በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

ከተጠመቅኩ በኋላ ምን ማድረግ ያስፈልገኛል?—ክፍል 2፦ ንጹሕ አቋምህን ጠብቀህ ኑር

ከተጠመቅኩ በኋላ ምን ማድረግ ያስፈልገኛል?—ክፍል 2፦ ንጹሕ አቋምህን ጠብቀህ ኑር

 መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “ንጹሕ አቋም ይዘው የሚመላለሱትን ይሖዋ አንዳች መልካም ነገር አይነፍጋቸውም።” (መዝሙር 84:11) ‘ንጹሕ አቋም ይዞ መመላለስ’ ሲባል ምን ማለት ነው? ራስህን ለይሖዋ ስትወስን የገባኸውን ቃል እንደምታከብር በሚያሳይ መንገድ መኖር ማለት ነው። (መክብብ 5:4, 5) ከተጠመቅክ በኋላም ንጹሕ አቋም ይዘህ መመላለስ የምትችለው እንዴት ነው?

በዚህ ርዕስ ላይ

 ችግሮችን በጽናት ተቋቋም

 ቁልፍ ጥቅስ፦ “በብዙ መከራ አልፈን ወደ አምላክ መንግሥት መግባት አለብን።”—የሐዋርያት ሥራ 14:22

 ምን ማለት ነው? ሁሉም ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ውስጥ ችግሮች እንደሚያጋጥሟቸው መጠበቁ ምክንያታዊ ነው። አንዳንድ ችግሮች የሚገጥሙህ ለምሳሌ ፌዝ ወይም ተቃውሞ የሚደርስብህ ክርስቲያን ስለሆንክ ብቻ ነው። ሌሎቹ ችግሮች ግን ማንኛውም ሰው ላይ ሊደርሱ የሚችሉ ናቸው፤ ለምሳሌ የገንዘብ ችግር ወይም ሕመም።

 ምን ሊያጋጥምህ ይችላል? የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በሕይወት ውስጥ ለውጥ ማጋጠሙ አይቀርም፤ አንዳንዶቹን ለውጦች መቀበል ግን ከባድ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው መጥፎ ነገሮች ማንኛውም ሰው ላይ ሊደርሱ ይችላሉ፤ ክርስቲያን ሆነም አልሆነ።—መክብብ 9:11

 ምን ማድረግ ትችላለህ? በሕይወትህ ውስጥ ችግሮች እንደሚያጋጥሙህ ስላወቅክ ከአሁኑ ተዘጋጅ። የሚያጋጥሙህን ችግሮች እምነትህን ለማጠናከርና በይሖዋ ይበልጥ ለመታመን እንደሚያስችሉህ አጋጣሚዎች አድርገህ ተመልከታቸው። (ያዕቆብ 1:2, 3) በኋላ ላይ፣ ከራስህ ተሞክሮ ተነስተህ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ መናገር ትችላለህ፦ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ።”—ፊልጵስዩስ 4:13

 እውነተኛ ታሪክ። “ከተጠመቅኩ ብዙም ሳይቆይ ወንድሞቼ እውነትን ተዉ፤ ወላጆቼ ታመሙ፤ በኋላ ላይ ደግሞ እኔም ታመምኩ። ሁኔታው ተስፋ የሚያስቆርጥ ነበር፤ ራሴን ለአምላክ ስወስን በሕይወቴ ውስጥ ምንጊዜም የእሱን አምልኮ ለማስቀደም የገባሁትን ቃል ለመተው ተፈትኜ ነበር። ግን ችግሮቼን ለመቋቋም የረዳኝም እሱ ነው፤ ራሴን ለይሖዋ ስወስን የገባሁት ቃል።”—ካረን

 ጠቃሚ ምክር፦ ስለ ዮሴፍ ለማወቅ ጥረት አድርግ። ስለ ዮሴፍ ታሪክ ለማወቅ ዘፍጥረት ምዕራፍ 37⁠ን እና ከ39 እስከ 41⁠ን ማንበብ ትችላለህ። እነዚህን ጥያቄዎች አስብባቸው፦ ዮሴፍ ምን ያልተጠበቁ ችግሮች አጋጥመውታል? ችግሮቹን የተወጣው እንዴት ነው? ይሖዋ የረዳውስ እንዴት ነው?

 ተጨማሪ እገዛ ያስፈልግሃል?

 ለኃጢአት ፈተናዎች እጅ አትስጥ

 ቁልፍ ጥቅስ፦ “እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምኞት ሲማረክና ሲታለል ይፈተናል።”—ያዕቆብ 1:14

 ምን ማለት ነው? ሁላችንም መጥፎ ነገር ለማድረግ የምንፈተንበት ጊዜ አለ።

 ምን ሊያጋጥምህ ይችላል? ከተጠመቅህ በኋላም ‘የሥጋ ምኞቶች’ ይኖሩሃል። (2 ጴጥሮስ 2:18) ሌላው ቀርቶ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት ለመፈጸምም ትፈተን ይሆናል።

 ምን ማድረግ ትችላለህ? ፈተና ውስጥ ከመግባትህ በፊት አሁኑኑ ወስን፤ በስሜት ተነድተህ ማንኛውንም እርምጃ ላለመውሰድ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ኢየሱስ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም” በማለት የተናገረውን ሐሳብ አስታውስ። (ማቴዎስ 6:24) ጌታህ ማን እንደሚሆን መምረጥ ትችላለህ። ምርጫህ ይሖዋ ይሁን። መጥፎ ነገር ለማድረግ የሚፈትንህ ስሜት ምንም ያህል ጠንካራ ቢሆን እጅ አለመስጠት ትችላለህ፤ ምርጫው የአንተ ነው!—ገላትያ 5:16

 ጠቃሚ ምክር፦ ጠንካራና ደካማ ጎንህን ለይ። ያሉህን ጥሩ ባሕርያት እንድታዳብር የሚረዱህ ጓደኞች ምረጥ። ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ይበልጥ ፈታኝ እንዲሆንብህ ከሚያደርጉ ሰዎች፣ ቦታዎችና ሁኔታዎች ደግሞ ራቅ።—መዝሙር 26:4, 5

 ተጨማሪ እገዛ ያስፈልግሃል?

 ቅንዓትህን አቀጣጥል

 ቁልፍ ጥቅስ፦ “እስከ መጨረሻው . . . ያንኑ ትጋት እንድታሳዩ እንመኛለን፤ ይህም . . . ዳተኞች እንዳትሆኑ ነው።”—ዕብራውያን 6:11, 12

 ምን ማለት ነው? ሥራው ላይ የማያተኩር ሰው እየለገመ ይሄዳል፤ ዳተኛ ወይም ሰነፍ ይሆናል።

 ምን ሊያጋጥምህ ይችላል? የተጠመቅክ ሰሞን ይሖዋን ለማገልገል ያለህ ስሜትና ቅንዓትህ ልዩ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይሖዋንም በጣም ትወደው ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ይሖዋን መታዘዝ እየከበደህ ሄዶ ይሆናል፤ ይህም ተስፋ ሊያስቆርጥህና ቅንዓትህ እንዲቀዘቅዝ ሊያደርግ ይችላል።—ገላትያ 5:7

 ምን ማድረግ ትችላለህ? ውስጥህ አድርግ አድርግ ባይልህም እንኳ ትክክለኛውን ነገር ማድረግህን ቀጥል። (1 ቆሮንቶስ 9:27) ስለ ይሖዋ ይበልጥ በመማርና አዘውትረህ ከእሱ ጋር በጸሎት በመነጋገር በሰማይ ካለው አባትህ ጋር መቀራረብህንም ቀጥል። ከዚህም ሌላ ይሖዋን ማገልገል ከሚያስደስታቸው ሰዎች ጋር ያለህን ጓደኝነት አጠናክር።

 ጠቃሚ ምክር፦ ይሖዋ በጣም እንደሚወድህና ምንጊዜም ሊረዳህ ዝግጁ እንደሆነ አስታውስ። ለጊዜው ቅንዓትህ ቢቀዘቅዝም እንኳ አዝኖብኛል ብለህ ለመደምደም አትቸኩል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ “ለደከመው ኃይል፣ ጉልበት ለሌላቸውም የተሟላ ብርታት ይሰጣል” ይላል። (ኢሳይያስ 40:29) ቅንዓትህን ለማቀጣጠል የምታደርገውን ጥረት ይባርክልሃል።

 ተጨማሪ እገዛ ያስፈልግሃል?

 ዋናው ነጥብ፦ ንጹሕ አቋም ይዘህ የምትመላለስ ከሆነ የይሖዋን ልብ ደስ ማሰኘት ትችላለህ! (ምሳሌ 27:11) ከእሱ ጎን ለመሰለፍ በመምረጥህ በጣም ይደሰታል፤ ደግሞም የሰይጣንን ጥቃት ለመቋቋም የሚያስፈልግህን እርዳታ ሁሉ ያደርግልሃል።