በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

መጽሐፍ ቅዱስ ሊጠቅመኝ የሚችለው እንዴት ነው?—ክፍል 2፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን አስደሳች ማድረግ

መጽሐፍ ቅዱስ ሊጠቅመኝ የሚችለው እንዴት ነው?—ክፍል 2፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብን አስደሳች ማድረግ

 “መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት ማንበብ እንዳለብህ ካላወቅክ አሰልቺ መስሎ ሊታይህ ይችላል” በማለት በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ዊል ተናግሯል።

 የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህን አስደሳች ለማድረግ የሚረዱህን ዘዴዎች ማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ ይህ ርዕስ ይረዳሃል።

 የምታነበው ጥቅስ ሕያው እንዲሆንልህ አድርግ

 በምታነበው ነገር ተመሰጥ። የሚከተሉትን ዘዴዎች መጠቀም ትችላለህ፦

  1.   ማጥናት የምትፈልገውን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ምረጥ። ከወንጌል ዘገባዎች ውስጥ የተወሰነ ክፍል አሊያም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ልትመርጥ ትችላለህ፤ ወይም ደግሞ በ​jw.org ላይ ከሚገኙት ድራማዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች ውስጥ አንዱን መምረጥ ትችላለህ።

  2.   ዘገባውን አንብብ። ዘገባውን ለብቻህ አሊያም ከጓደኞችህ ወይም ከቤተሰብህ አባላት ጋር ማንበብ ትችላለህ። አንድ ሰው ተራኪ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በዘገባው ውስጥ የተጠቀሱትን ሰዎች ገጸ ባሕርይ ወክለው ማንበብ ይችላሉ።

  3.   ከሚከተሉት ሐሳቦች መካከል ቢያንስ አንዱን [ወይም ከዚያ በላይ የሆኑትን] ሞክር፦

    •   ዘገባውን በሥዕል መልክ ለማስቀመጥ ሞክር። ወይም ደግሞ ክንውኖቹን በጊዜ ቅደም ተከተል የሚያሳዩ ቀላል ሥዕሎችን ሳል። እያንዳንዱ ሥዕል ምን እንደሚያመለክት የሚያሳይ መግለጫ ጻፍ።

    •   ስለ አንድ ታማኝ ሰው የሚናገር ዘገባ ስታነብ፣ ግለሰቡ ያሉትን ባሕርያትና ያደረጋቸውን ነገሮች እንዲሁም ያገኛቸውን በረከቶች ጻፍ።

    •   ዘገባውን በዜና መልክ አቀናብረው። ከዚያም በታሪኩ ውስጥ ለተጠቀሱት ለዋናዎቹ ባለታሪኮችና የዓይን ምሥክሮች “ቃለ መጠይቅ” በማድረግ ዘገባውን ከተለያየ አቅጣጫ ለማቅረብ ሞክር።

    •   በዘገባው ውስጥ የተጠቀሰ አንድ ሰው የተሳሳተ ውሳኔ አድርጎ ከሆነ፣ ግለሰቡ ምን ቢያደርግ ውጤቱ የተሻለ ሊሆን ይችል እንደነበር አስብ። ለምሳሌ፣ ጴጥሮስ ኢየሱስን ስለ መካዱ የሚናገረውን ዘገባ አንብብ። (ማርቆስ 14:66-72) በዚያ ወቅት ጴጥሮስ ምን ቢያደርግ የተሻለ ይሆን ነበር?

    •   ንባብህ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ተጨማሪ ነገር ማድረግ ከፈለግክ ደግሞ ባነበብከው ዘገባ ላይ ተመሥርተህ የራስህን ድራማ ጻፍ። ከድራማው ሊገኝ የሚችለውን ትምህርትም ግለጽ።—ሮም 15:4

      መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው እንዲሆንልህ ማድረግ ትችላለህ!

 ጥልቅ ምርምር አድርግ!

 የአንድን ዘገባ ዝርዝር ሁኔታዎች ከመረመርክ በዘገባው ውስጥ ያሉትን ውድ መንፈሳዊ ሀብቶች ማግኘት ትችላለህ። ደግሞም አንዳንድ ጊዜ፣ በዘገባው ውስጥ የተጠቀሱ አንድ ወይም ሁለት ቃላት ብቻ ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ።

 ለምሳሌ ያህል፣ ማቴዎስ 28:7ን ከማርቆስ 16:7 ጋር አወዳድር።

  •    ማርቆስ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱና “ለጴጥሮስ” እንደሚታይ የሚገልጸውን ዝርዝር ሐሳብ ያሰፈረው ለምንድን ነው?

  •  ፍንጭ፦ ማርቆስ እነዚህ ሁኔታዎች ሲፈጸሙ በቦታው አልነበረም፤ ይህን መረጃ ያገኘው ከጴጥሮስ ነው።

  •  ምርምር ማድረግህ የሚያስገኝልህ ውድ ሀብት፦ ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ሊያገኘው እንደሚፈልግ በማወቁ ተጽናንቶ መሆን አለበት የምንለው ለምንድን ነው? (ማርቆስ 14:66-72) ኢየሱስ ለጴጥሮስ እውነተኛ ወዳጅ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? አንተስ ኢየሱስን መምሰልና ለሌሎች እውነተኛ ወዳጅ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

 መጽሐፍ ቅዱስን ሕያው እንዲሆንልህ በሚያደርግ መንገድ ማንበብህና ጥልቅ ምርምር ማድረግህ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብህ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ይረዳሃል!