በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የቤት ሥራዬን ሠርቼ መጨረስ የምችለው እንዴት ነው?

የቤት ሥራዬን ሠርቼ መጨረስ የምችለው እንዴት ነው?

 “እስከ ሌሊቱ 7:00 ድረስ ቁጭ ብሎ የቤት ሥራ መሥራት በጣም አድካሚ ነው። በዚያ ሰዓት የሚታየኝ መተኛት ብቻ ነው።”—ዴቪድ

 “አንዳንድ ጊዜ እስከ ሌሊቱ 10:30 ድረስ እያጠናሁ አመሽ ነበር፤ ከዚያም ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ 12:00 ላይ እነሳለሁ። ጨርሶ አልተኛም ነበር ማለት ይቻላል!”—ተሪሳ

 የቤት ሥራ በጣም እንደሚበዛብህ ይሰማሃል? ከሆነ ይህ ርዕስ መፍትሔ እንድታገኝ ይረዳሃል።

 አስተማሪዎች የቤት ሥራ የሚሰጡት ለምንድን ነው?

 የቤት ሥራ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ጨምሮ ብዙ ጥቅሞችን ያስገኝልሃል።

  •   እውቀትህን እንድታሰፋ ይረዳሃል

  •   ኃላፊነት የሚሰማው ሰው እንድትሆን ይረዳሃል

  •   የጊዜ አጠቃቀም እንድትማር ይረዳሃል

  •   ክፍል ውስጥ የተማርካቸውን ነገሮች እንዳትረሳ ይረዳሃል a

 “አስተማሪዎች የቤት ሥራ የሚሰጡት ተማሪዎቻቸው የተማሩትን ነገር በአንድ ጆሯቸው ሰምተው በሌላኛው ከማፍሰስ ይልቅ በተግባር እንዲያውሉት ለማድረግ ነው።”—ማሪ

 በተለይ እንደ ሒሳብ እና ሳይንስ ያሉ ትምህርቶች ችግሮችን የመፍታት ችሎታ እንድታዳብር ይረዱሃል። አንዳንድ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት አእምሮህን በዚህ መንገድ ማሠራትህ በአንጎልህ ውስጥ አዳዲስ የነርቭ ግንኙነቶች እንዲፈጠሩ ያደርጋል። ስለዚህ የቤት ሥራ ለአንጎልህ እንደ ስፖርት ነው ሊባል ይችላል።

 ጥቅሙን ተረዳኸውም አልተረዳኸው የቤት ሥራ የማይቀርልህ ነገር ነው። ደስ የሚለው ነገር፣ የሚሰጥህን የቤት ሥራ ብዛት መቀነስ ባትችልም እንኳ የቤት ሥራውን ለማጠናቀቅ የሚፈጅብህን ጊዜ መቀነስ ትችላለህ። እንዴት?

 ጠቃሚ ምክሮች

 የቤት ሥራህን ሠርተህ ለመጨረስ ከተቸገርክ መፍትሔው በብልሃት መሥራት ሊሆን ይችላል። ከዚህ በታች የቀረቡትን ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር፦

  •   አንደኛ፦ ቅድመ ዝግጅት አድርግ። መጽሐፍ ቅዱስ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል” ይላል። (ምሳሌ 21:5) የቤት ሥራህን መሥራት ከመጀመርህ በፊት የሚያስፈልጉህን መሣሪያዎች በሙሉ አሟላ፤ ይህም ከተቀመጥክበት መነሳት ሳያስፈልግህ የቤት ሥራህን ለመሥራት ያስችልሃል።

     በተጨማሪም ትኩረትህን ለመሰብሰብ የሚያስችልህ ቦታ ምረጥ። አንዳንዶች ቤታቸው ውስጥ ጸጥ ያለና በቂ ብርሃን ያለው ክፍል ውስጥ መሥራት ይመርጣሉ። ሌሎች ሰዎች ደግሞ ሌላ ቦታ ለምሳሌ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ቢሠሩ የተሻለ እንደሆነ ይሰማቸዋል።

     “ፕሮግራምህን በማስታወሻ ደብተር ወይም በቀን መቁጠሪያ ላይ በጽሑፍ ማስፈርህ ጊዜህን በጥበብ ለመጠቀም ያስችልሃል። ምን የቤት ሥራ እንዳለህና መቼ መጠናቀቅ እንዳለበት የምትከታተል ከሆነ ውጥረትህን መቀነስ ትችላለህ።”—ሪቻርድ

  •   ሁለተኛ፦ የተደራጀህ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን” ይላል። (1 ቆሮንቶስ 14:40) በመሆኑም የቤት ሥራህን በምን ዓይነት ቅደም ተከተል ብትሠራ የተሻለ እንደሚሆን አስቀድመህ መወሰንህ ጠቃሚ ነው።

     አንዳንዶች ከከባዱ መጀመርን ይመርጣሉ። ሌሎች ደግሞ ለቀጣዩ ሥራ ሞራል እንዲሰጣቸው ከቀላሉ መጀመርን ይመርጣሉ። ለአንተ ተስማሚ የሆነውን ዘዴ ተጠቀም።

     “ሥራዎችህን በዝርዝር መጻፍህ ምን መሥራት እንዳለብህና በምን ቅደም ተከተል መሥራት እንዳለብህ ለማወቅ ይረዳሃል። እንዲህ ካደረግክ የቤት ሥራህን በፕሮግራምህ መሠረት ስለምትሠራ ሸክም እንደበዛብህ አይሰማህም።”—ሃይዲ

  •   ሦስተኛ፦ ሥራህን ቶሎ ጀምር። መጽሐፍ ቅዱስ “ታታሪዎች ሁኑ እንጂ አትስነፉ” ይላል። (ሮም 12:11) የቤት ሥራህን መሥራት በሚኖርብህ ሰዓት ሌሎች ነገሮች ጊዜህን እንዲሻሙብህ አትፍቀድ።

     ዛሬ ነገ የማለት ልማድ ያላቸው ሰዎች በአብዛኛው ሥራቸውን በተገቢው ጊዜ መጨረስ ያቅታቸዋል፤ አሊያም ደግሞ ሥራቸውን የሚያከናውኑት በሩጫ ስለሚሆን ሥራቸው ጥራት አይኖረውም። የቤት ሥራህን በተቻለህ ፍጥነት በመጀመር ራስህን ከአላስፈላጊ ጭንቀት መታደግ ትችላለህ።

     “የቤት ሥራዬን ከትምህርት ቤት እንደመጣሁ ከሠራሁ ወይም የተሰጠኝን ፕሮጀክት ወዲያውኑ መሥራት ከጀመርኩ በኋላ ላይ አያስጨንቀኝም፤ እንዲሁም ሌሎች እንቅስቃሴዎቼን አይነካብኝም።”—ሰሪና

     እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ሁሌም የቤት ሥራህን በተመሳሳይ ሰዓት ላይ ሥራ። ይህም ራስህን የመግዛት ባሕርይ እንድታዳብርና የፕሮግራም ሰው እንድትሆን ይረዳሃል።

  •   አራተኛ፦ ትኩረትህን ሰብስብ። መጽሐፍ ቅዱስ “ፊት ለፊት በትኩረት ተመልከት” ይላል። (ምሳሌ 4:25) ይህን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ፣ በምታጠናበት ወቅት ትኩረትህን ከሚከፋፍሉ ነገሮች በተለይ ከኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች መራቅ ይኖርብሃል።

     ኢንተርኔት መጠቀም ወይም የጽሑፍ መልእክት መለዋወጥ የቤት ሥራህን ለመጨረስ የሚያስፈልግህን ጊዜ በእጥፍ ሊጨምረው ይችላል። ሆኖም ትኩረትህን መሰብሰብ መቻልህ ውጥረት የሚቀንስልህ ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ ትርፍ ጊዜ እንዲኖርህ ይረዳሃል።

     “የሞባይል ስልክ፣ ኮምፒውተር፣ ቴሌቪዥን እና የቪዲዮ ጌሞች ባሉበት ትኩረት መሰብሰብ ከባድ ነው። ስልኬን ማጥፋቴና በአቅራቢያዬ ያሉ ትኩረቴን ሊከፋፍሉ የሚችሉ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን መንቀሌ ትኩረቴ እንዳይከፋፈል ይረዳኛል።”—ጆኤል

  •   አምስተኛ፦ ሚዛናዊ ሁን። መጽሐፍ ቅዱስ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ይላል። (ፊልጵስዩስ 4:5) እረፍት ሲያስፈልግህ በእግርህ በመንሸራሸር፣ ብስክሌት በመንዳት ወይም በመሮጥ የቤት ሥራ መሥራት የሚፈጥርብህን ውጥረት መቀነስ ትችላለህ።

     እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ ካደረግክ በኋላም የቤት ሥራ ከመጠን በላይ እንደበዛብህ የሚሰማህ ከሆነ አስተማሪዎችህን አነጋግራቸው። የቻልከውን ሁሉ እንዳደረግክ ካስተዋሉ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ለማድረግ ሊነሳሱ ይችላሉ።

     “ከቤት ሥራ ጋር የተያያዘ ጭንቀት ደስታህን እንዲያሳጣህ አትፍቀድ። የምትችለውን ያህል ጥረት አድርግ። እንደ ቤት ሥራ ባለ ነገር ምክንያት ሕይወትህ እንዲመሰቃቀልብህ ልትፈቅድ አይገባም።”—ጁልያ

 ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦

  •   የቤት ሥራዬን ለመሥራት የትኞቹ መሣሪያዎች ያስፈልጉኛል?

  •   የቤት ሥራዬን ለመሥራት ከሁሉ የተሻለው ጊዜ የትኛው ነው?

  •   ትኩረቴን መሰብሰብ የምችለው የት ብሆን ነው?

  •   ዛሬ ነገ የማለት ልማድን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

  •   ትኩረቴ እንዲከፋፈልና ቶሎ እንዳልጨርስ ሊያደርጉኝ የሚችሉት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

  •   ትኩረቴን ከሚከፋፍሉ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችና ሌሎች ነገሮች መራቅ የምችለው እንዴት ነው?

  •   ለቤት ሥራ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረኝ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

 ማሳሰቢያ፦ የቤት ሥራው ምን እንደሆነ በትክክል ሊገባህ ይገባል። ያልገባህ ነገር ካለ ከክፍል ከመውጣትህ በፊት አስተማሪህን ጠይቅ።

a ሐሳቦቹ የተወሰዱት በጂን ስካም ከተዘጋጀው ስኩል ፓወር የተሰኘ መጽሐፍ ነው።