በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የትምህርት ውጤቴ ዝቅተኛ ከሆነ ምን ላድርግ?

የትምህርት ውጤቴ ዝቅተኛ ከሆነ ምን ላድርግ?

 “አንዳንዶቹ የክፍሌ ልጆች አስተማሪው ሲያስተምር መጽሐፍ እንኳ ሳይዙ ጆሯቸው ላይ ሄድፎን ሰክተው ሙዚቃ እየሰሙ ይቀመጣሉ። እነሱስ ቢወድቁ አያስገርምም! በሌላ በኩል ደግሞ እንደ እኔ ያሉ ልጆች መጽሐፋቸው ላይ ተተክለው ቢውሉም ጥሩ ውጤት አያመጡም። ይህ የሚሆነው ለምን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም። ሳምንቱን ሙሉ እስከ ሌሊት ሳጠና ከቆየሁ በኋላ መጥፎ ውጤት ሳገኝ በጣም እበሳጫለሁ።”—ዮላንዳ

 አንተስ እንደ ዮላንዳ ተሰምቶህ ያውቃል? እውነቱን ለመናገር በተለይ በተከታታይ መጥፎ ውጤት ማግኘት ስሜት ይጎዳል።

 ዝቅተኛ ውጤት ያላቸው አንዳንድ ልጆች ተስፋ ስለሚቆርጡ ውጤታቸውን ለማሻሻል ጥረት ማድረጋቸውን ያቆማሉ። ሌሎቹ ደግሞ ከናካቴው ትምህርት ሊያቆሙ ይችላሉ። አንተም ከሁለቱ አማራጮች አንዱን ለማድረግ ትፈተን ይሆናል፤ ሆኖም ችግሩን መፍታት የሚቻልበት ሌላ መንገድ አለ። ውጤትህን ለማሻሻል የሚረዱህን ስድስት እርምጃዎች እስቲ እንመልከት።

 ምን ማድረግ ትችላለህ?

  •   ከትምህርት ቤት አትቅር። ‘ይሄማ ግልጽ ነው’ ብለህ ታስብ ይሆናል፤ ሆኖም በተደጋጋሚ ከክፍል ከቀረህ ውጤትህ ማሽቆልቆሉ አይቀርም።

     “እኛ ትምህርት ቤት ብዙ ጊዜ ከክፍል የሚቀሩት ለውጤታቸው የማይጨነቁት ልጆች ናቸው፤ ይህ ደግሞ እንደሚጎዳቸው ጥያቄ የለውም።”—ማቲው

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።”—ገላትያ 6:7

  •   ክፍል ውስጥ በደንብ ተከታተል። ክፍል ውስጥ መገኘት በራሱ ጥሩ ነገር ነው፤ ሆኖም በደንብ መከታተልም ያስፈልግሃል። ጥሩ ማስታወሻ ያዝ። አስተማሪው የሚያስተምረውን ነገር ለመረዳት ጥረት አድርግ። የሚፈቀድልህ ከሆነ ክፍል ውስጥ ጥያቄ ጠይቅ።

     “ክፍል ውስጥ ብዙ ጥያቄ እጠይቃለሁ፤ ምክንያቱም አስተማሪው ያልገባው ተማሪ እንዳለ ካወቀ በተሻለ መንገድ ያስረዳናል።”—ኦሊቪያ

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እንዴት እንደምታዳምጡ በጥሞና አስቡ።”—ሉቃስ 8:18

  •   አትኮርጅ። ኩረጃ ሐቀኝነት የጎደለው ድርጊት ነው። ተማሪዎች በተለያዩ መንገዶች ይኮርጃሉ። አንዱ መንገድ የሌሎችን ሥራ የራስ አስመስሎ ማቅረብ ነው። ይህን ማድረግ ሐቀኝነት ማጉደል ከመሆኑም ሌላ የሚኮርጀውን ሰውም ይጎዳዋል።

     “ፈተና ላይ መልሱን የማታውቀው ጥያቄ ካለ ከሌሎች ተማሪዎች አትኮርጅ። መኮረጅ ምንም አይጠቅምህም። ችግርህን በራስህ ከመፍታት ይልቅ የሌሎች ጥገኛ ሆነህ ትቀራለህ።”—ጆናታን

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም . . . እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።”—ገላትያ 6:4

  •   የቤት ሥራህን ለመሥራት ቅድሚያ ስጥ። የሚቻል ከሆነ የቤት ሥራህን ሌሎች ነገሮች ከማከናወንህ በፊት፣ በተለይ ደግሞ ከመዝናናትህ በፊት ሥራ። a የቤት ሥራህን ከጨረስክ በኋላ የመዝናኛ ጊዜህን ይበልጥ አስደሳች በሆነ መንገድ ማሳለፍ ትችላለህ።

     “ለቤት ሥራዬ ቅድሚያ ስለምሰጥ የትምህርት ውጤቴ ተሻሽሏል። ቤት ስገባ ቶሎ መተኛት ወይም ሙዚቃ መስማት ነበር የምፈልገው። አሁን ግን መጀመሪያ የቤት ሥራዬን ከሠራሁ በኋላ ለማረፍ እሞክራለሁ።”—ካልቪን

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10

  •   እርዳታ ጠይቅ። የሌሎችን እርዳታ መቀበል ሊያሳፍርህ አይገባም። ወላጆችህን ምክር ጠይቃቸው። እንዲሁም አስተማሪህ ውጤትህን ማሻሻል እንድትችል እንዲረዳህ ጠይቀው። ምናልባትም አስጠኚ ማግኘት ትችል ይሆናል።

     “አስተማሪህን በቀጥታ አነጋግር። ትምህርቱን ለመረዳትና ውጤትህን ለማሻሻል እንዲረዳህ ጠይቀው። አስተማሪው ውጤትህን ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት ማድነቁና ሊረዳህ መነሳሳቱ አይቀርም።”—ዴቪድ

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ብዙ አማካሪዎች ባሉበት . . . ስኬት ይገኛል።”—ምሳሌ 11:14

  •   ያሉህን አጋጣሚዎች በሙሉ ተጠቀምባቸው። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የሚሰጡ ፈተናዎች የተማሪዎችን ውጤት ከፍ ለማድረግ የሚረዱ ተጨማሪ ጥያቄዎች ይኖሯቸዋል። ወይም ደግሞ ተጨማሪ የቤት ሥራዎችን በመሥራት ውጤትህን ማሻሻል የምትችልበት አጋጣሚ ታገኝ ይሆናል። ፈተና ከወደቅክ ፈተናውን በድጋሚ ለመፈተን ጥያቄ ማቅረብም ትችል ይሆናል።

    ውጤትህን ማሻሻል የሙዚቃ መሣሪያ መጫወት እንደ መማር ነው። ቀላል አይደለም፤ ሆኖም ይክሳል

     “ውጤቴን ማሻሻል ከፈለግኩ የራሴን እርምጃ መውሰድ ይኖርብኛል። ውጤቴን ከፍ ለማድረግ የሚረዳ የቤት ሥራ ለመሥራት ወይም ፈተናውን በድጋሚ ለመፈተን አስተማሪዎቼን እጠይቃለሁ።”—ማኬንዚ

     የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “በትጋት ያከናወኑት ነገር ሁሉ ጥቅም ያስገኛል።”—ምሳሌ 14:23

a የጥናት ልማድህን ማሻሻል ስለምትችልበት መንገድ ጠቃሚ ምክር ለማግኘት “የወጣቶች ጥያቄ . . . የቤት ሥራዬን ሠርቼ መጨረስ የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።