በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የፍቅር ጓደኝነት—ክፍል 2፦ በፍቅር ጓደኝነት ውስጥ ምን ነገሮችን ልጠብቅ?

የፍቅር ጓደኝነት—ክፍል 2፦ በፍቅር ጓደኝነት ውስጥ ምን ነገሮችን ልጠብቅ?

 በቅርቡ ያገኘሃት አንዲት ልጅ ቀልብህን ገዝታዋለች፤ አሁን አንዳችሁ ለሌላው ጥሩ የትዳር አጋር ትሆኑ እንደሆነ ለማወቅ የፍቅር ጓደኝነት ጀምራችኋል። እርስ በርስ ይበልጥ እየተዋወቃችሁ ስትሄዱ ምን ነገሮችን መጠበቅ ይኖርብሃል?

በዚህ ርዕስ ውስጥ

 በግልጽ መነጋገር እንደሚኖርብህ ጠብቅ

 አንተና የፍቅር ጓደኛህ ይበልጥ ጊዜ ባሳለፋችሁ ቁጥር አንዳችሁ ስለ ሌላው ብዙ ነገሮችን ማወቃችሁ አይቀርም። አንዳንዶቹን ነገሮች የምታስተውሉት ሌላኛው ወገን በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር የሚያሳየውን ባሕርይ በመመልከት ነው።

 ሆኖም ሁለታችሁም በግልጽ ልትነጋገሩባቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች አሉ። እንዲህ ባሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስትነጋገሩ በተቻለ መጠን ምክንያታዊ መሆንና ስሜታችሁ እይታችሁን እንዳይጋርደው መጠንቀቅ ይኖርባችኋል።

 ሁለታችሁም ልትነጋገሩባቸው ከሚገቡ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  •   የገንዘብ ጉዳይ። ዕዳ አለባችሁ? ወጪያችሁን መቆጣጠር ይከብዳችኋል? ትዳር ከመሠረታችሁ ከገቢ እና ከወጪ ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን የምታደርጉት እንዴት ነው?

  •   ጤና። ጥሩ ጤንነት አላችሁ? ከዚህ በፊት ከባድ የጤና ችግር አጋጥሟችሁ ያውቃል?

  •   ግብ። በሕይወታችሁ ውስጥ የትኞቹን ነገሮች ማሳካት ትፈልጋላችሁ? ግቦቻችሁ እርስ በርስ ይስማማሉ? ከተጋባችሁ በኋላ ከአቅም በላይ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ ግቦቻችሁ ላይ መድረስ ባትችሉ ደስታችሁን ጠብቃችሁ መኖር ትችላላችሁ?

  •   ቤተሰብ። አሁን ላይ የቤተሰብ ኃላፊነት አለባችሁ? ወደፊትስ ምን ዓይነት ኃላፊነቶች ሊኖሩባችሁ ይችላሉ? ልጆች መውለድ ትፈልጋላችሁ? ከሆነስ ስንት?

 እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ስትወያዩ ግልጽና ሐቀኛ ሁኑ። ሌላኛውን ወገን ለማስደሰት ስትሉ ብቻ እውነታውን ከመደበቅ ወይም ከማዛባት ተቆጠቡ።—ዕብራውያን 13:18

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ስለ ፍቅረኛህ የትኞቹን ነገሮች ማወቅ ይኖርብሃል? እሷስ ስለ አንተ ምን ማወቅ ይኖርባታል? ወደፊት ትዳር ለመመሥረት ከወሰናችሁ አሁን ላይ በግልጽ መወያየታችሁ ያኔም በሐቀኝነት እንድትነጋገሩ መንገድ የሚጠርግላችሁ እንዴት ነው?

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “እውነትን ተነጋገሩ።”—ኤፌሶን 4:25

 “እሷ ‘በስድስት ወር ውስጥ መተጫጨታችን አይቀርም’ ብላ ታስብ ይሆናል፤ እሱ ግን ‘ከአንድ ዓመት በኋላ’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። በዚህ ጊዜ እሷ ልትጎዳና ግራ ልትጋባ ትችላለች፤ ምክንያቱም ይህን ያህል ጊዜ ይዘገያል ብላ አስባ አታውቅም። ስለዚህ ሁለቱም ስለ ጉዳዩ ተመሳሳይ አመለካከት መያዛቸው አስፈላጊ ነው።”—አሪያና፣ በትዳር አንድ ዓመት የቆየች።

 የአመለካከት ልዩነት እንደሚኖር ጠብቅ

 ፍጹም አንድ ዓይነት የሆኑ ሰዎች የሉም። ስለዚህ አንተና የፍቅር ጓደኛህ በሁሉም ነገር እንደምትስማሙ ወይም ለነገሮች ያላችሁ ስሜት ተመሳሳይ እንደሚሆን አትጠብቅ። እንደ ባሕልና አስተዳደግ ያሉት ነገሮች አመለካከታችሁን ይቀርጹታል።

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ በጥቃቅን ጉዳዮች በመካከላችሁ ልዩነት ሲፈጠር በግልጽ የተቀመጠ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ እስከሌለ ድረስ ሁለታችሁም ለሰላም ስትሉ ለመስማማት ፈቃደኛ ናችሁ?

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።”—ፊልጵስዩስ 4:5

 “‘በሁሉም ነገር የምንጣጣም ሰዎች ነን’ ብላችሁ ብታስቡ እንኳ በመካከላችሁ ልዩነት መኖሩ አይቀርም። በፍቅር ግንኙነት ውስጥ መጣጣም አስፈላጊ ቢሆንም ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ልዩነት በሚፈጠርበት ጊዜ ሁለቱም ወገን የሚያሳዩት ባሕርይ ነው።”—ማቲው፣ በትዳር አምስት ዓመት የቆየ።

 የፍቅር ጓደኝነት ውጥረት እንደሚፈጥር ጠብቅ

 የፍቅር ጓደኝነት ብዙ ጊዜህን እንደሚወስድብህና በተወሰነ መጠን ውጥረት ሊፈጥርብህ እንደሚችል አይካድም። ታዲያ ምን ሊረዳህ ይችላል?

 ምክንያታዊ ገደቦች አብጅ። በፍቅር ሕይወትህ በጣም ከመጠመድህ የተነሳ ሌሎች ኃላፊነቶችህን ወይም ሌሎች ጓደኞችህን ችላ እንዳትል ተጠንቀቅ። ለአምስት ዓመት በትዳር የቆየች አላና የተባለች ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ካገባችሁ በኋላም ጓደኞቻችሁ ያስፈልጓችኋል፤ እናንተም ታስፈልጓቸዋላችሁ። ገና ለገና የፍቅር ጓደኛ ያዝኩ ብላችሁ ችላ አትበሏቸው።”

 ካገባህ በኋላ ሁሉንም የሕይወትህን ገጽታዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማስኬድ እንደሚያስፈልግህ አስታውስ። ታዲያ ሚዛን አስጠብቆ የመሄዱን ጉዳይ ለምን ከወዲሁ አትጀምርም?

 ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ የፍቅር ጓደኛህ ከልክ ያለፈ ጊዜና ትኩረት እንድትሰጥህ ትጠብቃለህ? እሷስ ከአንተ ብዙ እንደምትጠብቅ ይሰማሃል? በፍቅር ግንኙነታችሁ ውስጥ ሁለታችሁም እንዳትዝሉ ወይም መፈናፈኛ እንዳጣችሁ እንዳይሰማችሁ ሚዛናዊ መሆን የምትችሉት እንዴት ነው?

 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወን ነገር ሁሉ ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1

 “የፍቅር ጓደኛሞች አብረው ጊዜ የሚያሳልፉት በመዝናናት ብቻ ከሆነ የትዳር ሕይወት ሊያስደነግጣቸው ይችላል። ጥንዶች አስቤዛ እንደ ማድረግ፣ የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንደ መሥራትና በአምልኮ እንደ መካፈል ባሉ መደበኛ የሕይወት እንቅስቃሴዎች አብረው መካፈላቸው ጥሩ ነው። ይህም ለትዳራቸው ጥሩ መሠረት ለመጣል ይረዳቸዋል።”—ዳንኤል፣ በትዳር ሁለት ዓመት የቆየ።

 የፍቅር ጓደኝነት ወደ ውሳኔ የሚመራ ጊዜያዊ ሂደት እንደሆነ አስታውስ፤ ውሳኔው ወይ መጋባት ወይም የፍቅር ግንኙነቱን ማቆም ሊሆን ይችላል። የዚህ ተከታታይ ርዕስ ክፍል 3 ከዚህ ውሳኔ ጋር በተያያዘ ልታስብባቸው የሚገቡ ነጥቦችን ያብራራል።