በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

መንፈሰ ጠንካራ ነኝ?

መንፈሰ ጠንካራ ነኝ?

 መንፈሰ ጠንካራ እንደሆንክ ይሰማሃል? የሚከተሉት ነገሮች አጋጥመውሃል?

  •   የቤተሰብህን አባል በሞት አጥተሃል?

  •   ከባድ የጤና እክል አለብህ?

  •   በምትኖርበት አካባቢ የተፈጥሮ አደጋ ደርሶ ያውቃል?

 ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት ከሆነ የመንፈስ ጥንካሬ የሚያስፈልገን ከባድ ችግር ሲያጋጥመን ብቻ አይደለም። የዕለት ተዕለት ውጣ ውረድም በጤንነታችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ከዚህ አንጻር፣ ያጋጠመህ ችግር ቀላልም ይሁን ከባድ መንፈሰ ጠንካራ መሆን ያስፈልግሃል።

 የመንፈስ ጥንካሬ ምንድን ነው?

 የመንፈስ ጥንካሬ የሚባለው የሕይወትን ውጣ ውረዶችና ፈተናዎች በስኬት የማለፍ ችሎታ ነው። መንፈሰ ጠንካራ የሆኑ ሰዎች እንደ ማንኛውም ሰው መከራ ያጋጥማቸዋል። ሆኖም መከራውን በጽናት ይቋቋማሉ፤ እንዲሁም መከራው ጉዳት ቢያስከትልባቸውም ከበፊቱ ይበልጥ ጠንካራ ይሆናሉ።

አንዳንድ ዛፎች ኃይለኛ አውሎ ነፋስ ሲመጣ ዘመም ብለው ነፋሱ ሲያልፍ እንደሚቃኑ ሁሉ አንተም ካጋጠመህ ችግር ማገገም ትችላለህ

 መንፈሰ ጠንካራ መሆን የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?

  •   መከራ መድረሱ ስለማይቀር። መጽሐፍ ቅዱስ “ፈጣኖች በውድድር ሁልጊዜ አያሸንፉም፤ . . . እውቀት ያላቸው ሰዎችም ሁልጊዜ ስኬታማ አይሆኑም፤ ምክንያቱም ሁሉም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሟቸዋል” ይላል። (መክብብ 9:11) ነጥቡ ምንድን ነው? ጥሩ ሰዎችም እንኳ ምንም ጥፋት ሳይሠሩ መከራ የሚደርስባቸው ጊዜ አለ።

  •   መንፈሰ ጠንካራ መሆን ጥበቃ ስለሚያስገኝልህ። በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚሠሩ አንድ የተማሪዎች አማካሪ እንዲህ ብለዋል፦ “በጣም ብዙ ተማሪዎች ፈተና ላይ C ሲያገኙ ወይም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያበሳጭ ነገር ሲጻፍባቸው ወደ ቢሮዬ መጥተው ሁሉ ነገር እንደጨለመባቸው ይነግሩኛል።” እኚህ ሰው እንደገለጹት፣ እንዲህ ካሉ ቀላል የሚመስሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘም እንኳ ጠንከር ብለው ችግሩን ማለፍ የማይችሉ ልጆች “ለተለያዩ አእምሯዊና ስሜታዊ ቀውሶች ይጋለጣሉ።” a

  •   መንፈሰ ጠንካራ መሆን አሁንም ሆነ አዋቂ ስትሆን ስለሚጠቅምህ። ዶክተር ሪቻርድ ለርነር እንደጻፉት “አንድ ሰው በሕይወቱ ስኬታማና ውጤታማ መሆን የሚችለው ያሰበው ነገር አልሳካ ሲለው ሁኔታውን መቋቋምና ሌላ ግብ ማውጣት ወይም ዕቅዱን ለማሳካት አማራጭ መንገዶችን መፈለግ ከቻለ ነው።” b

 መንፈሰ ጠንካራ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

  •  ችግርህን ክብደት መመዘን ተማር። ከባድና ቀላል ችግሮችን ለይ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝ ሰው ቁጣውን ወዲያውኑ ይገልጻል፤ ብልህ ሰው ግን ስድብን ችላ ብሎ ያልፋል” ይላል። (ምሳሌ 12:16) ትንሽ ችግር ስላጋጠመህ ብቻ በሐዘን ልትዋጥ አይገባም።

     “ትምህርት ቤት ያሉ ልጆች ስለ ትናንሽ ችግሮች አካብደው ይናገራሉ። የማኅበራዊ ሚዲያ ጓደኞቻቸው ጉዳዩን ሲያራግቡላቸው ደግሞ ጭራሽ ይብስባቸዋል፤ ይህም የችግሩን ክብደት መመዘን እንዲከብዳቸው ያደርጋል።”—ጆአን

  •   ከሌሎች ተማር። መጽሐፍ ቅዱስ “ብረት ብረትን እንደሚስል ሁሉ ሰውም ጓደኛውን ይስለዋል” ይላል። (ምሳሌ 27:17) ከባድ መከራ ካሳለፉ ሰዎች ብዙ ጠቃሚ ትምህርት ማግኘት ይቻላል።

     “ከሌሎች ጋር ስትነጋገሩ ብዙ መከራ ቢያሳልፉም አሁን ግን ደህና እንደሆኑ ማስተዋል ትችላላችሁ። መከራውን ለመቋቋም ሲሉ ምን እንዳደረጉ ወይም ምን ከማድረግ እንደተቆጠቡ ልትጠይቋቸው ትችላላችሁ።”—ጁልያ

  •   ትዕግሥተኛ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ ሰባት ጊዜ ቢወድቅ እንኳ መልሶ ይነሳል” ይላል። (ምሳሌ 24:16) ያጋጠመህን ሁኔታ ለመቀበል ጊዜ ይወስዳል፤ ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ በሐዘን ብትዋጥ ልትገረም አይገባም። ዋናው ነገር ‘መልሰህ መነሳትህ’ ነው።

     “መከራው ካለፈ በኋላ ወደ ቀድሞ ሁኔታህ ለመመለስ ልብህ ማገገም ይኖርበታል። ይሄ ደግሞ በአንዴ የሚሆን ነገር አይደለም፤ ጊዜ ይፈልጋል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን ሐዘኑ ቀለል እንደሚል አስተውያለሁ።”—አንድሪያ

  •   አመስጋኝ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ” ይላል። (ቆላስይስ 3:15) ያለህበት መከራ ምንም ያህል ከባድ ቢሆን አመስጋኝ መሆን የምትችልበት ነገር እንደሚኖር ጥርጥር የለውም። ሕይወትህን አስደሳች የሚያደርጉ ሦስት ነገሮችን ለማሰብ ሞክር።

     “መከራ ሲያጋጥምህ ‘ለምን እኔ ላይ ደረሰ?’ ብለህ መጠየቅህ አይቀርም። መንፈሰ ጠንካራ ከሆንክ ግን ስለ ችግሩ ከልክ በላይ ከማሰብ ይልቅ ስላሉህ ወይም ማከናወን ስለምትችላቸው ነገሮች አመስጋኝ ትሆናለህ።”—ሰማንታ

  •   ባሉህ ነገሮች ለመርካት ሞክር። ሐዋርያው ጳውሎስ “በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብሆን ባለኝ ረክቼ መኖርን ተምሬአለሁ” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 4:11) ጳውሎስ ያጋጠሙት መከራዎች ከቁጥጥሩ ውጭ ነበሩ። ለመከራው የሚሰጠውን ምላሽ ግን መቆጣጠር ይችል ነበር። በመሆኑም ባለው ነገር ለመርካት ወስኗል።

     “አብዛኛውን ጊዜ መከራ ሲያጋጥመኝ መጀመሪያ የምሰጠው ምላሽ ጥሩ እንዳልሆነ አስተውያለሁ። ስለዚህ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ አዎንታዊ ለመሆን ግብ አውጥቻለሁ። እንዲህ ማድረጌ ለእኔም ሆነ አብረውኝ ላሉ ሰዎች ጠቃሚ ነው።”—ማቲው

  •   ጸልይ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል። ጻድቁ እንዲወድቅ ፈጽሞ አይፈቅድም” ይላል። (መዝሙር 55:22) ጸሎት የምናቀርበው ስሜታችን እንዲረጋጋ ስለምንፈልግ ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የምንጸልየው ‘ስለ እኛ የሚያስበውን’ ፈጣሪያችንን ማነጋገር ስለምንፈልግ ነው።—1 ጴጥሮስ 5:7

     “ብቻዬን ለምን እቸገራለሁ? ስለ ችግሩ በግልጽ በመጸለይና አምላክን ላደረገልኝ ነገሮች በማመስገን አሉታዊ ስሜቶቼን ማስወገድ እችላለሁ፤ ይሖዋ ባደረገልኝ ነገር ላይ አተኩራለሁ። ጸሎት በጣም አስፈላጊ ነው!”—ካርሎስ

a በቶማስ ከርስቲንግ ከተዘጋጀው ዲስኮኔክትድ የተባለ መጽሐፍ የተወሰደ።

b ዘ ጉድ ቲን—ሬስክዩኢንግ አዶለሰንስ ፍሮም ዘ ሚዝስ ኦቭ ዘ ስቶርም ኤንድ ስትረስ ይርስ ከተባለው መጽሐፍ የተወሰደ።