በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጥንታዊ ማሰሮ ላይ ተጽፎ የተገኘ የመጽሐፍ ቅዱስ ስም

በጥንታዊ ማሰሮ ላይ ተጽፎ የተገኘ የመጽሐፍ ቅዱስ ስም

በ2012 የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች 3,000 ዓመታትን ያስቆጠረ የአንድ ማሰሮ ስብርባሪ በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል። ይህን ግኝት ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? የተመራማሪዎቹን ትኩረት የሳቡት ስብርባሪዎቹ ሳይሆኑ በስብርባሪዎቹ ላይ የተጻፉት ነገሮች ናቸው።

የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎቹ ስብርባሪዎቹን በመገጣጠም በማሰሮው ላይ የሰፈረውን የጥንት ከነዓናውያን ጽሑፍ ማንበብ ችለዋል። ጽሑፉ “ኤሽባዓል ቤን ቤዳ [ኤሽባዓል የቤዳ ወንድ ልጅ]” ይላል። የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ይህን ስም ጥንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ተቀርጾ ሲያገኙት ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ነው።

እርግጥ ነው፣ ኤሽባዓል የሚባል ሌላ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን እሱም ከንጉሥ ሳኦል ወንዶች ልጆች መካከል አንዱ ነው። (1 ዜና 8:33፤ 9:39) በቁፋሮው ሥራ ላይ የተካፈሉት ፕሮፌሰር ዮሴፍ ጋርፊንከል እንዲህ ብለዋል፦ “ኤሽባዓል የሚለው ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጻፈውም ሆነ አሁን በአርኪኦሎጂ በተገኙ ማስረጃዎች ላይ የተቀረጸው በዳዊት የግዛት ዘመን ወቅት መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።” አንዳንዶች ይህ ስም በዚያ ዘመን የኖሩ ሰዎች ብቻ ይጠቀሙበት የነበረ መጠሪያ እንደሆነ ያስባሉ። ይህ ግኝት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ዝርዝር ነገሮችም ጭምር የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎች ድጋፍ እንዳላቸው ያረጋግጣል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ኤሽባዓል የሚለው ስም በሌላ ቦታ ላይ ኢያቡስቴ (ኢሽቦሼት) ተብሏል፤ “ባዓል” የሚለው “ቦሼት” በሚለው ተተክቷል። (2 ሳሙ. 2:10) ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ተመራማሪዎች እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፦ “በሁለተኛ ሳሙኤል ላይ ኤሽባዓል የሚለውን ስም መጠቀም እንዳልተፈለገ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል፤ ምክንያቱም ስሙ የከነዓናውያን የዝናብ አምላክ ከሆነው ከባአል ጋር ይመሳሰላል። . . . ይሁንና በዜና መዋዕል መጽሐፍ ላይ ኤሽባዓል የሚለው ስም ተጠቅሶ ይገኛል።”