ እንድንችል ይረዳናል። ይሖዋ ውሳኔ የማድረግ ኃላፊነት የሰጠን ለእኛው ጥቅም ነው። ይህን የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

6, 7. የጥንቶቹ እስራኤላውያን ምን ዓይነት ምርጫ ተደቅኖባቸው ነበር? ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ማድረግ የከበዳቸው ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

6 የጥንቶቹ እስራኤላውያን በተስፋይቱ ምድር መኖር ከጀመሩ በኋላ፣ መሠረታዊና አስፈላጊ የሆነ አንድ ውሳኔ ማድረግ ነበረባቸው፤ ይሖዋን ከማምለክና ሌሎች አማልክትን ከመከተል አንዱን መምረጥ ነበረባቸው። (ኢያሱ 24:15ን አንብብ።) ይህ ቀላል ውሳኔ ይመስል ይሆናል። ሆኖም የሚያደርጉት ውሳኔ ሕይወት ሊያስገኝ አሊያም ሞት ሊያስከትል ይችላል። እስራኤላውያን በመሳፍንት ይተዳደሩ በነበሩበት ዘመን በተደጋጋሚ ጊዜ ጥበብ የጎደለው ውሳኔ ያደርጉ ነበር። ይሖዋን በመተው የሐሰት አማልክትን አምልከዋል። (መሳ. 2:3, 11-23) ከተወሰነ ጊዜ በኋላም የአምላክ ሕዝቦች ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። ነቢዩ ኤልያስ የነበራቸውን ምርጫ በግልጽ አስቀምጦላቸዋል፦ ይሖዋን አሊያም ደግሞ ባአል የተባለውን የሐሰት አምላክ ከማገልገል አንዱን መምረጥ ነበረባቸው። (1 ነገ. 18:21) እስራኤላውያን ይወላውሉ ስለነበር ኤልያስ ወቅሷቸዋል። ሕዝቡ የተደቀነባቸው ውሳኔ ቀላል እንደነበር ታስብ ይሆናል፤ ምክንያቱም ይሖዋን ማገልገል ምንጊዜም ቢሆን ጠቃሚና ጥበብ የሚንጸባረቅበት አካሄድ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። በእርግጥም አስተዋይ የሆነ ማንኛውም ሰው ባአልን ለማምለክ ሊመርጥ አይችልም። እስራኤላውያን ግን “በሁለት ሐሳብ [እያነከሱ]” ነበር። ኤልያስ ከሁሉ የላቀውን አምልኮ ይኸውም የይሖዋን አምልኮ እንዲመርጡ አጥብቆ አሳስቧቸዋል።

7 እስራኤላውያን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ ያን ያህል የከበዳቸው ለምን ሊሆን ይችላል? አንደኛው ምክንያት በይሖዋ ላይ እምነት ማጣታቸውና እሱን መስማት አለመፈለጋቸው ነው። ትክክለኛ እውቀት ወይም አምላካዊ ጥበብ ለማግኘት ጥረት አላደረጉም፤ እንዲሁም በይሖዋ አልታመኑም። ትክክለኛ እውቀት ቢኖራቸው ኖሮ ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ ማድረግ ይችሉ ነበር። (መዝ. 25:12) በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሌሎች ተጽዕኖ እንዲያደርጉባቸው አልፎ ተርፎም ውሳኔ እንዲያደርጉላቸው ፈቅደዋል። እስራኤላውያን፣ በዙሪያቸው የነበሩ ይሖዋን የማያመልኩ ሰዎች በአስተሳሰባቸው ላይ ተጽዕኖ ስላሳደሩባቸው እነዚያን ጣዖት አምላኪዎች መከተል ጀመሩ። ይሖዋ ይህ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አስቀድሞ አስጠንቅቋቸው ነበር።—ዘፀ. 23:2

ሌሎች ውሳኔ ሊያደርጉልን ይገባል?

8. ውሳኔ ማድረግን በተመለከተ ከእስራኤላውያን ታሪክ ምን ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን?

8 ቀደም ሲል ያየናቸው ምሳሌዎች ጠቃሚ ትምህርት ያስተላልፋሉ። ውሳኔ ማድረግ የእያንዳንዳችን ኃላፊነት ነው፤ በተጨማሪም ጥበብ የሚንጸባረቅበትና ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግ የምንችለው ቅዱስ ጽሑፋዊ እውቀት ሲኖረን ነው። ገላትያ 6:5 “እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል” በማለት ያሳስበናል። ሌላ ሰው ውሳኔ እንዲያደርግልን ኃላፊነቱን ልንሰጠው አይገባም። ከዚህ ይልቅ በአምላክ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ራሳችን ለይተን ማወቅና ይህን ለመከተል መምረጥ ይኖርብናል።

9. ሌሎች እንዲወስኑልን ማድረግ አደገኛ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

9 ሌሎች ሰዎች ውሳኔ እንዲያደርጉልን በመፍቀድ አደገኛ የሆነ አካሄድ ልንከተል የምንችለው እንዴት ነው? የእኩዮች ተጽዕኖ መጥፎ ውሳኔዎችን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይችላል። (ምሳሌ 1:10, 15) ሌሎች ሰዎች ምንም ያህል ተጽዕኖ ሊያደርጉብን ቢሞክሩም በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነውን ሕሊናችንን መከተል የእኛ ኃላፊነት ነው። ሌሎች ውሳኔ እንዲያደርጉልን የምንፈቅድ ከሆነ እነሱን ‘ለመከተል’ መርጠናል ማለት ነው። እንዲህ ዓይነቱ ምርጫ ግን ውጤቱ አስከፊ ነው።

10. ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች ምን ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል?

10 ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሌሎች ውሳኔ እንዲያደርጉልን መፍቀድ ያለውን አደጋ በተመለከተ በገላትያ ለነበሩት ክርስቲያኖች ግልጽ የሆነ ማሳሰቢያ ሰጥቷቸዋል። (ገላትያ 4:17ን አንብብ።) በጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንዶች ለሌሎች ውሳኔ ማድረግ ይፈልጉ ነበር፤ ይህን ያደርጉ የነበረው ለምንድን ነው? እነዚህ ራስ ወዳድ ሰዎች፣ ወንድሞችን ከሐዋርያት በማራቅ የእነሱ ተከታዮች እንዲሆኑ ለማድረግ ስለፈለጉ ነው። እነዚህ ሰዎች ቦታቸውን አልፈው ከመሄዳቸውም ሌላ ክርስቲያን ወንድሞቻቸው የራሳቸውን ውሳኔ በማድረግ ረገድ ያላቸውን መብት አላከበሩላቸውም።

11. ሌሎች የግል ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?

11 ሁላችንም ጳውሎስ ከተወው ጥሩ ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን፤ ጳውሎስ፣ ወንድሞቹ የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳላቸው በመገንዘብ ይህን መብታቸውን አክብሮላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:24ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም ከግል ምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ምክር ሲሰጡ የእሱን ምሳሌ ሊከተሉ ይገባል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መመሪያዎችን ለመንጋው አባላት ለማካፈል ፈቃደኞች ናቸው። ያም ሆኖ ሽማግሌዎች፣ ውሳኔ የማድረጉን ኃላፊነት ለእያንዳንዱ ግለሰብ መተው ይኖርባቸዋል። እንዲህ ማድረጋቸው ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ውሳኔው የሚያስከትለውን ውጤት የሚቀበለው ራሱ ነው። በመሆኑም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የምናገኘው አንድ ጠቃሚ ትምህርት አለ፦ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን ወይም ምክሮችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ሌሎችን ልንረዳቸው እንችላለን። ያም ሆኖ ሌሎች የራሳቸውን ውሳኔ የማድረግ መብት እንዳላቸው እንዲሁም ይህ የእነሱ ኃላፊነት እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። እነዚህ ሰዎች ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ሲያደርጉ እንደሚጠቀሙ ጥርጥር የለውም። በግልጽ ለመረዳት እንደምንችለው፣ ለሌሎች ወንድሞችና እህቶች ውሳኔ የማድረግ ሥልጣን እንዳለን አድርገን ፈጽሞ ልናስብ አይገባም።

አፍቃሪ የሆኑ እረኞች፣ የራሳቸውን ውሳኔ እንዲያደርጉ ሌሎችን ይረዳሉ (አንቀጽ 11ን ተመልከት)

በስሜት ተገፋፍታችሁ ውሳኔ አታድርጉ

12, 13. በተበሳጨንበት ወይም ተስፋ በቆረጥንበት ወቅት ልባችን የሚለንን መከተል አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

12 ብዙ ሰዎች ‘ልብህ የሚልህን አድርግ’ ሲሉ ይሰማሉ። እንዲህ ማድረግ ግን አደገኛ ሊሆን ይችላል። ደግሞም ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፍጹም ያልሆነውን ልባችንን ተከትለን ወይም በስሜት ተገፋፍተን ውሳኔ እንዳናደርግ ያሳስበናል። (ምሳሌ 28:26) ልባችን የሚለንን መከተል የሚያመጣውን አስከፊ መዘዝ የሚያሳዩ ዘገባዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው እናገኛለን። ፍጽምና የጎደለን በመሆናችን ልባችንን ማመን አንችልም፤ ምክንያቱም “ልብ ከምንም ነገር በላይ ከዳተኛ ነው፤ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ አይመለስም።” (ኤር. 3:17፤ 13:10፤ 17:9፤ 1 ነገ. 11:9) ውሳኔ ስናደርግ ልባችን የሚለንን ብንከተል ውጤቱ ምን ይሆናል?

13 ልብ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው፤ ክርስቲያኖች ይሖዋን በሙሉ ልባቸው እንዲወዱ እንዲሁም ባልንጀራቸውን እንደ ራሳቸው እንዲወዱ ታዘዋል። (ማቴ. 22:37-39) ሆኖም ቀደም ባለው አንቀጽ ላይ ያሉት ጥቅሶች እንደሚያሳዩት ስሜታችን በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድር መፍቀድ አደገኛ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በተበሳጨንበት ወቅት ውሳኔ ብናደርግ ምን ሊፈጠር ይችላል? ከዚህ ቀደም በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ውሳኔ አድርገን ከነበረ መልሱ አይጠፋንም። (ምሳሌ 14:17፤ 29:22) ተስፋ በቆረጥንበት ጊዜም ቢሆን ጥሩ ውሳኔ ማድረግ እንደማንችል የታወቀ ነው። (ዘኁ. 32:6-12፤ ምሳሌ 24:10) መጽሐፍ ቅዱስ “ለአምላክ ሕግ ባሪያ” መሆን የጥበብ አካሄድ መሆኑን እንደሚገልጽ እናስታውስ። (ሮም 7:25) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎችን ስናደርግ ስሜታችን እንዲቆጣጠረን ከፈቀድን በቀላሉ ልንሳሳት እንችላለን።

ውሳኔያችንን መቀየር የሚኖርብን መቼ ነው?

14. ያደረግነውን ውሳኔ አንዳንድ ጊዜ መቀየር አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል እንዴት እናውቃለን?

14 ሁላችንም ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ማድረግ አለብን። ይህ ሲባል ግን አንድ ጊዜ ያደረግነውን ውሳኔ ፈጽሞ መቀየር የለብንም ማለት አይደለም። ውሳኔያችንን መለስ ብለን ማጤን ምናልባትም መቀየር የሚያስፈልገን ጊዜ ሊኖር ይችላል። በዮናስ ዘመን ይሖዋ ከነነዌ ሰዎች ጋር በተያያዘ ያደረገውን ነገር እንደ ምሳሌ መመልከት እንችላለን። “እውነተኛው አምላክ ያደረጉትን ነገር ይኸውም ከክፉ መንገዳቸው እንዴት እንደተመለሱ አየ፤ በእነሱም ላይ አመጣዋለሁ ያለውን ነገር መልሶ በማጤን ጥፋቱን ከማምጣት ተቆጠበ።” (ዮናስ 3:10) ይሖዋ የነነዌ ሰዎች ንስሐ እንደገቡና እንደተለወጡ ሲያይ ውሳኔውን ቀይሯል። ይህን በማድረግ ምክንያታዊ፣ ትሑትና ሩኅሩኅ አምላክ መሆኑን አሳይቷል። ከዚህም ሌላ አምላክ፣ በሚቆጣበት ጊዜም እንኳ ብዙ ሰዎች እንደሚያደርጉት ያልታሰበበት ውሳኔ አያደርግም።

15. ውሳኔያችንን እንድንቀይር የሚያነሳሳን ምን ሊሆን ይችላል?

15 አንዳንድ ጊዜ፣ ያደረግነውን ውሳኔ መለስ ብለን ማጤናችን ጥሩ ይሆናል። እንዲህ ለማድረግ የሚያነሳሳን ሁኔታዎቹ መቀየራቸው ሊሆን ይችላል። ይሖዋም ቢሆን ሁኔታዎች በመለወጣቸው የተነሳ ውሳኔዎቹን የቀየረባቸው ጊዜያት አሉ። (1 ነገ. 21:20, 21, 27-29፤ 2 ነገ. 20:1-5) አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ውሳኔያችንን እንድንቀይር የሚያደርግ አዲስ መረጃ እናገኝ ይሆናል። ንጉሥ ዳዊት የሳኦል የልጅ ልጅ የሆነውን ሜፊቦስቴን በተመለከተ የተሳሳተ ወሬ ተነግሮት ነበር። ከጊዜ በኋላ ዳዊት ስለ ሁኔታው ትክክለኛ መረጃ ሲያገኝ ውሳኔውን አስተካክሏል። (2 ሳሙ. 16:3, 4፤ 19:24-29) እኛም አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ማድረግ ይኖርብን ይሆናል።

16. (ሀ) ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱን አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው? (ለ) ያደረግናቸውን ውሳኔዎች መለስ ብለን ማጤን ያለብን ለምንድን ነው? በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል?

16 የአምላክ ቃል፣ ከበድ ያለ ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ እንዳንቸኩል ያሳስበናል። (ምሳሌ 21:5) ከምናደርገው ውሳኔ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ወይም ሁኔታዎችን በሙሉ ጊዜ ወስደን በሚገባ መመርመራችን ጥሩ ውሳኔ እንድናደርግ ይረዳናል። (1 ተሰ. 5:21) የቤተሰብ ራሶች አንድ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት በአምላክ ቃልና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎች ላይ ምርምር ማድረጋቸው እንዲሁም ሌሎች የቤተሰባቸው አባላት ያላቸውን አመለካከት ግምት ውስጥ ማስገባታቸው አስፈላጊ ነው። አምላክ፣ አብርሃምን የሚስቱን ሐሳብ እንዲሰማ እንዳሳሰበው አስታውስ። (ዘፍ. 21:9-12) ሽማግሌዎችም ጊዜ ወስደው ምርምር ማድረግ አለባቸው። ምክንያታዊና ትሑት ከሆኑ፣ ውሳኔያቸውን እንደገና ማጤን እንዳለባቸው የሚያሳይ ጠቃሚ የሆነ አዲስ መረጃ ሲያገኙ፣ ሌሎች ለእነሱ ያላቸው አክብሮት እንዳይቀንስ በመፍራት ይህን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ አመለካከታቸውንና ውሳኔያቸውን ለማስተካከል ፈቃደኞች መሆን አለባቸው፤ ሁላችንም ብንሆን የእነሱን ምሳሌ መከተላችን ጠቃሚ ነው። ይህም በጉባኤ ውስጥ ሰላምና ሥርዓት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያደርጋል።—ሥራ 6:1-4

ውሳኔያችሁን ተግባራዊ አድርጉ

17. ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል?

17 አንዳንድ ጊዜ ከበድ ያሉ ውሳኔዎች ማድረግ ሊያስፈልገን ይችላል። እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን ስናደርግ ጊዜ ወስደን በሚገባ ማሰብና ስለ ጉዳዩ መጸለይ ይኖርብናል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ትዳር ከመመሥረትና የትዳር ጓደኛ ከመምረጥ ጋር የተያያዙ ከባድ ውሳኔዎች ማድረግ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ከዚህም ሌላ አንድ ክርስቲያን፣ ብዙ በረከት በሚያስገኘው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ሲያስብ ከባድ ውሳኔዎችን ማድረግ ሊኖርበት ይችላል፤ ‘የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን መቼ ልጀምር? በየትኛው የአገልግሎት ዘርፍ ብሰማራ ይሻላል?’ የሚሉትን ጥያቄዎች በሚገባ ሊያስብባቸው ይገባል። ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ይሖዋ ጥበብ ያዘለ መመሪያ ሊሰጠን እንደሚችል ሙሉ በሙሉ መተማመን ይኖርብናል። (ምሳሌ 1:5) በመሆኑም ከሁሉ የተሻለ ምክር የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስን መመርመራችን እንዲሁም በጸሎት የይሖዋን ምክር መጠየቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። ደግሞም ይሖዋ ከእሱ ፈቃድ ጋር የሚስማሙ ውሳኔዎች ለማድረግ የሚረዱ ባሕርያትን እንድናፈራ ያስችለናል። ትላልቅ ውሳኔዎችን በምናደርግበት ጊዜ ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘የማደርገው ውሳኔ ይሖዋን እንደምወድ የሚያሳይ ነው? ቤተሰቤ ደስተኛና ሰላማዊ እንዲሆን አስተዋጽኦ ያደርጋል? ደግሞስ ታጋሽና ደግ እንደሆንኩ ያሳያል?’

18. ይሖዋ የራሳችንን ውሳኔ እንድናደርግ የሚጠብቅብን ለምንድን ነው?

18 ይሖዋ እሱን እንድንወደውና እንድናገለግለው አያስገድደንም። ይህ ለእኛ ምርጫ የተተወ ነገር ነው። የመምረጥ ነፃነት ስለሰጠን እሱን ለማገልገልም ሆነ ላለማገልገል የራሳችንን ‘ምርጫ’ የማድረግ መብት አለን፤ ይሖዋ ይህን ኃላፊነታችንንና መብታችንን ያከብርልናል። (ኢያሱ 24:15፤ መክ. 5:4) ይሁን እንጂ እሱ በሚሰጠን መመሪያ ላይ ተመሥርተን የምናደርጋቸውን ውሳኔዎች በተግባር እንድናውል ይጠብቅብናል። ይሖዋ በሚሰጠን መመሪያ ላይ እምነት ካለንና እነዚህን መመሪያዎች በተግባር ካዋልናቸው ያላንዳች መወላወል ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ እንችላለን።—ያዕ. 1:5-8፤ 4:8