በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የወጣቶች ጥያቄ

የፆታ ጥቃትን በተመለከተ ማወቅ ያለብኝ ነገር ምንድን ነው?—ክፍል 2፦ ከጥቃቱ ማገገም

የፆታ ጥቃትን በተመለከተ ማወቅ ያለብኝ ነገር ምንድን ነው?—ክፍል 2፦ ከጥቃቱ ማገገም

 የጥፋተኝነትን ስሜት መቋቋም

 የፆታ ጥቃት የተፈጸመባቸው ብዙ ሰዎች ከፍተኛ የኀፍረት ስሜት ያድርባቸዋል። ሌላው ቀርቶ ለተፈጠረው ነገር ጥፋተኞቹ እነሱ እንደሆኑ ሊሰማቸው ይችላል። ካረን የተባለችውን የ19 ዓመት ወጣት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ካረን ከ6 እስከ 13 ዓመቷ ባለው ጊዜ ውስጥ የፆታ ጥቃት ተፈጽሞባት ነበር። እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ከሁሉ ይበልጥ ለመቋቋም የከበደኝ ነገር የጥፋተኝነት ስሜት ነው። ‘ይህን ለሚያህል ጊዜ ጥቃቱ ሲፈጸም ዝም ብዬ ያለፍኩት ለምንድን ነው?’ እያልኩ አስባለሁ።”

 አንቺም a እንዲህ የሚሰማሽ ከሆነ ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ተመልከቺ፦

  •   ልጆች የግብረ ሥጋ ግንኙነት ለመፈጸም በአካልም ሆነ በስሜት ዝግጁ አይደሉም። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ምን ማለት እንደሆነ ስለማያውቁ በደንብ ገብቷቸውና ወደው እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ሊፈጽሙ አይችልም። በመሆኑም በፆታ የተነወረ አንድ ልጅ ድርጊቱ የተፈጸመበት በእሱ ጥፋት አይደለም።

  •   ልጆች አዋቂዎችን የማመን ዝንባሌ ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ብልግና የሚፈጽሙ ሰዎች ስለሚጠቀሙባቸው የተንኮል ዘዴዎች ምንም የሚያውቁት ነገር የለም፤ ይህ ደግሞ ልጆች ለጥቃት የተጋለጡ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ዘ ራይት ቱ ኢኖሰንስ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው ከሆነ “ሌሎችን በፆታ የሚያስነውሩ ሰዎች የተዋጣላቸው አታላዮች ስለሆኑ ልጆች የእነሱን የተንኮል ዘዴዎች ሊነቁባቸው አይችሉም።”

  •   አንድ ልጅ ጥቃቱ በሚፈጸምበት ወቅት የፆታ ስሜቱ ሊነሳሳ ይችላል። አንቺም እንዲህ ዓይነት ስሜት ተሰምቶሽ ከሆነ ሰውነታችን ለየት ባለ መንገድ ሲነካ የሚሰጠው ተፈጥሯዊ ምላሽ ውጤት እንጂ በድርጊቱ እንደተስማማሽ የሚያሳይ ነገር እንዳልሆነ እርግጠኛ ሁኚ። በመሆኑም የፆታ ጥቃቱ የተፈጸመብሽ ተስማምተሽ ነው ሊባል አይችልም ወይም ለተፈጸመው ነገር ተጠያቂ ነሽ ማለት አይደለም።

 ጠቃሚ ሐሳብ፦ እስቲ ጥቃቱ በተፈጸመብሽ ወቅት በነበረሽ ዕድሜ ላይ የምትገኝን አንዲት ልጅ ለማሰብ ሞክሪ። ከዚያም ራስሽን እንዲህ እያልሽ ጠይቂ፦ ‘ይህች ልጅ በዚህ ዕድሜዋ የፆታ ጥቃት ቢፈጸምባት ለድርጊቱ እሷን ተጠያቂ ማድረግ ተገቢ ይሆናል?’

 ካረን ሦስት ትናንሽ ልጆችን ሞግዚት ሆና መጠበቅ ስትጀምር ይህን ጥያቄ አስባበት ነበር፤ ከምትንከባከባቸው ልጆች መካከል አንዱ ስድስት ዓመት ገደማ የሚሆነው ሲሆን ይፈጸምባት የነበረው የፆታ ጥቃት የጀመረው እሷ በዚህ ዕድሜ እያለች ነበር። ካረን እንዲህ ብላለች፦ “በዚህ ዕድሜ ያለ ልጅ ምንም ስለማያውቅ ምን ያህል ለጥቃት የተጋለጠ እንደሆነ በሌላ አባባል እኔም ምን ያህል ለጥቃት የተጋለጥኩ እንደነበርኩ ተገነዘብኩ።”

 እውነታው፦ ለተፈጸመብሽ ጥቃት ተጠያቂው ጥቃቱን የፈጸመብሽ ሰው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የክፉውም ሰው ክፋት የሚታሰበው በራሱ ላይ ብቻ ነው” ይላል።​—ሕዝቅኤል 18:20

 ጉዳዩን ለሚታመን ሰው መናገር ያለው ጥቅም

 ስለተፈጸመብሽ ጥቃት ለምታምኚው አዋቂ ሰው መናገርሽ እፎይታ እንዲሰማሽ ሊያደርግ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው” ይላል።​—ምሳሌ 17:17

 ስለተፈጠረው ነገር ለሌላ ሰው ከመናገር በመቆጠብ ራስሽን ከጉዳት መጠበቅ እንደምትችይ ሆኖ ይሰማሽ ይሆናል። ምናልባትም ዝምታ የባሰ ጉዳት እንዳይደርስብሽ ለመከላከል የገነባሽው አጥር ሊሆን ይችላል። ይሁንና ራስሽን ከጉዳት ለመከላከል የገነባሽው ይህ የዝምታ አጥር እርዳታ ከማግኘት ሊከለክልሽም እንደሚችል አትርሺ።

ራስሽን ከጉዳት ለመከላከል የገነባሽው የዝምታ አጥር እርዳታ ከማግኘት ሊከለክልሽም ይችላል

 ጃኔት የተባለች ወጣት ስለተፈጸመባት ጥቃት መናገሯ ከፍተኛ እፎይታ እንዲሰማት አድርጓል። እንዲህ ብላለች፦ “አንድ የማውቀውና የማምነው ሰው ገና በትንሽነቴ በፆታ ያስነውረኝ ጀመር፤ ጉዳዩን ለዓመታት ለራሴ አምቄ ለመያዝ ሞከርኩ። የተፈጠረውን ነገር ለእናቴ ከነገርኳት በኋላ ግን ትልቅ ሸክም ከላዬ ላይ የወረደልኝ ያህል ቅልል አለኝ።”

 ጃኔት ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት የፆታ ጥቃት የተፈጸመባቸው አንዳንድ ሰዎች ስለ ጉዳዩ ለመናገር የሚፈሩት ለምን እንደሆነ ስትናገር “የፆታ ጥቃት ለማውራት ደስ የማይል ነገር ነው” ብላለች። አክላም “እኔ በራሴ ሁኔታ እንደተመለከትኩት ከሆነ ግን በዝምታ ችግሩን አምቆ መኖር በጣም ይጎዳል። ስለ ጉዳዩ ሳልዘገይ መናገሬ ጠቅሞኛል” በማለት ተናግራለች።

 ‘ለመፈወስ ጊዜ አለው’

 የተፈጸመብሽ የፆታ ጥቃት ስለ ራስሽ መጥፎ አመለካከት እንዲኖርሽ አድርጎሽ ይሆናል፤ ለምሳሌ ከዚህ በኋላ ዋጋ እንደሌለሽና ምንም እንደማትረቢ ወይም የተፈጠርሽው የሌሎችን የፆታ ስሜት ለማርካት እንደሆነ እንዲሰማሽ አድርጎ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ለመፈወስም ጊዜ አለው” ይላል፤ በመሆኑም እንዲህ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን ማስወገድ የምትችዪበት አጋጣሚ አሁን ነው። (መክብብ 3:3) ታዲያ በዚህ ረገድ ምን ሊረዳሽ ይችላል?

 መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ሐሳብ ይነግረናል፤ ይህ ደግሞ ስለ ራስሽ ያደረብሽን የተሳሳተ አመለካከት ጨምሮ “ምሽግን ለመደርመስ የሚያስችል . . . ኃይል” አለው። (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5) ለምሳሌ የሚከተሉትን ጥቅሶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አውጥተሽ በማንበብ አስቢባቸው፦ ኢሳይያስ 41:10፤ ኤርምያስ 31:3፤ ሚልክያስ 3:16, 17፤ ሉቃስ 12:6, 7፤ 1 ዮሐንስ 3:19, 20

 ጸሎት። እንደማትረቢ ሲሰማሽ ወይም በጥፋተኝነት ስሜት ስትዋጪ በጸሎት አማካኝነት ‘ሸክምሽን በይሖዋ ላይ ጣዪ።’ (መዝሙር 55:22) መቼም ቢሆን ብቻሽን አይደለሽም!

 የጉባኤ ሽማግሌዎች። እነዚህ ክርስቲያን ወንዶች “ከነፋስ እንደ መከለያ፣ ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ” ለመሆን የሚያስችላቸውን ሥልጠና አግኝተዋል። (ኢሳይያስ 32:2) ስለ ራስሽ ተገቢ አመለካከት እንዲኖርሽ እንዲሁም በወደፊት ሕይወትሽ ላይ ትኩረት እንድታደርጊ ሊረዱሽ ይችላሉ።

 ጥሩ ጓደኞች። በክርስትና ሕይወታቸው ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑሽ የሚችሉ ወንዶችንና ሴቶችን ለመመልከት ሞክሪ። እነዚህ ሰዎች አንዳቸው ሌላውን እንዴት እንደሚይዙ አስተውዪ። በሚቀርቧቸው ሰዎች ላይ ጥቃት የሚፈጽሙት ሁሉም ሰዎች እንዳልሆኑ እየተረዳሽ ትመጫለሽ።

 ታንያ የተባለች አንዲት ወጣት ይህን አስፈላጊ ትምህርት አግኝታለች። ከትንሽነቷ ጀምሮ በርካታ ወንዶች የፆታ መጠቀሚያ አድርገዋት ነበር። ታንያ “እቀርባቸው የነበሩ ወንዶች ሁሉ ጎድተውኛል” በማለት ተናግራለች። ከጊዜ በኋላ ግን እውነተኛ ፍቅር የሚያሳዩ ወንዶች እንዳሉ ተገነዘበች። ይህን መገንዘብ የቻለችው እንዴት ነው?

 ታንያ በክርስትና ሕይወታቸው ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኑ ባልና ሚስት ጋር አብራ ጊዜ ማሳለፍ ከጀመረች በኋላ አመለካከቷ ተቀየረ። እንዲህ ብላለች፦ “ባልየው የሚያደርገውን ነገር ስመለከት ሁሉም ወንዶች በሌሎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙ ተረዳሁ። ባልየው ሚስቱን ይንከባከባት ነበር፤ የአምላክ ዓላማም ቢሆን እንዲህ እንዲሆን ነው።” b​—ኤፌሶን 5:28, 29

a ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በሴት ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

b ከባድ የመንፈስ ጭንቀት፣ የአመጋገብ ችግር፣ ራስን የመጉዳት ልማድ፣ ዕፆችንና መድኃኒቶችን ያለአግባብ የመጠቀም ልማድ፣ የእንቅልፍ ችግር ካለብሽ ወይም ራስሽን የማጥፋት ሐሳብ የሚመጣብሽ ከሆነ የሕክምና ባለሙያ ማማከርሽ የተሻለ ነው።