በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ውስጥ እንስሳት ይሸጡ የነበሩት ሰዎች “ዘራፊዎች” መባላቸው ተገቢ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

የማቴዎስ ወንጌል እንዲህ ይላል፦ “ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ገብቶ በቤተ መቅደሱ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን መቀመጫዎችም ገለባበጠ። እንዲህም አላቸው፦ ‘“ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል” ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አድርጋችሁታል።’”—ማቴ. 21:12, 13

የአይሁድ የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት በቤተ መቅደሱ የነበሩት ነጋዴዎች የእንስሳቱን ዋጋ በጣም በማስወደድ ገዢዎቹን ይበዘብዙ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሚሽና የተባለው መጽሐፍ (ኬሪቶት 1:7) በመጀመሪያው መቶ ዘመን መሥዋዕት ሆነው የሚቀርቡ ሁለት ርግቦች ዋጋ አንድ የወርቅ ዲናር ደርሶ እንደነበር ዘግቧል። አንድ የወርቅ ዲናር ከአንድ የጉልበት ሠራተኛ የ25 ቀን ደሞዝ ጋር ተመጣጣኝ ዋጋ ነበረው። ድሆች ርግቦችን ወይም ዋኖሶችን መሥዋዕት አድርገው ማቅረብ ይፈቀድላቸው ነበር፤ ሆኖም የእነዚህ ወፎች ዋጋ እንኳ የማይቀመስ ሆኖ ነበር። (ዘሌ. 1:14፤ 5:7፤ 12:6-8) ስምዖን ቤን ገማልያል የተባለ ረቢ በዚህ ሁኔታ በጣም በመበሳጨቱ አይሁዳውያን ማቅረብ የሚጠበቅባቸው መሥዋዕቶች ቁጥር እንዲቀንስ አደረገ፤ በዚህም ምክንያት የሁለት ርግቦች ዋጋ ወዲያውኑ ቀነሰ።

ከዚህ መመልከት እንደምንችለው በቤተ መቅደሱ የነበሩት ነጋዴዎች ስግብግብና ሕዝቡን የሚበዘብዙ ነበሩ። በመሆኑም ኢየሱስ እነዚህን ነጋዴዎች “ዘራፊዎች” ብሎ መጥራቱ ተገቢ ነው።