በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

3 | ከመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች የምናገኘው ትምህርት

3 | ከመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች የምናገኘው ትምህርት

መጽሐፍ ቅዱስ . . . “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት” የነበራቸውን ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ታሪክ ይዟል።—ያዕቆብ 5:17

ምን ማለት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ዓይነት ስሜት ያስተናገዱ በርካታ ወንዶችና ሴቶችን ታሪክ ይዟል። ከእነዚህ ታሪኮች መካከል የእኛ ዓይነት ስሜት ያጋጠመው ሰው እናገኝ ይሆናል።

የሚረዳን እንዴት ነው?

ሁላችንም ሌሎች ስሜታችንን እንዲረዱልን እንፈልጋለን። በተለይ ከአእምሮ ጤንነት ጋር የተያያዘ ችግር ሲያጋጥመን ስሜታችንን የሚረዳልን ሰው ይበልጥ እንፈልጋለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች ያጋጠሟቸውን ነገሮች ስናነብ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አስተሳሰብና ስሜት እንደነበራቸው እናስተውል ይሆናል። በዚህ ጊዜ፣ ከስሜታዊ ችግሮች ጋር የታገሉ ሌሎች ሰዎችም እንደነበሩ እንገነዘባለን፤ እንዲሁም ከጭንቀትና ከሚረብሹ ስሜቶች ጋር የምንታገለው እኛ ብቻ እንደሆንን አይሰማንም።

  • መጽሐፍ ቅዱስ፣ መውጫ ቀዳዳ እንዳጡ የተሰማቸው በርካታ ሰዎች የተናገሯቸውን ሐሳቦች ይዟል። ‘አሁንስ በቅቶኛል! ከአቅሜ በላይ ነው’ ብለህ ታውቃለህ? ሙሴ፣ ኤልያስና ዳዊት እንዲህ ዓይነት ስሜት ተሰምቷቸው ነበር።—ዘኁልቁ 11:14፤ 1 ነገሥት 19:4፤ መዝሙር 55:4

  • መጽሐፍ ቅዱስ ሐና የተባለች ሴት፣ ልጅ መውለድ ባለመቻሏ እንዲሁም ጣውንቷ በዚህ ምክንያት ታደርስባት በነበረው ዘለፋ የተነሳ “በጣም ተማርራ” እንደነበር ይናገራል።—1 ሳሙኤል 1:6, 10

  • መጽሐፍ ቅዱስ ኢዮብ የተባለን ሰው ታሪክ ይነግረናል፤ እኛም የእሱ ዓይነት ስሜት ይሰማን ይሆናል። ኢዮብ የእምነት ሰው ቢሆንም ከፍተኛ የስሜት ሥቃይ ስለደረሰበት በአንድ ወቅት “ሕይወቴን ተጸየፍኳት፤ በሕይወት መቀጠል አልፈልግም” ብሎ ነበር።—ኢዮብ 7:16

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች አሉታዊ አስተሳሰባቸውን ማሸነፍ የቻሉት እንዴት እንደሆነ መማራችን ያለንበትን ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ይሰጠናል።