በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የማልፈልገውን ነገር የምናገረው ለምንድን ነው?

የማልፈልገውን ነገር የምናገረው ለምንድን ነው?

 “አንዳንዴ አንደበቴን በመቆጣጠር ረገድ ይሳካልኛል፤ አንዳንዴ ግን አእምሮዬ አንደበቴን መቆጣጠር የተሳነው ይመስል እንዳመጣልኝ እናገራለሁ!” —ጄምስ

 “ፍርሃት ሲሰማኝ እንዳመጣልኝ እናገራለሁ፤ ዘና ስል ደግሞ ብዙ አወራለሁ። በአጭር አነጋገር፣ ሁሌም ስናገር እዘባርቃለሁ ማለት ይቻላል።”—ማሪ

 መጽሐፍ ቅዱስ “ምላስ . . . እሳት ናት” እንዲሁም “በጣም ሰፊ የሆነን ጫካ በእሳት ለማያያዝ ትንሽ እሳት ብቻ ይበቃል!” ይላል። (ያዕቆብ 3:5, 6) በምትናገረው ነገር የተነሳ ብዙ ጊዜ ችግር ውስጥ ትወድቃለህ? ከሆነ ይህ ርዕስ ሊረዳህ ይችላል።

 የማልፈልገውን ነገር የምናገረው ለምንድን ነው?

 የወረስነው ኃጢአት። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለንና። በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር . . . ፍጹም ሰው ነው።” (ያዕቆብ 3:2) የወረስነው ኃጢአት፣ በአረማመዳችን ብቻ ሳይሆን በንግግራችንም እንድንሰናከል ያደርገናል።

 “አእምሮዬና ምላሴ ፍጽምና የጎደላቸው እስከሆኑ ድረስ ሁለቱንም ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እችላለሁ ብዬ ብናገር ሞኝነት ይሆንብኛል።”—አና

 ብዙ ማውራት። መጽሐፍ ቅዱስ “ከቃላት ብዛት ስህተት አይታጣም” ይላል። (ምሳሌ 10:19) ብዙ የሚያወሩና ጥቂት የሚያዳምጡ ሰዎች አጉል ነገር ተናግረው ሌሎችን ቅር የማሰኘት አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው።

 “አንድ ሰው ብዙ ስላወራ አዋቂ ነው ማለት አይደለም። ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች መካከል በእውቀቱ ተወዳዳሪ የሌለው ቢሆንም ከመናገር የተቆጠበባቸው ጊዜያት ነበሩ።”—ጁሊያ

 ተረብ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል” ይላል። (ምሳሌ 12:18) “ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል” ተብሎ ሊፈረጅ ከሚችል አነጋገር ውስጥ አንዱ ተረብ ነው፤ ተረብ ሌሎችን ለማዋረድ ተብሎ የሚነገር ጎጂ ንግግር ነው። ሌሎችን የሚተርቡ ሰዎች “ቀልዴን እኮ ነው!” ይሉ ይሆናል። ሆኖም ሌሎችን ማዋረድ ፈጽሞ እንደ ቀልድ የሚታይ ጉዳይ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “ስድብ ሁሉ እንዲሁም ክፋት ሁሉ ከእናንተ መካከል ይወገድ” በማለት ይመክረናል።—ኤፌሶን 4:31

 “በጣም ተጫዋች ነኝ፤ እንዲሁም ሰዎችን ማሳቅ ደስ ይለኛል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ በቀላሉ ወደ ተረብ ሊመሩ ይችላሉ። በዚህ ምክንያት በተደጋጋሚ ችግር ውስጥ እወድቃለሁ።”—ኦክሳና

የጥርስ ሳሙና አንዴ ካወጣችሁ በኋላ ወደ ዕቃው መመለስ እንደማትችሉ ሁሉ የተናገራችሁትንም ነገር መመለስ አትችሉም

 ምላስን መቆጣጠር

 ምላስን መቆጣጠር ቀላል ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም በዚህ ረገድ የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ እስቲ የሚከተሉትን ጥቅሶች ተመልከት።

 “የምትናገሩትን . . . በልባችሁ ተናገሩ፤ ጸጥም በሉ።”—መዝሙር 4:4

 አንዳንድ ጊዜ ከሁሉ የተሻለው ምላሽ ዝምታ ነው። ሎራ የተባለች ወጣት “በተበሳጨሁበት ወቅት የሚሰማኝ ስሜት በኋላ ላይ ሊቀየር ይችላል” በማለት ተናግራለች። አክላም “ከተረጋጋሁ በኋላ ሳስበው አብዛኛውን ጊዜ፣ ልናገር አስቤ የነበረውን ነገር ባለመናገሬ ደስ ይለኛል” ብላለች። ሌላው ቀርቶ ለጥቂት ሴኮንዶች እንኳ ቆም ብለህ ማሰብህ በኋላ ላይ የምትቆጭበትን ነገር ከመናገር ሊጠብቅህ ይችላል።

 “ምላስ የምግብን ጣዕም እንደሚለይ ሁሉ፣ ጆሮስ ቃላትን አያመዛዝንም?”—ኢዮብ 12:11

 የሚከተሉትን ጥያቄዎች ተጠቅመህ፣ ወደ አእምሮህ የሚመጣውን ነገር የምታመዛዝን ከሆነ ራስህን ከብዙ ሐዘን ታድናለህ፦

  •   እውነት ነው? ደግነት የሚንጸባረቅበት ነው? አስፈላጊስ ነው?—ሮም 14:19

  •   ሌላ ሰው እኔን እንደዚህ ቢለኝ ምን ይሰማኛል?—ማቴዎስ 7:12

  •   የግለሰቡን አመለካከት እንደማከብር ያሳያል?—ሮም 12:10

  •   ይህን ለመናገር ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው?—መክብብ 3:7

 “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።”—ፊልጵስዩስ 2:3

 ይህ ምክር ለሌሎች ጥሩ አመለካከት እንድታዳብር ይረዳሃል፤ ይህ ደግሞ ምላስህን እንድትቆጣጠርና ከመናገርህ በፊት ቆም ብለህ እንድታስብ ያግዝሃል። እንዲህ ሳታደርግ ቀርተህ ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ብትናገር እንኳ ትሕትና በተቻለ ፍጥነት ይቅርታ እንድትጠይቅ ያነሳሳሃል! (ማቴዎስ 5:23, 24) ለወደፊቱ ምላስህን በመቆጣጠር ረገድ እየተሻሻልክ ለመሄድ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።